
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በመተከል ዞን ነዋሪዎችን ባወያዩበት ማግስት ጭፍጨፋ መፈጸሙ ለሰጡት የሥራ መመሪያ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አመራሮች ተገዢ አለመሆናቸውን እንደሚያሳይ ተገለጸ፡፡
በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ ዛሬም ዘርን መሰረት ያደረገ ጭፍጨፋ እንደተፈጸመ ነዋሪዎች ለአብመድ ገልጸዋል፡፡
ድርጊቱ ካሁን ቀደም በተደጋጋሚ የተፈጸመ ቢሆንም አሁንም እየተባበሰ መምጣቱን ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
ጭፍጨፋው ዘር ተኮር በመሆኑ ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች ድርጊቱን በማውገዝ የጋራ ድምጽ ማሰማት እንዳለባቸው የሕግ አማካሪዉ አስረስ ማረ ገልጸዋል፡፡
በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ነዋሪዎችን ባወያዩበት ማግስት እንዲህ ዓይነት ጭፍጨፋ መፈጸሙ ለሰጡት የሥራ መመሪያ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አመራሮች ተገዢ አለመሆናቸውን ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
የቤኔሻንጉል ጉሙዝ አመራሮች በየቀኑ የሰው ሕይወት እየተቀጠፈ ድርጊቱን በማውገዝ የአማራ ክልል መንግስት በሚያወጣው መግለጫ ቃላትን እየሰነጠቁ ሁኔታውን በመግለጽና ኀላፊነት እንደሚወስዱ ቢገልጹም ዘር ተኮር ጭፍጨፋው ቀጥሏል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አመራሮች የዜጎችን ጭፍጨፋ ማስቆም እና የነዋሪዎችን ደኅንነት ማስጠበቅ ስለተሳናቸው የፌዴራል እና የአማራ ክልል መንግሥት ዜጎችን ለመጠበቅ ርምጃ ሊወስዱ ይገባል፤ በሕገ መንግሥትም ሆነ በዓለምአቀፍ ሕጎችና ስምምነቶች በየትኛውም ክልል በዜጎች ጭፍጨፋ ሲፈጽም ጣልቃ መግባት አለበት ነው ያሉት፡፡
አቶ አስረስ የፌዴራል መንግሥት ከዚህ በፊት የመከላከለያ ሰራዊት ኀይል በአካባቢው በማሰማራት እና በኮማንዶ ፖስት ቀጣናው እንዲመራ ማድረጉ ተገቢ ቢሆንም ድርጊቱን የሚመጥን ኀይል አስመራቶ ችግሩን ባለመቆጣጠሩ ዜጎች ተጨፍጭፈዋል፤ ለዚህም የፌዴራል መንግሥት ኀላፊነት መውሰድ አለበት ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል መንግሥትም ዜጎቹ በዘግናኝ ሁኔታ ህይወታቸው እየተቀጠፈ የራሱን ኀይል በማሰማራት ዜጎችን መታደግ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ የአማራ ክልለ መንግሥት በጉዳዩ ላይ ኀይል እንዳያስገባ የሚከለከል ሕግ እንደሌለም አስገንዝበዋል፡፡
ጭፍጨፋው በዚህ ከቀጠለ በቀጣይ በሀገር ሊደርስ የሚችለውን ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ ሊታሰብበት ይገባል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው