በሰላም ቀን ማረስ ፣ በክፉ ቀን የወገን አለኝታነቱ የቆዬ መገለጫ ነው። ጀግና ሲተኩስ ብቻ ሳይሆን ሲራመድም ያስፈራል። ልቡ ሸፍቶ ከቤት ሲወጣ ፊቱ ባሻገር ይጋረፋል።

1040
“ኧረ ምን ትወልድ ምን ታምጥ እናት
ያረማመዱ የአንገቱ ጥራት
አጀብ ያሰኛል የልቡ ኩራት”
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 16/2013 ዓ.ም (አብመድ) በሰላም ቀን ማረስ ፣ በክፉ ቀን የወገን አለኝታነቱ የቆዬ መገለጫ ነው። ጀግና ሲተኩስ ብቻ ሳይሆን ሲራመድም ያስፈራል። ልቡ ሸፍቶ ከቤት ሲወጣ ፊቱ ባሻገር ይጋረፋል።
“እስኪ ትጠየቅ የጀግናው እናት፣
ሰው የማያውቀው ሚስጥር እንዳላት” እንዳለ የኢትዮጵያ እናት ጀግና መውለድን ታውቅበታለች። ሲቸግር የሚጠራ፣ ዘምቶ የሚያኮራ፣ የልብ የሚሰራ፣ ጠላትን በግርማው የሚያስፈራ ልጅ ትወልዳለች- ኢትዮጵያ።
ጀግንነት የሚታደሉት፣ ከዘር የሚቀበሉት፣ የሚኖሩት እንጂ የሚገዙት ወይም የሚመኙት አይደለም። ጀግንነት ለኢትዮጵያዊያን ቀዳሚው ታሪካቸው ነው። ጀግና መሆን ያስከብራል። ኢትዮጵያ ተከብራ የኖረችው ጀግና ልጆች ስላሏት እንጂ ስለተዛነላት አይደለም። በጀግኖች ልጆቿ ዳሯን እሳት አድርጋ የኖረች፣ እየኖረች ያለችና የምትኖር ሃገር ናት።
በኢትዮጵያውያን ጀግኖች የማይቀና የለም።
“ለወዳጁ ማር ለጠላት ኮሶ፣
ካልደረሱበት አይነካም ደርሶ” የተባለለት የኢትዮጵያ ጀግና ደርሶ በማናለብኝነት የሰውን ድንበር ጥሶ አይረግጥም። ምንም ቢሰራ የራሱን መሬት በስንዝር አይሰጥም። ቃሉ አይለወጥም። ራቅ ሲል በጠመንጃ፣ ቀረብ ሲል በሳንጃ እየቀላ ጠላቱን አይቀጡ ቅጣት እየቀጣ ይመልሳል።
ኢትዮጵያ ከቀደሙት በቀደመው፣ ከዘመኑት በዘመነው የረጅም ጊዜ ታሪኳ አያሌ ጦርነቶች ገጥመዋታል። ታዲያ በዘመናት ሂደት የገጠማትን ጦርነት ሁሉ እያሸነፈች፣ የጠላትን አንገት እያስደፋች ከክብር ላይ ክብር፣ ከታሪክ ላይ ታሪክ እየጨመረች የኖረች ሀገር ናት። ባሕር ማዶ ይሁን ከአብራኳ ተወልዶ የሚገጥማት ጠላት ብዙ ነው። ፍቅር ስትፍልግ ፀብ የሚመጣባት፣ ወርቅ ስታበድር ጠጠር የሚመለስላት፣ ጥበብ ስታስተምር ጥበብሽ የእኛ ነው የምትባል ሀገር ከኢትዮጵያ ውጭ ያለ አይመስልም። ብዙ ጊዜ ትከዳለች ሁሉንም ግን ታሸንፋለች።
ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን ከከዱት መካከል አንደኛው ትህነግ ነው። ትህነግ ሆድ እንጂ አንጄት የሌለው የቡድን ስብስብ ነበር። ከትጥቅ ትግል ጀምሮ ተመልሶ እስከ ትጥቅ ትግል እስከሚገባበት ድረስ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን በድሏል። ይህ ቡድን ከበደል ላይ በደል እየጨመረ ዓመታትን ሲዘልቅ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ስለ ፍቅርና ስለሀገር ብለው ታግሰውት ኖረዋል። ትዕግስትን ፍረሃት፣ ማስተዋልን ሞኝነት፣ ሀገር ማለትን ደግሞ የድሮ ስርዓት ናፋቂነት አድርጎ የወሰደው ትህነግ ሞት ሲጠራው መጥፊያው ሲደርስ መከላከያ ሠራዊቱን ተዳፈረ። የአማራ ክልልንም ለማጥቃት ጥቃት ሰነዘረ። ለዓመታት የቆዬው ትዕግስት ወደ ንዴት ሲለወጥ የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኀይልና ሚሊሻ አሳምነው ቀጡት።
በሕግ ማስከበሩ ዘመቻ ታላቅ ጅብዱ ከፈፀሙት የአማራ ልዩ ኀይል አባላት መካከል በትግል ላይ በካሜራ እይታ ውስጥ የገባ አንድ ጀግና የልዩ ኀይል አባል አለ። የዚህ ጀግና ምስል በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች በሰፊው ሲንሸራሸር ቆይቷል። የጀግናውን ምስል ከታዋቂው የፊልም ባለሙያ ሽዋንዚገር ጋር በማመሳሰል ኢትዮጵያዊ ሽዋንግዛው የሚል ስም ተሰጥቶታል። ይሄን ጀግና የልዩ ኃይል አባል ጠላቱን ድል አድርጎ በተቀመጠበት በወፍላ ተራራዎች ላይ አግኝተነዋል። ምክትል ሳጅን ሁሴን አብዱ ይባላል። ብዙዎች በዘመቻው በወጣለት ስም ሽዋንግዛው ብለው ያውቁታል። በአንድ ጥይት አንድ ጠላት አልሞ የሚመታ ብሬን ተኳሽ ነው።
“ኧረ ምን ትወልድ ምን ታምጥ እናት
ያረማመዱ የአንገቱ ጥራት
አጀብ ያሰኛል የልቡ ኩራት” አስፈሪና አኩሪ ግርማ ሞገስ አለው። ጥይቱን በዋዛ አያባክንም ይሉታል ጓደኞቹ። ምላጭ ከሳበ የጥይቱ ማረፊያ ከጠላት ግንባር ላይ ነው። የብዙዎች መነጋገሪያ እና ምልክት የሆነው ምክትል ሳጅን ሁሴን ብዙዎች በትግሉ ሂደት እንደተሰዋ ቢያስወሩበትም እርሱ ግን ዛሬም በህይወት አለ። ሁሴን ውትድርናን የጀመረው በ2003ዓ.ም ነበር። በዚያ ጊዜ ወደ ሀገር መከላከያ ሠራዊት ገብቶ እስከ 2008ዓ.ም ሀገሩን በታማኝነት አገልግሏል። በዚያ ወቅት የትህነግ የፖለቲካ ዙፋን መነቃነቅ የጀመረበት፣ የመሄጃ መስመሩ የጠፋበት ጊዜ ስለነበር ትህነግ ያሰጉኛል የምትላቸውን ልቧ የፈቀደውን ርምጃ ትወስድባቸው ነበር። ሁሴንም በትህነግ ተላላኪ መኮንኖች ያለ ምክንያት የማባረሪያ ደብዳቤ የደረሰው ወታደር ነበር። ባለ ጊዜ ናቸውና ሁሴን እንደተባረረ ሲነገረው ከሚወደው ሙያው ወጥቶ ወደ ቤተሰቦቹ ተመለሰ። ሁሴን ሀገሩንና ሕዝቡን በሚወደው ሙያ ማገልገል ይፈልግ ነበርና በ2011ዓ.ም የአማራ ልዩ ኀይልን ተቀላቀለ።
የባለ ጊዜዎች ዘመን ሲያበቃ ሁሴንን ከመከላከያ ሠራዊት ያስወጡት የትህነግ ታጣቂዎች የመከላከያ ሠራዊት ጎደኞቹን በግፍ ተዳፈረች። “ትህነግ የመከላከያ ሠራዊት ጓደኞቼን ሲነካ በጣም ነው የተሰማኝ። እኔ ብቻ ሳይሆን መላው የልዩ ኀይል አባላት ተሰምቶናል” ነው ያለኝ። የመከላከያ ሠራዊት አባል በነበረበት ጊዜ በሰሜን እዝ በመሆን ሠራዊቱ ለትግራይ ሕዝብ ምን ያደርግ እንደነበር ያውቀዋል። እርሱም እስኪወጣ ድረስ የትግራይን ሕዝብ ሲያገለግል እንደነበር ነግሮኛል። “ትህነግ በ27 ዓመታት በአማራ ክልል ችግር ሲፈጥር ነበር። ማንነትን እስከመቀማት ደርሷል” ያለው ሁሴን ኀይላቸውን ወደ አማራ ክልል ሲያስጠጉ የአማራ ልዩ ኀይል ልማት ላይ እንደነበረ ነው የነገረኝ። ትዕግስታቸው አስገራሚ ነበር ብሏል።
ከሕዝብ ጋር ስላስተዋወቀችው ምስል “የተነሳሁት ዋጃ አካባቢ ነው። ማን እንዳነሳኝ ግን አላስታውስም። በዚያ ሰዓት ቁጭት ውስጥ ነበርን። መከላከያ ከተደፈረ ጀምሮ በቁጭት ውስጥ ነው የነበርነው። በዚያ ሰዓት ሀሳባችን ከጠላት ጋር መተናነቅ ነው” ነበር ያለኝ። ውጊያው ቀጠለ፣ ዋጃ ጥሙጋን እና አላማጣን ተቆጣጥረው ግራ ካሶ ገቡ። ሁሴን ብሬኑን እንዳነገተ ጠላቱን እያነከተ ወደፊት ገሰገሰ። የአማራ ልዩ ኀይል ጀብዱ አጀብ ያሰኝ ነበር።
በግራ ካሶ ውጊያ ብሬን ተኳሹ ሁሴን እና ጓደኞቹ ጠላትን አንገት እያስደፉ፣በአፍ ጢሙ እየደፉ ቀጠሉ። በግራ ካሶ ውጊያ የጠላት ጦር ያለ የሌለ ኀይሉን ተጠቅሞ ለጦርነት የተፈጠረ ከሚመስለው ምቹ ስፍራ ጋር ሆኖ ከባድ ትግል ቢያደርግም መመከት ግን አልቻለም። ሰራዊቱ በእግሩ ከቆቦ ተነስቶ ከምሽግ ምሽግ እየሰበረ፣ ጠላቱን እንደ ፍዬል እያባረረ ገስግሶ ሕዝቡን ነፃ አወጣ። የትህነግ ምሽጎች እንዳልነበሩ ሆኑ።
“ሀገር ጠባቂ ቀንና ማታ፣
ልቡ እንደትጥቁ የማይፈታ”
የአማራ ልዩ ኀይል ልበ ሙሉ ነው። መሸሽ ብሎ ነገር ከዘሩ የለበትም። ሁሴንና ባልደረቦቹን ያገኘንበት የወፍላ ተራራዎች ቅዝቃዜያቸው አያድርስ ነው። ከድንጋይ ሥር ለሕዝብ ሰላም የቆሙት እኒያ ጀግኖች በጀግንነት በሚኖሩበት በዚያ አስቸጋሪ አየር ንበረት እኛ ለሰዓታት መቋቋም አቅቶን ነበር። እነዚያ ጀግኖች ግን ብርዱን ረስተው ለዓላማ ፀንተው ተቀምጠውበታል። “ልብ ከቆረጠ ሁሉም ነገር ቀላል ነው” ነበር ያሉን። እነርሱን አለማክበር አይቻልም። አየር ንብረቱን መቋቋም ብቻ ታላቅ ጀግንነት ነው። የእነርሱ ግን ከዚያም በላይ ነው። ሕዝቡ የሚያደርግላቸው ድጋፍ ለትግላቸው ወኔ እንደጨመረላቸው የነገረኝ ሁሴን ጠላትን እያስለቀቁ በሄዱበት ሁሉ ወተት እየያዘ ሲቀባለቸው እንደነበር ነግሮኛል። “እኛ እንደ አማራ ብቻ ሳይሆን የምናስበው እንደ ኢትዮጵያ ነው። በየትኛውም ቦታ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ለሚመጣ ጠላት ወደ ኋላ አንመለስም። ኢትዮጵያ ከሌለች የሚኖር የለም። በኢትዮጵያ ጉዳይ አንደራደርም” የሁሴን የዘወትር ሀሳብ ነው።
የአማራ ልዩ ኀይል ለሀገር ፍቅር ሲል የተዋደቀና ግዳጁንም በላቀ ጀግንነት የተወጣ ነው። ሁሉም ዜጋ ሀገሩን የመጠበቅ ግዴታ አለበት። ኢትዮጵያ መከበር አለባት። ያለፈውን ካስታወስን ሀገር አንሰራም አሁን መስራት የሚገባንን መሥራት አለብንም ብሏል ምክትል ሳጅን ሁሴን። ከዚያ ቅዝቃዜ በተሞላበት አስቸጋሪ ምድር ሥራውን ወዶ ከጀግና ሕዝብ የወጣ ጀግና ሠራዊት በማዬቴ ደስ አለኝ። ከእነዚያ ጀግኖች የተሻለ ለኢትዮጵያ የሚያስብ፣ በኢትዮጵያ የሚኮራ ያለ አይመስልም። ምን አይነት መታደል ይሆን ራስን ሰጥቶ ለወገን መኖር። ምስጋና ሁሉ ሲያንሳቸው ነው ለመኖራችን ምክንያት ለአንገታችን መቃናት ከፊት ቀድመውልናልና። በእነርሱም ኮርቻለሁ። ሰላም ሁሉ ይሁን።
በታርቆ ክንዴ
Previous articleየቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አመራሮች እጃቸዉን አስገብተው ንፁኃን እንዲጨፈጨፉ እያደረጉ በመሆኑ የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡
Next articleየአላማጣ ከተማ ሰላማዊና የተረጋጋች መሆኗን ጊዜያዊ አስተዳደሩ አስታወቀ።