
መንግሥት በዘር ማጥፋት ወንጀል የተሳተፉ ቡድኖችን ለሕግ እንዲያቀርብ በአሜሪካ የኢትዮጵያን የዘር ማጥፋት ወንጀል የሚከታተል ድርጅት ጠየቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 06/2013 ዓ.ም (አብመድ) ባለፉት ዓመታት ዘር ተኮር ፌዴራሊዝምን የሙጥኝ ብሎ የኢትዮጵያን ፖሊቲካ ሲዘወር የነበረው ወራሪው፣ ተስፋፊውና አሸባሪው ትህነግ በሃገሪቱ ዜጎች ኢፍትሐዊነትን አንግሶ ቆይቷል፡፡
የጭቆና ቀንበሩና የፈፀመው ግድያ በተለዬ መልኩ በልዩ ልዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች በሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ላይ እንደነበር በተደጋጋሚ ተነስቷል፡፡ ለዚህ አንዱ ማሳያ አሸባሪው ትህነግ ያራመደው የሃሰት ትርክት ይጠቀሳል፡፡
በምጣኔ ሃብት ተጠቃሚነት፣ በትምሕርት፣ በመሠረተ ልማትና በሌሎችም መስኮች የፈፀመው አድሏዊ አሠራር የአማራ ክልልን ማኅበራዊ፣ ኦኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ክፉኛ ጎድቶት ቆይቷል፡፡
በአሜሪካ በተለያዩ የሥራ መስኮች የተሠማሩ የአማራ ተወላጆች ይህን ችግር በመረዳት ነበር የአማራ ባለሙያዎች ማኅበርን (አምባ) የመሠረቱት፡፡
ከተመሠረተ በኋላም ሀገሪቱ በእኩልነት የምትተዳደርበት ሥርዓት እንዲፈጠር ምሁራዊ አስተያየት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡
የክልሉን ማኅበራዊ ልማት ለመርዳትም ወንፈል የተሰኘ የተራድዖ ድርጅት ተመሥርቶ የተለያዩ ሥራዎችን አከናውኗል፡፡
ባለፉት ሦሥት አስርት ዓመታት በሀገሪቱ ዘርን መሠረት ያደረገ ጅምላ ግድያን አስመልክቶም በኢትዮጵያ የዘርፍጅት ቅድመ መከላከል ድርጅት እንዲመሰረት አድርገዋል፡፡
በሚኒሶታ ዩኒቨርስቲ የባዮሴኪዩሪቲ ተመራማሪ ዶክተር ሰናይት ደረጀ የአምባ ስራ አስፈጻሚና የዘር ፍጅት ቅድመ መከላከል ድርጅቱ ሊቀመንበር ናቸው፡፡
ዶክተር ሰናይት እንዳሉት አንድን ሰው በማንነቱ ምክንያት ብቻ ለማጥፋት ታልሞ የሚሠራ ድርጊት የዘር ማጥፋት ወንጀል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በአማራዎች ላይ የተፈጸሙ አሰቃቂ ጭፍጨፋዎችም የዚህ ማሳያ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ በተለይ ወራሪው፣ ተስፋፊውና አሸባሪው ትሕነግ በሕዝብ ተቃውሞ ተሸንፎ መቀሌ ከመሸገ በኋላ በአማራ ላይ የሚፈጸሙ ግድያዎችንና በቀጥታና በማስተባበር ከእኩይ ዓላማው አስፈፃሚዎች ጋር በመቀናጀት ፈጽሟል፡፡
በምዕራብ ወለጋ፣ በመተከልና በማይካድራና በሌሎችም አካባቢዎች የተፈጸመውን ግድያ በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡
ድርጅታቸው የዘር ማጥፋት ወንጀሉ መቼ እና የት ቦታ እንደተፈጸመ፣ ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰና በማን አማካኝነት እንደተፈጸመ የተሟላ መረጃ ሰብስቧል ብለዋል፡፡
መረጃዎቹን በመተርጎምና በሚፈለገው መልኩ በማደራጀት ለአምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ለዓለም አቀፉ ሰብዓዊ መብት ተሟጋችና ለተለያዩ የፍርድ ቤት ተዋረዶች ማስተላለፉንም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት (አይ ሲ ሲ) ስምምነትን ባትፈርምም እንዳስፈላጊነቱ በተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሀፊ የሚታይበት አግባብ መኖሩን አስታውቀዋል፡፡
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድርጊቱን በጥብቅ እንዲያወግዘውም ጠይቀዋል፡፡
የተሰበሰቡ መረጃዎችን በመሰነድ ወደፊት በጉዳዩ ላይ ለሚሠሩና ክስ ለሚመሠርቱ አካል በቂ ግብዓት እንዲሆን እየተሠራ መሆኑን ዶክተር ሰናይት ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት በሃገሪቱ ባለፉት ጊዜያት በዘር ማጥፋት የተሳተፉ ወንጀሎችን ለፍርድ እንዲያቀርብም እንፈልጋለን ነው ያሉት ዶክተር ሰናይት፡፡
መቀመጫውን አሜሪካ አድርጎ በኢትዮጵያ የሚፈጸሙ የዘር ማጥፋት ወንጀሎችን በትኩረት የሚከታተለው ድርጅቱ ወንጀለኞች ለፍርድ እንዲቀርቡ በትኩረት እንደሚሠራም ገልፀዋል፡፡
በሀገሪቱ ሕግና ሥርዓትን የማስከበር ዘመቻው በአጭር ጊዜ በስኬት መጠናቀቁን አድንቀዋል፡፡
ህግ የማስከበር ርምጃው በጦርነት ጊዜ በንጹኃን ላይ ይደርስ የነበረውን ጉዳት ያስቀረ በመሆኑ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ለአማራ ልዩ ኃልና ሚሊሻ ብሎም ለአፋር ልዩ ኃይል ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት በህግ የማስከበር ስራዉ ቦታው ድረስ በመገኘት ትልቅ ሙያዊ አበርክቶውን በመወጣቱ አድናቆታቸውን ገልፀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ