
የጎንደርን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማነቃቃት የአገልግሎት ክፍያ ቅናሽ ለማድረግ እየተሠራ ነው።
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 08/2013 ዓ.ም (አብመድ) የጎንደር ከተማን የቱሪዝም እንቅስቃሴ መልሶ ለማነቃቃትና የሀገር ውስጥ ጎብኝዎችን ለማበረታታት የአገልግሎት ክፍያን ለመቀነስ እየተሠራ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ባሕል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ አስታወቀ።
ከ18 በላይ ቋሚ ቅርሶችን ጨምሮ 96 ልዩ ልዩ ቅርሶች የሚገኙባት ጎንደር ከተማ ከፍተኛ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ካለባቸው ስመጥር የኢትዮጵያ አካባቢዎች አንዷ ናት፡፡
በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በዘርፉ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማስተናገድ ቀዳሚ ልትሆን እንደምትችልም ከተማ አስተዳደሩ አመላክቷል፡፡
ሕይወታቸውን በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ያደረጉ የቱሪዝም ማኅበራት፣ ምግብ አብሳዮች፣ አስጎብኝዎች፣ የባህል ምሽት ቤቶች፣ የእደጥበብ ማኅበራትና ሌሎች አገልግሎት የሚሰጡ አካላት ከፍተኛ ጫና ውስጥ ገብተዋል፡፡
በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ አካላት የደረሰባቸውን ጫና እንዲቋቋሙ በመንግሥት በኩል ውጤታማ ሥራ አለመሠራቱን የከተማ አስተዳደሩ የባሕል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ የቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ አይቸው አዲሱ ተናግረዋል።
ለ16 ሆቴሎች ግን ወደ 12 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በአምስት በመቶ የወለድ ክፍያ የረጅም ጊዜ ብድር እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረዋል። ይህም ያለምንም ገቢ እስከመዘጋት የደረሱ ሆቴሎች ሠራተኞቻቸውን ይዘው እንዲቆዩ በማድረግ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል ነው ያሉት፡፡
በዘርፉ የተሠማሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የገጠማቸውን የኢኮኖሚ ችግር ለማካካስ የሚወሰዱ አማራጮችን በተመለከተ የክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ጠይቀናል፡፡ ቢሮው በዘርፉ ለሚሰሩ አካላት አማራጭ የሥራ ንድፈ ሀሳብ እንዲያዘጋጁ መጠየቁን የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ሙሉቀን አዳነ ተናግረዋል፡፡
ዶክተር ሙሉቀን እንዳሉት ንድፈ ሀሳቡ ከተዘጋጀ በኋላ ባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከዓለም አቀፍ ረጂ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያመቻች ጥያቄ ቀርቦ ነበር፡፡ ነገር ግን የኮሮናቫይረስ ባደረሰው ኢኮኖሚያዊ ጫና ምክንያት የታሰበው አልተሳካም ብለዋል፡፡ የክልሉ መንግሥት ብድር እንዲያመቻች ጥያቄ መቅረቡን አመላክተዋል፡፡
ክልሉ ጉዳቱን በአግባቡ እንደተረዳው ያስታወቁት ዶክተር ሙሉቀን በቀጣይም የካቢኔ አባላት ውሳኔ እንደሚጠበቅ አመላክተዋል፡፡
በ2012 በጀት ዓመት የኮሮናቫይረስ መከሰቱ እስከታወቀበት መጋቢት ወር ድረስ ከቱሪዝሙ ወደ 6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ተገኝቶ ነበር፡፡ ባለፈው ዓመት ዕቅድ መሠረት እንኳን በ2013 በጀት ዓመት የመጀመሪያ አራት ወራት እስከ 3 ሚሊዮን ብር የቱሪዝም ገቢ መገኘት ነበረበት፡፡ የጎብኝዎች ቁጥርም ሆነ ከቱሪዝም የተገኘው ገቢ በጣም ዝቅተኛ መሆኑ ከመምሪያው የተገኘ መረጃ ያመላክታል።
አቶ አይቸው እንዳሉት የውጪ ጎብኝዎች በ98 በመቶ ቀንሷል። 111 የውጪና 12 ሺህ 665 የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች ጎንደርን የጎበኙ ሲሆን ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም 50 በመቶ ገደማ ቅናሽ አለው። የተገኘው ገቢም 136 ሺህ 303 ብር ብቻ ነው፡፡
ኮሮናቫይረስ ባስከተለው ጫና ምክንያት ክፉኛ ከተጎዱ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መካከል የጎንደር ሂልስ ሪዞርት ይጠቀሳል። ሪዞርቱ በብዛት የሚያስተናግደው የውጪ ሀገራት ጎብኝዎችን ነበር። ለ130 ሰዎችም ቋሚ የሥራ ዕድል ፈጥሯል። የውጪ ጎብኝዎች ሙሉ ለሙሉ በማቆማቸው ምክንያት ሪዞርቱ ለሥድስት ወራት ያለምንም ገቢ ተዘግቶ ቆይቷል። ምንም እንኳን ገቢ ባያገኝም ከሠራተኞች ጋር ተስማምቶ የደመወዝ ቅናሽ በማድረግ ሠራተኞችን ሳይበትን አቆይቷል። በዚህ ጊዜ ሙሉ ደመወዛቸውን እየከፈለ መሆኑን የሪዞርቱ ሥራ አስኪያጅ ሰያር ያሲን ተናግረዋል።
በቅርቡ የኢትዮጵያ የቱሪዝም መዳረሻዎች ለጉብኝት ክፍት እንዲሆኑ መወሰኑ ይታወሳል። ይህንን ተከትሎ ጎንደር ሂልስ ሆቴል የሀገር ውስጥ ጎብኝዎችን የሚያበረታታ አማራጭ አገልግሎት ለማስጀመር መታሰቡንም አስታውቀዋል። የአገልግሎት ክፍያን መቀነሱንም ነው የተናገሩት።
ከተማ አስተዳደሩ በተለይ የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማበረታታት የአገልግሎት ክፍያን ለመቀነስ አስቧል፡፡ የጉብኝት ክፍያን በግማሽ ከመቀነስ ጀምሮ ሁሉም የቱሪዝም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የዋጋ ቅናሽ እንዲያደርጉ የማስገንዘብ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አቶ አይቸው አስታውቀዋል።
የጎንደር የቱሪዝም እንቅስቃሴ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ባዘጋጀው የኮሮናቫይረስ መከላከያ ፕሮቶኮል መሠረት ዳግም ሥራው ተጀምሯል፡፡ በከተማዋ ለሚገኙ ለሁሉም መዳረሻዎች የጸረ ተሕዋሲያን ርጭት ተደርጓል፡፡ ወረርሽኙን በመከላከል ቱሪዝሙን ማስቀጠል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከቱሪዝም ባለድርሻ አካላት ግንዛቤ መፈጠሩንም ተናግረዋል። በወቅታዊ ችግር ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የአየር ትራንስፖርት መጀመሩ ይታወሳል። ይህም ቱሪዝሙ እንዲነቃቃ አስተዋዕጾ ይኖረዋል ተብሎ ይገመታል።
ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ