የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ የተሰነዘረበትን ጥቃት በመመከት ሕግ በማስከበር ዘመቻው ከፍተኛ ሚና እንደነበረው በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ግንባታ ማዕከል ሚኒስትር ዛዲግ አብርሃ አስታወቁ።

1010
የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ የተሰነዘረበትን ጥቃት በመመከት ሕግ በማስከበር ዘመቻው ከፍተኛ ሚና እንደነበረው በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ግንባታ ማዕከል ሚኒስትር ዛዲግ አብርሃ አስታወቁ።
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 07/2013 ዓ.ም (አብመድ) አቶ ዛዲግ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከአሐዱ ቴሌቭዥን ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በቆይታቸውም በተለይ በሕግና ሥርዓት ማስከበር ዘመቻው፣ ስለ አማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ አባላት፣ ስለወሰንና የማንነት ጉዳዮች እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
አቶ ዛዲግ በትግራይ በተከናወነው የሕግና ሥርዓት ማስከበር ዘመቻ መንግሥት ሁሉንም አካባቢዎች በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታውቀዋል። የቀረው ተግባር የፖሊሥ ሥራ መሆኑን በማመላከትም መያዣ የወጣባቸውን ተጠርጣሪዎች በሕግ ቁጥጥር ሥር ለማዋል እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
አሸባሪው ትህነግ በከፈተው ጦርነት ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው የነበሩ ወገኖችን ማቋቋምና የጁንታው ቡድን ያወደማቸውን መሠረተ ልማቶች መልሶ መገንባትና መጠገን በፍጥነት የሚከናወን ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።
ወራሪውና ተስፋፊው የትህነግ ቡድን በትግራይ ሕዝብ ጉያ እንደመዥገር ተጣብቆ በተለይ የማንነት ጥያቄ ይነሳባቸው በነበሩ አካባቢዎች ሰብዓዊ ፍጡር ሊፈጽመው የማይገባ አሰቃቂና ዘግናኝ ግፍ ሲፈጽም ቆይቷል ብለዋል። ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱና የሕግ የበላይነት አደጋ ላይ ወድቆ መቆየቱንም ነው አቶ ዛዲግ የገለፁት።
በሕግና ሥርዓት የማስከበር ዘመቻው ንጹኃን የጥቃት ሰለባ እንዳይሆኑ መንግሥት ከፍተኛ ጥንቃቄ ቢያደርግም የጥፋት ቡድኑ ግን የዘር ማጥፋት ሲፈጽም እንደነበር አብራርተዋል፡፡ በርካታ የጅምላ መቃብር መገኘታቸውንም በማሳያነት ጠቅሰዋል።
ዘመቻውን በአጭር ጊዜ በጥሩ ውጤት ማጠናቀቅ እንደተቻለ አመላክተዋል። በተለይ የአማራ ክልል ልዩ ኃይልና ሚሊሻ የተሰነዘረባቸውን ጥቃት በመመከት መከላከያ ሰራዊትን ከጥቃት መታደጋቸውን አስታውቀዋል።
አቶ ዛዲግ የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ የተዋጉት ርስት ለማስመለስ ነው በሚል የሚነዛውን የተሳሳተ ሀሳብም አጣጥለዋል። “የአማራ ልዩ ኃይል ራሱን ነው የተከላከለው” በማለትም የማንነት ጥያቄው ከ30 ዓመታት በላይ ሲጠየቅ እንደነበር አመላክተዋል።
የራያና የወልቃይት ሕዝብ የማንነት ጥያቄውን በሕጋዊ መንገድ ሲያቀርብ እንደነበርም ተናግረዋል። ካሁን ቀደም በነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ ህዝቦች ኑሯቸው ሲኦል ነበር በማለት ገልጸውታል። ከዚህ ጋር በተያያዘ በተለይ “የራያ ሕዝብ ወደነበርንበት እንመለስ የሚል የዘመናት ትግል ነበረው። እንደግለሰብ እኔንም የሚመለከት ትግል ነው” ብለዋል።
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
Previous articleበጎንደር ከተማ የጥምቀትን በዓል ሃይማኖታዊ ትውፊቱንና ባህሉን ጠብቆ ለማክበር ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡
Next articleየጥረት ኮርፖሬት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አምላኩ አስረስ በሥራ አመራር አፈጻጸማቸው የክብር ፕሮፌሰር ማዕረግ ተሰጣቸው፡፡