“የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ ተሽከርካሪ ችግር ለጎንደር እንደ ዓለምአቀፍ መዳረሻነቷ ለታሪኳ የማይመጥን፣ ለዝናዋና ለክብሯ የማይገባ ነው” አስተያየታቸውን የሰጡ የከተማው ነዋሪዎች

321
“የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ ተሽከርካሪ ችግር ለጎንደር እንደ ዓለምአቀፍ መዳረሻነቷ ለታሪኳ የማይመጥን፣ ለዝናዋና ለክብሯ የማይገባ ነው” አስተያየታቸውን የሰጡ የከተማው ነዋሪዎች
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 10/2013 ዓ.ም (አብመድ) ጎንደር ከ200 ዓመታት በላይ የኢትዮጵያ መናገሻ ሆና ያገለገለች ጥንታዊና ታሪካዊ ከተማ ነች። በሰው ሰራሽ ቅርሶቿ፣ በታሪኳና በማኅበረሰባዊ ትውፊቶቿ ጎልታ ትታወቃለች። የበርካታ ጎብኝዎች መዳረሻ ከሆኑ የኢትዮጵያ አካባቢዎች መካከል በአስደናቂ የኪነጥበብ ሥራቸውና በጉልህ ታሪካዊ ድርሻቸው የጎብኚዎችን ቀልብ በሚስቡ ቅርሶቿ ቀዳሚ ናት፡፡
ለአብነት የአፄ ፋሲለደስ ቤተ መንግሥትን በርካታ ቅርሶችን፣ ተነግረው የማያልቁና ታይተው የማይጠገቡ ታሪካዊ ቅርሶችን፣ ዓለም እምብዛም ባልሠለጠነበት ዘመን የነበረውን የኢትዮጵያን ሥልጣኔ ፍንትው አድርገው የሚያሳዩ የኪነጥበብ ውጤቶችን አቅፎ የያዘ ነው። እስከ 400 ዓመታት ገደማ ያስቆጠሩ ጥንታዊ ግብረ ህንጻና ሌሎችም እድሜ ጠገብ ቅርሶች ይገኙበታል፡፡ የአፄ ፋሲል፣ የአፄ ዮሐንስ፣ የታላቁ አዲያም ሰገድ እያሱ፣ የአፄ ዳዊት፣ የንጉሥ መሲ ሰገድ በካፋና የእቴጌ ምንትዋብ አብያተ መንግሥታት የሚገኙትም በዚሁ ቅጥር ግቢ ነው።
እነዚህ ታሪካዊና እድሜ ጠገብ አብያተ መንግሥታት እያንዳንዱ ነገሥታት አሻራቸውን ለትውልድ ትተው ያለፉባቸው ቅርሶች ናቸው፡፡ ሌሎች እንደ ቤተ መዛግብት፣ መዋኛ ገንዳ፣ ቁስቋም ማርያም፣ ደረስጌ ማርያምን እና ሌሎች ታሪካዊ ቅርሶችን ያቀፈው ይህ ግቢ በተባበሩት መንግስታት የትምሕርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል።
ስለጎንደር ታሪክ፣ ቅርስና ዝና በጥቂቱም ቢሆን ለማስታዎስ ካልሆነ በቀር በቀላሉ አውርቶ መጨረስ አይታሰብም፡፡ በዚች አጭር ጽሑፍ በምናብ የኋሊት ተጉዞ ታሪክን በቀላሉ ማስታወስ ከቶውንም ቢሆን አይቻልም። 18 ቋሚ ቅርሶችን ጨምሮ ወደ 96 የሚጎበኙ ልዩልዩ ቅርሶች የሚገኙባት ጎንደር የጥምቀት በዓል በዓለም ከማይዳሰሱ ቅርሶ ዝርዝር ውስጥ መካተቱም ለጎንደት ቱሪዝም ተጨማሪ እድል ፈጥሯል።
ጎንደር በኢትዮጵያ ከፍተኛ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ካለባቸው ቦታዎች መካከል በቀዳሚነት በትጠቀስም አሁናዊ አቋሟ ግን “ለታሪኳ የማይመጥን፣ ለዝናዋም የማይስተካከል፣ ለክብሯም የማይገባ ነው” ይላሉ አብመድ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች። በዚህም ከቱሪዝሙ ማግኘት የሚቻለውን ገቢ በተሸለ ደረጃ ማግኘት እንዳልተቻለ ያነሳሉ፡፡ ቱሪዝም በኢኮኖሚው ውስጥ የጎላ አስተዋጽኦ እንዲኖረው አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ማልማት፣ ነባር መዳረሻዎች ተጨማሪ እሴት እንዲያስገኙ ማድረግ፣ የቱሪዝም ትውውቅን ማሳደግ፣ ፈጣንና ጥራት ያለው የቱሪዝም አገልግሎት መስጠት እንዲሁም የውጪ ሀገራትንና የሀገር ውስጥ ጎብኝዎችን ቁጥር በማሳደግ የቆይታ ጊዜያቸውን ማራዘም ያስፈልጋል፡፡
በተለይ የጎብኝዎችን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም የጉብኝት ቦታዎችን ማስዋብና ምቾት ያለው የአገልግሎት አሠጣጥን ማሳደግ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ ይሕንን ማድረግ ባለመቻሉ ባላት የቱሪዝም ሀብት ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ሳታገኝ በርካታ ዓመታት አልፈዋል፡፡
የከተማዋ ነዋሪ አቶ አንጋው ልጃለም ጎንደር የታሪካዊ ቅርሶች መገኛ ብትሆንም የከተማዋ ነባራዊ ሁኔታ እምቅ ሀብቷን አሟጥጦ መጠቀም የሚያስችል እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ ጎብኝዎች ከአውሮፕላን ማረፊያ ወጥተው በታክሲ ሲጓዙ አስፓልቱ ምቹ አይደለም፤ የከተማዋ የጽዳት ሁኔታም እንደ አንድ ዓለም አቀፍ የቱሪዝም መዳረሻ አይመጥናትም፤ ሆቴሎች በውሃ እጥረት ምክንያት ተገቢውን አገልግሎት መስጠት ተስኗቸዋል፤ የከተማ አስተዳደሩ ባሕል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያም ችግሩ የጎላ መሆኑን ያነሳል፡፡
የመምሪያው ምክትል ኀላፊ ማሩ ሙሐመድ እንዳሉት ቅርሶችን እና የቅርሶችን መገኛ አካባቢ በተቻለ መጠን ጽዱና ማራኪ ለማድረግ በባሕላዊ መንገድም ቢሆን ተሠርተል፡፡ የከተማዋ የጽዳት ሁኔታ ግን ሊታሰብበት ይገባል ብለዋል፡፡ በተለይ የፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገዱ ከፍተኛ ችግር ያለበት መሆኑ በተደጋጋሚ ይነሳል፡፡ በዚህም ነዋሪዎችና አገልግሎት ሰጪ ተቀማት ፍሳሽ ቆሻሻ ለማስወገድ ተቸግረዋል፡፡
በከተማ አስተዳደሩ አገልግሎት እሰጠ ያለው አንድ የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ ተሽከርካሪ ብቻ ነው፡፡ ይሕ ከ750 ሺህ በላይ ለሚገመት የጎንደር ሕዝብ ፈጽሞ ሊበቃ አይችልም፡፡ በዚህ ምክንያት የሕዝቡን ፍላጎት ማመላት እንዳልተቻለ ነው የከተማ አስተዳደሩ ውሃና ፍሳሽ ያስታወቀው፡፡ ችግሩን ለማስተካከል በተያዘው በጀት ዓመት አንድ የስፋሽ ቆሻሻ ማስወገጃ ተሽከርካሪ ለመግዛት መታቀዱን የአገልግሎቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አየልኝ መሳፍንት አስታውቀዋል፡፡
ዓለም ባንክ የጽዳት መርሃግብርም ተጨማሪ ሁለት ተሽከርካሪዎችን ለመግዛት ቃል መግባቱን አመላክተዋል፡፡ ይሕም ችግሩን በተወሰነ መልኩ ይቀንሰዋል ብለዋል፡፡ በዘላቂነት ችግሩን ለመፍታት በዓለም ባንክ አማካኝነት የተያዘ ፕሮጀክት መኖሩንም አስታውቀዋል፡፡ ለዚህም ጥናት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡ ለጊዜው ማሕበረሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ በተቻለ መጠን ጽዳቷን ለመጠበቅ እንደሚሠራ ተመላክቷል፡፡ ይሕ ከሆነ ደግሞ ጎንደር ከተማ ለስሟ የሚመጥን፣ ለክብሯም የሚበቃ ጽዳት ይኖራታል፡፡ በቀጣይ 10 ዓመታት የቱሪዝም ዘርፉ ዋንኛ የኦኮኖሚ ምንጭ እንዲሆን ከተፈለገ ከግለሰብ እስከ ድርጅት የነቃ ተሳትፎ ሊኖረው ይገባል፤ ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ያለው የመንግሥት መዋቅርም መሪ እቅዱን ሊያሳካ የሚችል አሠራር መተግበር እንደሚገባው ነው አስተያየታቸውን የሰጡ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች የተናገሩት፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ለሁለት ቀናት ሲያካሂድ የቆየዉን መደበኛ ስብሰባ አጠናቀቀ፡፡
Next articleየገቢዎች ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት ጣና ሐይቅን ለመታደግ 13 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረጉ፡፡