የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ልደትን በላልይበላ፣ ጥምቀትን በጎንደር ለማክበር መዘጋጀቱን አስታወቀ።

252
የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ልደትን በላልይበላ፣ ጥምቀትን በጎንደር ለማክበር መዘጋጀቱን አስታወቀ።
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 11/2013 ዓ.ም (አብመድ) የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት እና የጥምቀት በዓላት በድምቀት ለማክበር ዝግጅቱን ማጠናቀቁን የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል። በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በየዓመቱ ታኅሣሥ 29 የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል (ገና) በኢትዮጵያ በልዩ ልዩ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ሥርዓቶች ይከበራል። በተለይ በላልይበላ ዓለማቀፍ ገጽታን ተላብሶ በተለየ መልኩ ደምቆ ይከበራል።
ታኅሣሥ 29 የቅዱሱ ንጉሥ ላልይበላ ልደት ታስቦ የሚውልበት በመሆኑ ከሃይማኖታዊና ባህላዊነቱ ባለፈ ታሪካዊ ይዘትን ያላብሰዋል። በዚህም ከሌሎቹ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በተለየ መልኩ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት ጎብኝዎች ላልይበላ ተገኝተው በድምቀት ያከብሩታል። ከዚህ በፊት በነበሩት የበዓሉ አከባበርም በርካታ የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ለመከታተልና ለማክበር ወደ ሥፍራው በማቅናት የበዓሉን ባህላዊና ሃይማኖታዊ ትውፊት ከላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ድንቅ የጥበብ ሥራ ጋር አስተሳስረው በአድናቆት ታድመዋል።
በተመሳሳይ በሃይማኖቱ ተከታዮች በየዓመቱ ጥር 11 የኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊቱን ጠብቆ በመላ ኢትዮጵያ ይከበራል። በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገበው ይህ ሃይማኖታዊ በዓል በተለይ በታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ የሀገር ውስጥና የውጪ ሀገራት ጎብኚዎችና የሃይማኖቱ ተከታዮች በተገኙበት በተለየ ገጽታ ደምቆ እንደሚከበር ይታወቃል።
የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ሁለቱንም በዓላት በድምቀት ለማክበር በቂ ዝግጅት ማድረጉን የክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊ ሙሉቀን አዳነ (ዶክተር) አስታውቀዋል። የኮሮናቫይረስ በፈጠረው ጫና ምክንያት የቱሪዝም እንቅስቃሴው ተዳክሞ እንደነበር ይታወሳል። በቅርቡ ወረርሽኙን በመከላከል የቱሪዝም እንቅስቃሴውን ዳግም ለማስጀመር ሀገር አቀፍ የቱሪዝም ፕሮቶኮል ተዘጋጅቶ የማስጀመሪያ መርሀግብር ተካሂዷል።
በአማራ ክልልም በላልይበላ፣ በጎንደር፣ በስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ እና በጭስ ዓባይ ፏፏቴ የፌዴራልና የክልል የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት የማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል። ሆኖም አሸባሪው ትህነግ ሀገር የማፍረስ ዓላማ አንግቦ በፈጸመው ጥቃት ምክንያት የታሰበውን ማሳካት አልተቻለም። በዚህ ወቅትም መንግሥት በወሰደው ሕግ የማስከበር ዘመቻ ጉዳዩ እልባት አግኝቷል። የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ሙሉቀን እንዳሉትም የቱሪዝም እንቅስቃሴውን ለማነቃቃት የተጀመረው ሥራ እንዲጠናከር እየተከናወነ ነው።
የልደትና የጥምቀት በዓላትም የክልሉን የቱሪዝም እንቅስቃሴ በጥሩ መንፈስ ለማነቃቃት ምቹ አጋጣሚዎች ናቸው ብለዋል። አጋጣሚዎቹን በመጠቀምና የኮሮናቫይረስን በመከላከል በዓላቱ በድምቀት እንደሚከበሩም አመላክተዋል። ለዚህም የክልሉ መንግሥት ዝግጅት ማድረጉን ነው ዶክተር ሙሉቀን ያስታወቁት።
ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበአማራ ክልል በ1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር 14 የንፁህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች ሊገነቡ ነው፡፡
Next articleበአማራ ክልል የ8ተኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና እየተሰጠ ነው ፡፡