
ማኅበረሰቡ የተሟላ አገልግሎት እንዲያገኝ እየተሰራ መሆኑን የዋጃና ጥሙጋ ጊዜያዊ አስተዳደር አስታወቀ።
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 13/2013 ዓ.ም (አብመድ) በዋጃና ጥሙጋ የሚያሰጋ የሰላም ችግር አለመኖሩንም ጊዜያዊ አስተዳደሩ አስታውቋል።
የዋጃና ጥሙጋ አካባቢ በትህነግ የግፍ አገዛዝ ሲተዳደር ቆይቷል።
ትህነግ በመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በመፈፀሙ በተወሰደው የህግ ማስከበር ሥራ በመከላከያ ሠራዊት፣ በአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ አባላት ትህነግ ተመትቶ ከአካባቢው ከወጣ ቆይቷል። የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደርም ሥራውን እያከናወነ ነው።
የዋጃና ጥሙጋ ጊዜያዊ አስተዳደር ያሬድ አድማሴ ማኅበረሰቡ ጊዜያዊ አስተዳደሩን የመረጠው የአካባቢውን ሰላምና ፀጥታ እንዲጠብቅለት ነው ብለዋል። ከሰላምና ፀጥታው ጎን ለጎን የፈረሱ የልማት ተቋማት ካሉ እና ሌሎች ጥያቄዎችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ለመመለስና ለማስተካከል መሆኑንም ተናግረዋል። በአካባቢው አሁን ላይ የሚያሰጋ ነገር እንደሌለ የተናገሩት አቶ ያሬድ አንዳንድ አሉባልታዎችን እየሰሙ የሚሸበሩ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ ፤ ነገር ግን አካባቢው ሰላሙ የተረጋገጠ ነው ብለዋል።
በአካባቢው ትህነግ ሲፈጽመው የነበረውን መድሎና ግፍ ለማስተካከል እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል። ጊዜያዊ አስተዳደሩ ማኅበረሰቡ የተሟላ አገልግሎት እንዲያገኝ እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
የአገልግሎት ተቋማት በተሟላ ሁኔታ እንዲከፈቱ ማኅበረሰቡ ጥያቄ ማንሳቱን የተናገሩት ጊዜያዊ አስተዳደሩ በትህነግ ዘመን ሲፈጸምበት የነበረው ፍትሐዊ ያልሆነ አስተዳደር እንዳይደገምም ጠይቋል ብለዋል ።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሠራተኞች ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ እንዳደረገና የደሞዝ ክፍያም እንዲፈፀም እያደረገ መሆኑን ነው የተናገሩት።
ማኅበረሰቡ የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ ከፀጥታ ኀይሉ ጋር በጋራ እንዲሰራም ጊዜያዊ አስተዳደሩ ያሬድ አድማሴ አሳስበዋል። የሚነሱ ጥያቄዎች በቶሎ ምላሽ እንዲያገኙም ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ሕብረተሰቡ ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል። አብመድ በሥፍራው ተገኝቶ እንደተመለከተውም ማኅበረሰቡ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴው ተመልሷል። በተገኜው ሰላምና ነፃነትም ደስተኛ ነው።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ ከዋጃ ጥሙጋ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ