ከመተከል ዞን ዘር ተኮር ጥቃትና ጭፍጨፋ ጋር ተያይዞ እጃቸው እንዳለበት የተጠረጠሩ ተጨማሪ አመራሮች በቁጥጥር ሥር ዋሉ።

393
ከመተከል ዞን ዘር ተኮር ጥቃትና ጭፍጨፋ ጋር ተያይዞ እጃቸው እንዳለበት የተጠረጠሩ ተጨማሪ አመራሮች በቁጥጥር ሥር ዋሉ።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ዘር ተኮር ጥቃትና ጭፍጨፋ ጋር ተያይዞ እጃቸው እንዳለበት የተጠረጠሩ ሁለት አመራሮች እና አንድ የፖሊስ አባል ዛሬ በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡
ትናንት አምስት ከፍተኛ አመራሮች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውም ተመልክቷል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አቶ መለሰ በየነ ለኢዜአ እንደገለጹት ዛሬ በቁጥጥር ሥር ከዋሉት መካከል የክልሉ ግዥ እና ንብረት ማስወገድ ኤጀንሲ ዳይሬክተር አቶ ገመቹ አመንቴ ይገኙበታል፡፡
አቶ ገመቹ የቀድሞ የግልገልበለስ ከተማ ከንቲባ የነበሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሌሎቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት የክልሉ ገጠር መንገድ እና ትራንስፖርት ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ አድማሱ ሞርካ እና አንድ የክልሉ ጸረ-ሽምቅ ፖሊስ አባል መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
የክልሉ መንግስት የዞኑን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በቁርጠኛነት እየሠራ ነው ያሉት አቶ መለሰ፤ በዞኑ ለተፈጠረው ችግር እጃቸው አለበት ተብለው የተጠረጠሩ አምስት ከፍተኛ አመራሮች ትናንት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም አመልክተዋል፡፡
በዞኑ በቡለን ወረዳ በኩጂ ቀበሌ በንጹሃን ላይ ጥቃት የፈጸሙ 42 ሽፍቶች መደምሰሳቸውን ጠቁመው፤ በርካታ የጦር መሣሪያዎች እና ቀስቶች በቁጥጥር ስር እንደዋሉም ጠቅሰዋል፡፡
የአማራ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ህዝቦች አንድ እንደሆኑ የገለጹት ኀላፊው፤ ክልሉ ከአማራ ክልል ጋር በመቀናጀት የጸጥታ ችግሩን ለመፍታት ሲያደረግ የቆየውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጠል አስታውቀዋል፡፡
የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ከአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ጋር በበለጠ ተቀራርቦ ለመስራት መነጋገር እንደሚጀምሩ ጠቁመዋል፡፡
ህብረተሰቡ አካባቢውን ወደ ቀደመ ሠላሙ ለመመለስ የተጀመሩ ጥረቶችን በመደገፍ እገዛውን እንዲያጠናክር አቶ መለሰ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“በኢትዮጵያ የስራ ምቹነትና ቅልጥፍናን ለመፍጠር ተቋማት በቅንጅት መስራት ይጠበቅባቸዋል” የንግድና ኢንደስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል
Next articleየቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አመራሮች እጃቸዉን አስገብተው ንፁኃን እንዲጨፈጨፉ እያደረጉ በመሆኑ የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡