
“በኢትዮጵያ የስራ ምቹነትና ቅልጥፍናን ለመፍጠር ተቋማት በቅንጅት መስራት ይጠበቅባቸዋል” የንግድና ኢንደስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 15/2013 ዓ.ም (አብመድ) የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የሚመራው የንግድ ስራ ቅልጥፋና ማሻሻያ ሥራ ያለበትን ደረጃ የሚመለከት ውይይት ተካሂዷል።
አገልግሎት ፈላጊዎች፣ ነጋዴዎችና አልሚዎች ባሉበት ቦታ ሆነው አልያም በአንድ መስኮት የተቀላጠፈ አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ ለማድረግ እየተሰራ ነው መሆኑ ተመልክቷል።
“በኢትዮጵያ የስራ ምቹነትና ቅልጥፍናን ለመፍጠር ተቋማት በቅንጅት መስራት ይጠበቅባቸዋል” ብለዋል የንግድና ኢንደስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል፡፡
ተቋማቱ ግልፅ የመረጃ ልውውጥና መናብበ ማድረግ እንደሚገባቸውም ሚኒስትሩ ገልፀዋል።
የብሄራዊ ኮሚቴው አካል የሆነው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የንግድ ስራ ለመጀመር የሚያስችል መረጃዎችን የያዘ የንግድ መረጃ አቀባይ business.gov.et አልምቶ ይፋ ማድረጉን ገለጿል።
መረጃ አቀባዩ ወደ ንግድ ስርዓቱ ውስጥ ለመግባት የሚፈልጉ ዜጎች ባሉበት ቦታ ሆነው የተሟላ መረጃ ለማግኘት የሚያስችላቸው ነው ተብሏል። ንግድ ለመጀመርና ፍቃድ ለማውጣት የሚወስደው ጊዜ፣ የሚፈጀው ገንዘብ፣ መሟላት ያላባቸው መረጃዎች እና የመሳሰሉትን የያዘ መሆኑን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመላክታል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አህመዲን መሀመድ (ዶ.ር) የንግድ ማኅበረሰቡና የመንግሥት ሠራተኞች ትክክለኛ የመረጃ መለዋወጫ እንዲኖር እየተሰራ ነው ብለዋል።
የንግድ ስራ ቅልጥፍና ለመፍጠር ለተቋማቸው ተለይተው የተሰጡ ስራዎችም በታቀደው መሰረት እየተከናወኑ ስለመሆናቸው አብራርተዋል።
ባለፈው ዓመት በወጣ ሪፖርት ኢትዮጵያ በንግድ ስራ ቅልጥፍና ከዓለም ሀገራት 159ኛ ደረጃ ላይ ስትሆን በሚቀጥሉት ዓመታት ይህንን ለማስተካከል እየተሠራ መሆኑ ተገልጿል፡፡