
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አመራሮች እጃቸዉን አስገብተው ንፁኃን እንዲጨፈጨፉ እያደረጉ በመሆኑ የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 15/2013 ዓ.ም (አብመድ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በቡለን ወረዳ ስለደረሰው ጭፍጨፋ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ ነዋሪዎቹ ‹‹የክልሉ ባለሥልጣናት ዝግ ስብሰባ እያካሄዱ እኛ አካባቢዉን ለቅቀን ለመውጣት ሙከራ ስናደርግ ‹አትውጡ እኛ ስብሰባ የምናካሂደው የወጡትን ለመመለስ ነው› ብለውናል፡፡ ዓላማቸው እኛን ለማስጨረስ ነው፤ ከአንድ ቤተሰብ ብቻ 6 ሰዎች ተገድለዋል›› ብለዋል ነዋሪዎቹ ለኢብኮ በሰጡት መረጃ፡፡
ከጭፍጨፋዉ የተረፉ ዜጎች ‹‹ንብረታችንም ወድሞ በየቦታው ተበታትነን በችግር ውስጥ ስለሆን መንግሥት ፈጣን ምላሽ ሊሰጠን ይገባል፤ ለእነዚህ አጥፊ ኃይሎች መሳሪያ እያቀበሉ ያሉት ኀላፊነት የጎደላቸው የክልሉ አመራሮች ናቸው›› ብለዋል፡፡
አጥፊ ኀይሎች ቀድመው ስለተዘጋጁበት ዘርን መሰረት በማድረግና በመምረጥ ነው የጨፈጨፏቸው ብለዋል፡፡ ‹‹ቤት ሙሉ ንብረት ወድሞ፤ ቤተሰቦቼ ሁሉ አልቀው እኔ ብቻዬን ቀርቻለሁ›› ብላለች የቡለን ወረዳ ነዋሪ፡፡
የዞኑም ሆነ የክልሉ ባለሥልጣናት ለብዙ ዓመታት እጃቸዉን አስገብተው የንፁኃንን ሕይወት እየቀጠፉ በመሆኑ የፌዴራሉ መንግሥት ጣልቃ መግባት እንዳለበት አስተያየታቸዉን ሰጥተዋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሐሰን የሸፈቱ ኀይሎች ከመከላከያና ከጸጥታ ኀይሎች ጋር በተለያዩ ቀበሌዎች ውጊያ መግጠማቸውን ተናግረዋል፡፡
የደረሰው ግድያ ማንኛዉንም ኢትዮጵያዊና ሰው የሆነ ሁሉ ሊያወግዘው የሚገባ ነው ብለዋል፡፡ የጸረ ሠላም ኀይሎች ተልዕኮ ውስብስብ ስለሆነና አካባቢው የመንገድና የኔትዎርክ ችግር ስላለበት እንዲሁም እነዚህ አካላት ሕዝብ ውስጥ የራሳቸዉን መረብ የዘረጉ በመሆኑ ሁኔታዉን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ እንዳደረገው ተናግረዋል፡፡
ከባለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ እጃቸው ያለበት የክልሉ ኀላፊዎችም ሆነ ግለሰበች ላይ እርምጃ መወሰዱን አቶ አሻድሊ አስታውሰዋል፡፡ ከትናንት በስትያ በተፈጸመው ጭፍጨፋ ስድስት የክልሉ ከፍተኛ ኀላፊዎች እጃቸው እንዳለበት ማስረጃ በማግኘታችን በቁጥጥር ሥር አዉለናቸዋል ብለዋል፡፡
በአካባቢው ሠላም እስኪወርድ ድረስ በጸረ ሠላም ኃይሎች ላይ የሚወሰደው ርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያስረዱት አቶ አሻድሊ ሐሰን ጠቅላይ ሚንስትሩ ያስቀመጡት አቅጣጫ የሚተገበር ከሆነ ዘላቂ ሠላም ይመጣል ብለዋል፡፡
በብሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ