“የህወሓት ጁንታ ያልዋለበትን ገድል ለትውልድ ሲሰብክ ኖሯል” ሜጀር ጄኔራል ሹማ አብደታ

844
“የህወሓት ጁንታ ያልዋለበትን ገድል ለትውልድ ሲሰብክ ኖሯል” ሜጀር ጄኔራል ሹማ አብደታ
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 09/2013 ዓ.ም (አብመድ)
የህወሓት ጁንታ በስልጣን በነበረበት ዘመን በሀገራችን ህዝብ ላይ ያልፈጸመው ግፍና መከራ የለም ማለት ይቻላል። በተለይ ኢትዮጵያዊያንን በዘረኝነት ድንበር ለያይቶ የሀገር ፍቅርን አመለካከትና አስተሳሰብ የተዛባ እንዲሆን አድርጓል።
በሀገር መከላከያ ሠራዊት የልዩ ዘመቻዎች ኃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ሹማ አብደታ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ አድርገዋል፡፡
በብላቴ የሚገኘው የልዩ ዘመቻዎች ኃይል ማሠልጠኛ ማዕከል ለ33ኛ ዙር በመሠረታዊ ኮማንዶ ያሰለጠናቸውን የሪፐብሊካን ጋርድ አባላት ሰሞኑን ባስመረቀበት ወቅት በስፍራው በመገኘት የስራ መመሪያም አስተላልፈዋል።
ሜጀር ጄኔራል ሹማ አብደታ እንዳሉት የጁንታው ቡድን የሶስት ሺህ ዘመን ታሪክ ያላትን ታላቋን ኢትዮጵያን በመቶ ዓመት ታሪክ ብቻ በመገደብ ታሪኳን ሲያጠላሽ ቆይቷል።
አዲሱ ትውልድም ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን የአያት ቅድመ አያቶቹን ወርቃማ የኢትዮጵያዊ አልበገር ባይነት ገድሎችን እንዳያውቅ ለማድረግ ሲሰራ ቆይቷል።
“በተለይ ‘ተራራውን ያንቀጠቀጠ ትውልድ’ እያለ ያልዋለበትን ሜዳ ትርክት ልብወለድ ለትውልድ ሲሰብክ ኖሯል” ይላሉ።
እንኳንስ ኢትዮጵያዊ፣ ኢትዮጵያዊ ያልሆነ ዜጋ ለማወቅ የሚጓጓውን ተዝቆ የማያልቀውን የሀገራችንን ታሪክ ትውልድ እንዳያውቀው በማድረግ የኢትዮጵያዊነት ስሜትን ለመግደል ያደረገው ከንቱ ጥረት ባይሳካለትም ጁንታው ብዙ ዋትቷል ብለዋል።
ከዚህም ባሻገር የሀገርን ሀብት ዘርፏል፣ በዜጎቻችን ላይ ኢ-ሰብዓዊ ተግባርን ፈፅሟል።ብሄርን ከብሄር፣ሐይማኖትን ከሐይማኖት በማጋጨት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አገሪቱ እንዳትረጋጋ በማድረግ ብዙ መስራቱን ለአብነት ጠቅሰዋል።
በሠራዊቱ ውሰጥ እርስ በርስ መተማመን እንዳይኖር ማድረግ ብቻ ሳይሆን ጓደኛውን በተኛበት እንዲገድል እስከ ማድረስ የደረሰ አሳፋሪ ተግባር መፈጸሙን ነው ሜጀር ጄኔራሉ የሚናገሩት።
ሰላማዊና ወዳጅ መስሎ እራት ለመጋበዝ ጠርቶ እጅ ላይ ካቴና በማስገባት የሰራዊቱን አባላት በግፍ ማሰቃየቱንና መረሸኑን በቁጭት ያወሳሉ።
የጁንታው ስውር የባርነት ቀንበር ያማረራቸው የሀገራችን ህዝቦች በተባበረ ክንዳቸው ከሥልጣን አሸቀንጥረው ቢጥሉትም በህዝቦች ስም እየማለና እየተገዘተ ህዝቡን አሰቃይቷል።
ይህ የምድራችን እርጉም ቡድን መቀሌ ውሰጥ በትግራዋይ ጉያ ውሰጥ ተሸሽጎ ሌላ በዘር የተለወሰ የባርነት ቀንበርን በትግራይ ህዝብ ላይ በመጫን በሴይጣናዊ ስውር እጁ የሀገሪቱን ህዝቦች ደም መምጠጡን አላቆመም ሲሉ ይገልጹታል ጁንታውን።
“መንግሥት ሁኔታዎችን ሁሉ እያወቀ የአንድም ዜጋ ህይወት ያለ አግባብ እንዳይጠፋና ለሀገር ሰላም ካለው ቀናዒ አመለካከት በመነሳት ሁሉንም ነገር በሰላም ለመፍታት ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል” ይላሉ።
ሆኖም ገና ከበረሃ ጀምሮ እጁ በህዝብ ልጆች ደም የጨቀየው ይህ ቡድን ከአረሜኔያዊ ድርጊቱ ሊታቀብ አልቻለም።
በተለይ በስውር መንገድ ሀገሪቱን በማዳከም እጅና እግሯን አስሮ ለታሪካዊ ጠላቶቿ አሳልፎ ለመስጠትና ሀገሪቱን ለመበታተን በቀቢፀ ተስፋ መታተሩን እንደቀጠለበት አዛዡ አመላክተዋል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየባህርዳር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኮሚቴ የባህርዳር ከተማ ኤርፖርት ስያሜ እንዲቀየር ወሰነ።
Next article‹‹ወንጀል ፈጽመው ወደጎረቤት ሀገራት የሸሹ የጁንታው አባላት የሰላም ጠንቅ እንዳይሆኑ ከፍተኛ ሥራ መሠራት አለበት›› ወይዘሮ ያየሽ ተስፋሁነኝ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብቸኛዋ የትግራይ ክልል ተወካይ