በአማራ ክልል በ1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር 14 የንፁህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች ሊገነቡ ነው፡፡
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 11/2013 ዓ.ም (አብመድ) በመጭዎቹ ሦስት ዓመታት በክልሉ ዝናብ አጠር እና ደረቃማ አካባቢዎች የንፁህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች እደሚገነቡ ነው የተገለፀው፡፡ በአማራ ክልል መካከለኛ ከተሞች እና የገጠር ቀበሌዎች ያለውን የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ለማሳደግ ያስችላል የተባለለት ይህ ፕሮጀክት በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ በሰሜን ወሎ፣ ማዕካላዊ ጎንደር፣ ደቡብ
ወሎ እና ሰሜን ሽዋ ዞኖች እንደሚገነባም ታውቋል፡፡
የዚሁ ፕሮጀክት አካል የሆኑት በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አስ ከተማ እና በሰሜን ወሎ ዞን ሰኞ ገበያ የሚገነቡት የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ግንባታ የፊርማ ሥነ ሥርዓት ተከናውኗል፡፡
የግንባታ ውሉ የፊርማ ሥነ ሥርዓትም በፕሮጀክቱ አስፈፃሚ የአማራ ክልል ውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ቢሮ እና በሚገነባው የጢስ እሳት ኮንስትራክሽን ድርጅት መካከል ተካሂዷል፡፡
14ቱ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች በአየር ንብረት አይበገሬነት የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ፕሮግራም የሚከናወኑ ናቸው ያሉት የአማራ ክልል ውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ቢሮ ኀላፊ ማማሩ አያሌው (ዶክተር) ግንባታቸው በመጨዎቹ ሦስት ዓመታት ይጠናቀቃል ብለዋል፡፡
የንፁህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶቹን ገንብቶ ለማጠናቀቅ 1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር መመደቡንም የቢሮዉ ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡ በፕሮጀክቱ ግንባታ የፊርማ ሥነ ሥርዓት ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተፈጥሮ ሃብት ውኃ መስኖና ኢነርጂ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ክብርት ፈትያ የሱፍ፣ የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሽ በቀለ እና የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ፋንታ ማንደፍሮ (ዶክተር) ተገኝተዋል፡፡ለፕሮጀክቶቹ ተፈፃሚነት የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የውኃ ልማት ኮሚሽን እና የአማራ ክልል ውኃ መስኖና ኢነርጂ ቢሮ በጋራ እንደሚሰሩም ዶክተር ኢንጂነር ስለሽ በቀለ ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ