በአማራ ሕዝብ ላይ እየተፈፀመ ያለውን የማያባራ የዘር ፍጅት መላው ኢትዮጵያውያን እንዲያወግዙ አብን ጠይቋል።

518
በአማራ ሕዝብ ላይ እየተፈፀመ ያለውን የማያባራ የዘር ፍጅት መላው ኢትዮጵያውያን እንዲያወግዙ አብን ጠይቋል።
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት በዜጎች ላይ ለሚፈፀመው ጭፍጨፋ ቀዳሚ ተጠያቂ እንደሆነም አብን አስገንዝቧል።
በመተክል በአማራ ሕዝብ ላይ የቀጠለውን የዘር ፍጅት አስመልክቶ ከአብን የተሰጠው መግለጫ ቀጥሎ ይቀርባል።
“የአማራ ሕዝብና ሀገራችን ከገጠሟቸው ፈተናዎች ለመውጣት ዘላቂው መፍትኼ ሁሉንም ሕዝብና አካላት ባለቤት የሚያደርግ፣ አገራዊ መከራንም በጋራ መቀልበስ የሚያስችል ሥርዓትና ሥሪት ማቆም መሆኑን ሳናሰልስ ተናግረናል፣ አስገንዝበናል፣ ወትውተናል።
የፍትኅና እኩልነት ሥርዓት ስለማቆም ሳያሰልሱ መወትወትና መታገሉ በመሰረታዊነት አንዳችም ስህተት የሌለበት ቢሆንም ሀገራዊ ፕሮጀክቱ አማራውን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ከሚሰሩ የጥላቻ ኃይሎች ጋር በመሆን ማሳካት እንደማይቻል ግለፅ እየሆነ የመጣ እውነታ ሆኗል።
ሁሉንአቀፍ በጎ ውጥኖች በተግባር እስኪተረጎሙና የጥፋት ኃይሎችም ልቦና ገዝተው በባለቤትነት ስሜት ጭምር የየራሳቸውን አዎንታዊ አበርክቶ መወጣት ሊጀምሩ ይችላሉ ከሚለው እሳቤ በፊት የሕዝባችን ኅልውና የሚቀድም መሆኑን በመረዳት አሳዳጅና ገዳዮቻችን ክላሽ፣ ሜንጫና ቀስታቸውን ጥለው እስኪመጡ ድረስ ለሽግግር የሚሆን የተቀናጀ እርምጃ እንዲወሰድ ዛሬም ለማሳሰብ እንወዳለን።
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የመላው አማራ ሕዝብ ወኪል መሆኑን ማረጋገጥ ያለበት ወቅት መሆኑን በመረዳት በትሕነግ ላይ የወሰደውን ዓይነት ኅልውናን የማስከበር ታሪካዊ ቁርጥ ውሳኔ በማሳለፍ በመተክል እየተፈፀመ ያለውን የዘር ፍጅት ለማስቆም ተግባራዊ ምላሽ ሊሰጥ ይገባል። በዚህ ረገድ አብን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ለማድረግ ያለንን ቁርጠኝነትም መግለጽ እንወዳለን።
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት በዜጎቻችን ላይ ለሚፈፀመው ጭፍጨፋ ቀዳሚ ተጠያቂ ከመሆኑም በላይ በጭፍጨፋው የተሳተፉና በቸልታ የታለፉ ከክልል እስከ ቀበሌ የሚገኙ አመራሮችን በቸልታ በማለፍ የጥቃቱ ተባባሪ ሆኖ ይገኛል።
የፌደራል መንግስትም ኦሮሚያንና ቤንሻንጉልን ጨምሮ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈፀመውን ሰፊ የዘር ማጥፋት ወንጀል ማስቆም ካለመቻሉም በላይ ወንጀሉን በስሙ ባለመጥራት በዜጎቻችን ላይ ለሚፈፀመው ጅምላ ፍጅት ተባባሪ በመሆኑ ከተጠያቂነት እያመልጥም።
በአማራ ሕዝብ ላይ እየተፈፀመ ያለውን የማያባራ የዘር ፍጅት መላው ኢትዮጵያውያን እንድታወግዙና የአማራ ሕዝብ ኅልውናውን ለማስቀጠል ከሚያደርገው ትግል ጎን እንድትቆሙም ንቅናቄያችን በአክብሮት ይጠይቃል።
ንቅናቄያችን በመተከል በአማራ ወገኖቻችን ላይ የሚፈፀመውን የማያባራ የዘር ፍጅት በጽኑ እያወገዘ፤ ለዘር ፍጅት ሰለባ ቤተሰቦችና ለመላው የአማራ ሕዝብም መጽናናትን ይመኛል።”
Previous articleየኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማትን በዘላቂነት መምራት የሚያስችል መሪ ዕቅድ ይፋ ሆነ።
Next article“በኢትዮጵያ የስራ ምቹነትና ቅልጥፍናን ለመፍጠር ተቋማት በቅንጅት መስራት ይጠበቅባቸዋል” የንግድና ኢንደስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል