
የጥረት ኮርፖሬት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አምላኩ አስረስ በሥራ አመራር አፈጻጸማቸው የክብር ፕሮፌሰር ማዕረግ ተሰጣቸው፡፡
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 08/2013 ዓ.ም (አብመድ) መቀመጫውን እንግሊዘ ሀገር ኦክስፎርድ ያደረገው የአውሮፓ የንግድ ጉባዔ (Europe Business Assembly (EBA)) የተባለ ተቋም ለጥረት ኮርፖሬት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አምላኩ አስረስ ዘውዴ የክብር የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሰጣቸው፡፡
በሥራ አመራራቸው የምጣኔ ሀብታዊና ማኅበራዊ ዕድገት ለማምጣት፣ በማስተማርና ምርምር ዘርፍ ውጤታማ የተቋም ስነ አመራርን በመተግበር ተቋሞቻቸውን ወደ ከፍታ በማድረስ ለተመረጡ በሚሰጠው “የሶቅራጠስ ሽልማት” ለዶክተር አምላኩ አስረስ ዘውዴ የክብር ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ተሰጥቷቸዋል፡፡
ዶክተር አምላኩ አስረስ ቀደም ሲል በመሯቸው የአማራ መልሶ መቋቋም ድርጅትንና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ላይ አመርቂ ውጤት
ያስመዘገቡ ሲሆን የባንክ ኢንደስትሪን ጨምሮ በልዩ ልዩ ተቋማት የሥራ አመራር ቦርድ ዳይሬክተር በመሆን እስካሁን ድረስ እያገለገሉ ያሉና በተቋማቱ ዕድገት ላይ አሻራቸውን በማሳረፍ ላይ የሚገኙ መሪ ናቸው፡፡
ዶክተር አምላኩ አስረስ የከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በእርሻ ኢኮኖሚክስ ከመጀመሪያ እስከ ሶስተኛ ድግሪያቸውን በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ተከታትለዋል፡፡
የግብርና ባለሙያ ሆነው በሰሩበት የወጣትነት ዘመናቸው “ታታሪና መልካም ስነምግባር ያለው ኤክስፐርት ናቸው” ሲሉ የሥራ ባልደረቦቻቸው ይመሰክራሉ ፡፡
እ.አ.አ ከ ግንቦት ወር 2018 ጀምሮ 19 ኩባንያና 10 ፕሮጀክቶችን ከ 11 ሺህ በላይ ሰራተኞች ጋር ለሚያስተዳድረውና በችግር ውስጥ ተዘፍቆ የቆየውን ጥረት ኮርፖሬትን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት እንዲመሩም ተሰይመዋል፡፡
በቆይታቸውም ተቋሙን ከችግሩ አላቅቆ የተሻለ ተቋም ለማድረግ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡
ለዶክተር አምላኩ አስረስ የተሰጣቸው ሽልማት በሳይንስ ፣ በባህል እና በትምህርት መስኮች ዕድገትን ለማምጣት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ላበረከቱ ሰዎች የሚሰጥ የእውቅና እና የምስጋና ሽልማት መሆኑን ከጥረት ኮርፖሬት የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ