“ልዩ ድጋፍ የሚሹና ያልለሙ አካባቢዎችን በተሻለ መልኩ መለወጥ የሚያስችል የሦስት ዓመት ዕቅድ ይዘጋጃል” አቶ ደመቀ መኮንን

262
“ልዩ ድጋፍ የሚሹና ያልለሙ አካባቢዎችን በተሻለ መልኩ መለወጥ የሚያስችል የሦስት ዓመት ዕቅድ ይዘጋጃል” አቶ ደመቀ መኮንን
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 10/2013 ዓ.ም (አብመድ) የአቅምና የልማት ክፍተት በሚታይባቸውና ልዩ ድጋፍ በሚሹ አካባቢዎች የተሻለ ልማት ለማምጣት የሦስት ዓመት ዕቅድ የሚዘጋጅ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።
የፌዴራል ልዩ ድጋፍ ቦርድ አባላት የቦርዱን የ2011/12 ዓ.ም እቅድ አፈጻጸምና የ2013 ዓ.ም እቅድ ላይ ውይይት አድርገዋል።
በሰላም ሚኒስቴር አዘጋጅነት በተካሄደው በዚሁ ውይይት ላይ የእቅድ አፈጻጸሙን ያቀረቡት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ስዩም መስፍን “ቦርዱ በአሥር ዓመታት ቆይታው በርካታ ሥራዎችን አከናውኗል” ብለዋል።
ይሁን እንጂ ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ካሉበት ነባራዊ ሁኔታ አንጻር የሚጠበቀውን ያህል ለውጥ ሊያመጡ የሚያስችሉ ተግባራት እንዳልተከናወኑ አንስተዋል።
በተለይ ልዩ ድጋፍ በሚሹ ክልሎችና አርብቶ አደር አካባቢዎች ተከስተው የነበሩ የጸጥታ ችግሮች የእቅዱን አፈጻጸም እንዳጓተቱት ተናግረዋል።
በእነዚህ አካባቢዎች ያሉ አጎራባች ክልሎችም ቢሆኑ በጎንዮሽ ትስስር አስፈላጊውን እገዛ በማድረግ ረገድ ውስንነት እንደነበረባቸው ነው ሚኒስትር ዴኤታው የገለጹት።
“የክፍተቶቹ ድምር ውጤት ደግሞ በግብርና ዘርፍ፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በሲቪል ሰርቪስና መንገድን በመሳሰሉ መሠረተ ልማቶች የሚጠበቀው ውጤት እንዳይመዘገብ አድርጓል” ሲሉ አብራርተዋል።
የፌዴራል ልዩ ድጋፍ ቦርድ ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎችን በተሻለ መልኩ ለመለወጥ የሦስት ዓመት እቅድ እንደሚዘጋጅ ጠቁመዋል።
ኢዜአ እንደዘገበው የእቅድ ዝግጅቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ከመጪው ጥር ጀምሮ ወደ ትግበራ እንደሚገባ ነው የገለጹት።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየገቢዎች ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት ጣና ሐይቅን ለመታደግ 13 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረጉ፡፡
Next articleየአማራ ክልል ህዝቦች ሰማህታት መታሰቢያ ሐውልት ጽሕፈት ቤትየክልሉን ባህልና እሴት በጠበቀ መልኩ በአዲስ መልክ እየተደራጀ መሆኑን የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ገለጸ።