
“የአማራ ልዩ ኃይል ጠላቱን በጦር ወዳጁን በፍቅር አሸንፏል”
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 14/2013 ዓ.ም (አብመድ) አማራን የማይወደው ሀገር የማይወድና ፈሪ ነው። ከፈሪ ጥይት የአማራ ትግስት ያስፋራል። የአማራ ትግስት ጠላቶቹን ያስጨንቃል። አስቀድሞ ይሰብራል። ከትግስት በኋላ ምን ሊያስከትል እንደሚችል ያውቁታልና ይፈሩታል። አማራ ሲገጥሙት ይመታቸዋል፣ ሲሞግቱት ይረታቸዋል። አማራ ስለ ኢትዮጵያ ይዋደቃል፣ በኢትዮጵያ ይምላል፣ ለኢትዮጵያ ይኖራል፣ ኢትዮጵያን ያስቀድማል፣ ከኢትዮጵያ መነካት በፊት ራሱን ይሰጣል፣ ኢትዮጵያ ለአማራ የልቡ ውቅር፣ መንቀሳቀሸው የደሙ ስር፣ የማታረጅ ልዩ ክብር፣ የማይለውጣት ልዩ ሚስጥር ናት።
ኢትዮጵያን ያለው ሁሉ የአማራ ወዳጅ ነው። ኢትዮጵያን ዝቅ ለማድረግ ለሚጥረው ደግሞ የአማራ ቁጣ ይገነፍላል። እንደ ነዲድ ይፋጃል፣ እንደ አንበሳ ይጎማጃል፣ አማራ ሳያስታውል አይነሳም። ከተነሳ ሳያሸንፍ አይቀመጥም። ለውሸት ዘብ አይቆምም፣ ለጣለት እጅ አይሰጥም፣ ሕይወቱና ሞቱ ከእውነት ጋር ብቻ ነው። አማራ በአንዲት ሀገሬ አትምጡብኝ፣ በሰፋች ሀገር ውስጥ ጠብቤ እንድኖር አትፍረዱብኝ ባለ የጥፋት እጆች ሁሉ ተዘርግተውበት ኖሯል፤ ለዚህም ዋጋ ከፍሏል። ደሙን አፍስሰው ያሳነስነው ሲመስላቸው በደሜ አጠነከራችሁኝ እንጂ አላሰነሳችሁኝም ይላቸዋል፣ ሰበርነው ሲሉት ይሰብራቸዋል፣ አማራ ፈጣሪውን ፈሪ፣ ለባልንጀራው መልካም መካሪ፣ ታናሽ ታላቁን አክባሪ፣ ታሪክ ሰሪ ሕዝብ ነው።
የአማራን ዘር ለማጥፋት፣ አንገቱን ለማስደፋት፣ መልካም ስሙን ለማክፋት ረጅም ርቀት ከሄዱት መካከል ትህነግ ግንባር ቀደሙ ነው። ትህነግ የአማራን ሕዝብ ቢችል ለማጥፋት፣ ባይችል ግን አንገቱን ለማስደፋት ያልሄደው ያላደረገው የለም። ትህንግ እርስቱን በመውሰድ፣ ማንነቱን በመንጠቅ፤ አማራን በማሳደድ፣ በመግደልና በማሰር የግፍ ግፍ ፈፅሞበታል።
የትህነግ የክፋት ልክ በአማራና በሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ ያደረገው ግፍ አልበቃ ቢለው የኢትዮጵያን የቁርጥ ቀን ልጅ ደፈረ። በዚሕ ብቻ አላበቃም የአማራን ክልልም ለመቆጣጠር ሙከራ አደረገ። ዳሩ ለሀቅ የሚኖር፣ ለጠላቱ የማይበገር፣ ግንባሩ የማይሰበር ጀግና ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ነበርና የእብሪተኛውን የትህነግ ታጣቂ ከድንበር መልሶ፣ አመድ አልብሶ መለሰው። ራሱን በመከላከልና በማጥቃት የመከላካያ ሠራዊቱንም ከከፍተኛ ጥፋት ታድጓል። የአማራ ልዩ ኀልና ሚሊሻ በሕግ ማስከበሩ ዘመቻ በትህነግ የግፍ አገዛዝ ሥር የነበሩ አካባቢዎችን ነፃ በማውጣት ታላቅ ጀብዱ ፈፅሟል። የሚወዱት ኮርተውበታል፣ በጀግንነቱ ተደስተውበታል፡፡
ሰሞኑን በራያ ግንባር ድል አድርጎ በወፍላ ከሚገኘው የአማራ ልዩ ኀይል ጋር የመገናኘት እድሉን አግኝቼ ነበር። ልዩ ኃይሉ የተደራጄ የጠላትን ጦር፣ ከአስቸጋሪ የተፈጥሮ አቀማመጥ ጋር ነው እየደማሰሰ ድል ያደረገው። ሕግ እያስከበረ የሚገኜው የአማራ ልዩ ኃይል ጠላቱን በጦር ወዳጁን በፍቅር አሸንፏል። በወፍላ ወረዳ ውስጥ ፋላ በምትባል ቀበሌ ውስጥ ተገኝቻለሁ። የአማራ ልዩ ኃይል አካባቢውን ተቆጣጥሮ የሕዝቡን ሰላም እያስጠበቀ ነው። አካባቢው አስቸጋሪ ቢሆንም ልዩ ኃይሉ ግን በከፍተኛ ወኔ ግዳጁን በብቃት እየተወጣ ነው።
የወፍላ ተራራዎችን እያሰሰ የሕዝብ ዘብ መሆኑን እያሳየ ነው። ልዩ ኃይሉ ጠላቱን በጦር እንዳሸነፈ የተቆጣጠረው ቦታ፣ የማረከውና የደመሰሰው ጠላት ምስክሮች ናቸው። ወዳጁን በፍቅር ስለማሸነፉም በፋላ በተገኜሁበት ጊዜ ተመለከትኩ።
ሀዳስ ዓለመ ይባላሉ። ነዋሪነታቻው ፋላ ቀበሌ ውስጥ ነው። 78ኛ ዓመት እድሜያቸው ላይ ናቸው። የሚያሳዝኑ ኢትዮጵያዊት እናት ናቸው። እማማ ሀዳስ ሶስት ልጆች ወልደው አንድም ልጅ ከእሳቸው ጋር የለም። ሁሉንም በሞት አጥተው የወላድ መካን ሆነው ነው የሚኖሩት። ሰው በተራበችና የድህነት ጥላዋን ባጣለባት ቤት ውስጥ ነው የሚኖሩት። በዚህ እድላቸውም ለረጅም ጊዜ ፈጣሪያቸውን ሲያማርሩ እንደኖሩ ነግረውኛል። እማማ ሀዳስ በሚኖሩባት የፋላ ትንሽዬ መንደር አቅራቢያ የሽንብራ ማሳ አለቻቸው። የህግ ማስከበሩ ሥራ ወደ ፋላ ትንሽዬ መንደር እየተቃረበ ሲሄድ ከፍዬልና ከበግ እየጠበቁ ዓይን ዓይን የሚያዩዋት ሽንብራቸው ከጥቅም ውጭ እንደምትሆን ያስፈራሯቸው ነበር። እሳቸውም የሚሆነውን ሁሉ በትግስት እየተጠባበቁ ዝም አሉ።
ውጊያው ገፍቶ ፋላ መያዟ እውን እየሆነ ሲሄድ እማማ ሀዳስ ይልቀቁ ተባሉ፣ እሳቸው ግን “ግድ የለም ይምጡ ልጆቼ ናቸው እናታቸው ነኝ ምንም አያደርጉኝም” ነበር መልሳቸው። እርሳቸው አስቀድመው እንደተማመኑበት የአማራ ልዩ ኃይል ልጃቸው እርሳቸውም እናቱ ነበሩና ንፁሃንን እየተንከባከበ ጠላቱን እየነጠለ እያጠቃ አካባቢውን ተቆጣጠረው። የተፈራው ቀረ። ጠላትን እንጂ ወዳጅን የማይነካ ሠራዊት ሆኖ አገኙት።
ትህነግ ፈረጠጠች። በአካባቢው ሌላ ጊዜ መጥቶ እማማ ሀዳስ የሽንብራ ማሳቸውን ከእረኛ አልባ ፍዬልና በግ እየጠበቁ ይውላሉ። የአማራ ልዩ ኃይል ከእማማ ሀዳስ ማሳ በላይ ሰፍሯል። የደጋ ውርጭ ሳይበግረው አካባቢውን እየጠበቀ የሚገኜውን ጀግና ልዩ ኃይል ምን ምን ቢያደርጉለት ደስታቸውን እንደሚገልፅላቸው ሲያንሰላስሉ ሰንብተዋል። እንደሌላው ኢትዮጵያዊ በግ፣ ፍዬልና በሬ ወይንም ሌላ ከፍ ያለ ስጦታ መስጠት አይችሉም። ቤታቸው ባዶ ነው። ቤታቸው ውስጥ ያለው ሳይኖረው ጭምር መስጠት የሚሻ ንፁህ የእናትነት ሩህሩህ አንጄትና ልብ ነው። ወደስፍራው ሄደን ሳለ የ78 አመቷ እማማ ሀዳስ ከማሳቸው የሽንበራ እሸት ነቅለው ዳገቱን እየቧጠጡ መጥተው “እንኩ ልጆቼ እሸት ቅመሱ” ብለው ሰጧቸው።
የእሳቸው ደግነት እና ልዩ ኃይሉ በአካበቢው ምን ያህል እንደሚዋደዱ ስመለከት ገረመኝ እና በፎቶ ማንሻዬ ምስላቸውን አስቀረሁ። ልባቸው ውስጥ ያለውን ፍቅርና አክበሮት ይነግሩኝ ዘንድ ጠየኳቸው። “አይ ልጄ ደስ ስላለኝ አምጥቼ ሰጠኋቸው፣ እነሱ ከመግባታቸው በፊት እንቅልፍ አጥተን ነበር። ገና በ12:00 ሰዓት ግቡ እየተባለ ዱላ ነው። እነሱ ከመጡ ወዲህማ ሁሉ ነገር ሰላም ነው” አሉኝ። የትህነግ ታጣቂ አካባቢውን ለቅቆ ሊወጣ ሲል በፋላ ትንሽዬ መንደር የዱላ ውርጅብኝ ያወርድ እንደነበር እማማ ሀዳስ ነግረውኛል። ጠያቂም አልነበረም የተገኜሁ ሁሉ ይደበደብ ነበር ነው ያሉኝ።
እማማ ሀዳስ ስለ አማራ ልዩ ኃይል ሲናገሩ “ከመጡ ይረግጧችኋል፣ ይዘርፏችኋል ይገርፏችኋል ይባሉ ነበር። ከመጡ ወዲህ ግን የተባለው ነገር ቀርቶ ሰላማቸን የሚጠብቁ ናቸው” ነው ያሉኝ። የአማራ ልዩ ኃይል አካባቢውን ከመቆጣጠሩ በፊት ሽንብራቸውን ሳይቀር እንደማያገኟት ተነግሯቸው የነበሩት እማማ ሀዳስ የአማራ ልዩ ኃይል ከመጣ ወዲህ ከጠዋት እስከ ማታ እረኛ ከሌለው በግና ፍዬል ይጠብቋት የነበረችው ሽንብራ ለልዩ ኃይሉ አደራ ብለው እንደሚሄዱ ነው የተናገሩት።
“እነዚህ ወታደቶች ከሽንብራው አንድ እግር ለእሸት አልነቀሉም፣ እሸት ነው ብለው በእጃቸው ነቅለው አልቀመሱም” ነው ያሉት። የልዩ ኃይሉ ሕግ አክባሪነትና ሰው ወዳድነት እማማ ሀዳስን አስደንቋቸዋል። “ክብሩ ይስፋ በሰላም ተኛሁ፣ ደስ ስላለኝና ስለወደድኳቸው ነው ከፊታችሁ ድረስ የመጣሁት እንጂ ባልወዳቸውማ አልመጣም ነበር። ያቅሜን ይዤ ስለመጣሁ ደስ አለኝ። አደራ ልጆቼ በዚሁ ባሕሪያችሁ ቀጥሉ። ለሀገታችሁ መከታ ሁኑ” ነው ያሏቸው። የእማማ ሀዳስ የእናትነት ፍቅር፣ የልዩ ኃይሉ የሰው መውደድ አስደነቀኝ።
በስፍራው የሚገኜው የልዩ ኃይልም ሽንበራው ሲደርስ እንደሚሸክፍላቸው ቃል ሲገባላቸው ሰምቻለሁ። እውነተኛ ስትሆን የእውነት ወዳጆች ሁሉ ይወዱሃል። እውነተኛ ስትሆን ትልልቅ የውሸት ተራሮችን በቀላሉ ትንዳቸዋለህ። መገፋት፣ እውነትና ጀግንነትን የያዘው የአማራ ልዩ ኃይል ጠላቱን በጦር ወዳጁን በፍቅር አሸንፎ ታሪክ ሰርቷል። ለካስ ስጦታ ብዙ ገንዘብ አይደለም ቅን ልብና ለመስጠት የተዘጋጄ እጅ እንጂ።
የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ስንት እናቶች በሰላም እንዲተኙ እንዳደረጉ አሰብኩ። ኢትዮጵያ እንደ እማማ ሀዳስ ናት። ሰላምን የምትገልግ፣ መከፋፈልን የምትጠላ፣ በልጆቿ መልካም ሥራ ደስ የምትሰኝ። የእማማ ሀዳስ እና የሌሎች ኢትዮጵያውያን እናቶች ፀሎት ኢትዮጵያውያን ከምንም ነገር ሊጠብቃት እንደሚችል ተሰማኝ። አመንኩም። በእናት ውስጥ ማዘን አለ። በእናት ውስጥ መውደድ አለ። በእናት ውስጥ መልካም ምኞትና ተስፋ አለ። በድህነት ውስጥ የሚኖሩት እማማ ሀዳስ በቅንነትና በመስጠት የተመላ መልካም የእናትነት ልብ አላቸው።
ኢትዮጵያዊ መሆን ያኮራል። እማማ ሀዳስ በአሻገር ያለውን የመማፀኛ ደብር በእጃቸው እየጠቆሙ “ጠዋትና ማታ እየሄድኩ ተመስገን እያልኩት ነው። ሰላም እንዲመጣ እየተማፀንኩት ነው” ብለውኛል። ደግሞም የዋህ ልብ ልመናቸውን ሰምቶ ያሉት ሁሉ በኢትዮጵያ ይፈፀማል። የኢትዮጵያውያን እናቶች ሁሉ ክፉ አይንካቸው፣ የመከፋት የእንባ ዘለላ በዓይናቸው አይፍሰስ። ሰላም ለኢትዮጵያ።
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ