
ለርብ መስኖ ግድብ ፕሮጀክት አፈፃፀም መዘግየት የተቋራጭ ድርጅቱ የመፈፀም አቅም ዝቅተኛ መሆኑ ተገለፀ፡፡ ግንባታው እዲፋጠንም በአዲስ ተቋራጭ እዲገነባ እርክክብ እየተካሄደ ነው ተብሏል፡፡
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 11/2013 ዓ.ም (አብመድ) ባለፉት 10 ዓመታት በአማራ ክልል ምርት እና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ያስችላሉ የተባሉ ስድስት የመስኖ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክቶች ተጀምረው ነበር፡፡ ከነዚህ ታላላቅ የመስኖ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የሆነው የርብ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክት የበረካታ የአካካቢውን አርሶ አደሮች ህይዎት ይለውጣል ተብሎ ቢጠበቅም ግንባታው ግን በተያዘለት ጊዜ መጠናቀቅ አልቻለም፡፡
የርብ መስኖ ግድብ ፕሮጀክትን ፍፃሜ ከዛሬ ነገ በጉጉት ከሚጠብቁት የፎገራ ወረዳ ርብ አካባቢ ነዋሪዎች መካከል አቶ አለባቸው ጎበዜ አንዱ ናቸው፡፡ ‹‹የግድቡ ውኃ ወደማሳችን ባለመድረሱ በመስኖ ውኃ እጥረት ምክንያት ለእርስ በዕርስ ግጭት ሳይቀር ተዳርገናል” ብለዋል፡፡ ግድቡ ተጠናቆ አገልግሎት ይሰጣል ከተባለለት ጊዜ በላይ ለዓመታት እንደተጓተተም በምሬት ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል ውኃ መስኖና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ማማሩ አያሌው (ዶክተር) የርብ መስኖ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ውኃ መያዝ እዲችል ግድቡ ከተሰራ ሁለት ዓመታት እንዳስቆጠረ ተናግረው የማፋሰሻ ካናሎቹ ግንባታ በመዘግየቱ አገልግሎት ላይ እንዳይውል አድርጎታል ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በተባለለት ጊዜ አለመጠናቀቅ ከፈጠረው ምጣኔ ሃብታዊ ተፅዕኖ ባሻገር የመልካም አስተዳደር እና ማህበራዊ ቅራኔዎችን እየፈጠረ መሆኑን ነው ቢሮ ኃላፊው ያብራሩት፡፡ የተቋራጩ የመፈፀም አቅም ውስንነት በመኖሩ በአዲስ የመተካት ሥራው ተጠናቅቆ እርክክብ እየተፈፀመ ነው፡፡
ፕሮጀክቱ በተያዘው ዓመት ተጠናቆ ለሁለተኛ ዙር የመስኖ ሥራ እንዲደርስ እየተሠራ ሲሆን ከዚህ ቀደም የነበረው የተናጠል አካሄድ ቀርቶ ከፌደራል እስከ ቀበሌ በጋራ እና በትብብር እየተሠራ ነው ብለዋል የቢሮ ኀላፊው፡፡
ከሰሞኑ የርብ መስኖ ግድብ ፕሮጀክትን የአፈፃፀም ሁኔታ በመስክ ወርዶ የተመለከተው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተፈጥሮ ሃብት ውኃ መስኖና ኢነርጂ ቋሚ ኮሚቴም ከህዝቡ እና ከአስፈፃሚው አካል ጋር ምክክር አድርጓል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ክብርት ፈትያ የሱፍ በሀገር ደረጃ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ውስንነት መኖሩን ጠቅሰው ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የተቀናጀ አካሄድ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በክልሉ ያሉ የፌደራል መስኖ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን የገለፁት ክብርት ፈትያ የሱፍ የርብ መስኖ ግድብ ፕሮጀክት ግን ችግሮቹ ውስብስብ በመሆናቸው የቅርብ ክትትል እና ድጋፍ ያስፈልገዋል ነው ያሉት፡፡
የርብ መስኖ ግድብ ፕሮጀክት በ2002 ዓ.ም ተጀመሮ እስካሁን ያለው አፈፃፀምም 69 በመቶ አካባቢ ብቻ ነው፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ