
የሱር ሴራ፤ ከመቀሌ እስከ አበርገሌ
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 06/2013 ዓ.ም (አብመድ) ትህነግ ባለፈው ግማሽ ምዕተ ዓመት ኢትዮጵያን ለመበተን እና ኢትዮጵያዊነትን የጥርጣሬ ስንጥር ውስጥ ለመቀርቀር ያለሰራው ደባ ያልጎነጎነው ሴራ አልነበረም፡፡ በቤተ እምነት ግጭትን፣ በልማት ተቋማት ሸፍጥን፣ በብሔር ልዩነት ጥላቻን እና በፖለቲካ ርዕዮት ዓለም ሴራን እየፈተለ ከልዩነት በላይ የደመቀ አንድነትን፣ ከራስ በላይ የተገነባ ሃገር ወዳድነትን እና ኢትዮጵያዊ ስሜትን ክፉኛ ቦርቡሮት አልፏል፡፡
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በትግራይ ክልል በሚገኘው የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት የፈፀመው ትህነግ የኢትዮጵያዊያን ስሜት መጎዳት እና አብሮ መቆም ተመልክቶ እንኳን ለስህተቱ ፀፀት ለጥፋቱ እርማት ማድረግ ተሳነው፡፡ ያለፈው አልበቃ ብሎት ከሁመራ እስከ ማይካድራ፤ ከሽሬ እስከ አክሱም፤ ከተከዜ እስከ ዳንሻ በመሰረተ ልማት ላይ ውድመትን በሰብዓዊነት ላይ ጭካኔን እየፈፀመ እስከ ወዲያኛው አለፈ፡፡
አበርገሌ በአማራ ክልል በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ውስጥ ከሚገኙ የትግራይ ክልል አዋሳኝ ወረዳዎች አንዷ ናት፡፡ የጦር ጥበበኞቹ ዋጎች ጦርነትን እስከ ኮተቱ ጠንቅቀው ያውቁታልና ቀድመው ይጠሉታል፡፡ ዋጎች ለጦርነት ቶሎ አይፈሉም ቶሎም አይበርዱም፡፡ ትዕግስት፣ ፍቅር፣ መቻቻል እና የበዛ እምነት ስላላቸው መጠራጠርን ሳይቀር ይታገሱታል፤ ትናንት የሆነውም ይህው ነበር፡፡
ሱር ኮንስትራክሽን ድርጅት ወደአበርገሌ የገባው መሰረተ ልማት ግንባታ የተባለለትን የበግ ለምድ ለብሶ ነበር፡፡ አበርገሌዎች ትናንት ጨፌ በትነውና በግ አርደው የተቀበሉት ሱር ዛሬ ምድራቸውን አኬልዳማ ለማድረግ የሚያስችል ምሽግ ይቆፍራል ብለው እንዴት ይጠርጥሩት? ዳሩ የማይቀረው ባይቀርም ሱር አንድ ወር ሙሉ ዝግጅት የአበርገሌ ወረዳ ዋና ከተማ ኒሯቅም አንድ ወር ሙሉ ጭንቀትን አሳልፈዋል፡፡
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ትህነግ በሰሜን ዕዝ ላይ አሳፋሪ ክህደት ከፈፀመ በኋላ በማግስቱ ሱር አበርገሌ ውስጥ ያሉትን ማሽነሪዎች ወደአዋሳኝ የትግራይ ቀበሌዎች አሸሸ፡፡ የአስፓልት መንገድ ለመገንባት የገባው ድርጅት ድንበር ላይ በግራ እና ቀኝ እስከ ስድስት ኪሎ ሜትር ርዝመት እና እስከ ሁለት ሜትር ጥልቀት ያለው የጦር ምሽግ ወደ መቆፈር ተሸጋገረ፡፡ ሱር ተደራራቢ ምሽጎችን ቆፍሮ እንዳጠናቀቀም ከአበርገሌ ወረዳ ዋና ከተማ ኒሯቅ ቅርብ ርቀት ላይ ዲሽቃ እና ሞርተር ተጠመደ፤ የትግራይ ልዩ ሃይል አባላት እና ሚሊሻዎችም ለጥፋት ወደተቆፈረላቸው ምሽግ ተሰገሰጉ፡፡
ይህ ሁሉ ሲሆን ከፀና እምነታቸው ፈቀቅ ያላሉት አበርገሌዎች ለሚደርሳቸው ወፍ በረር መረጃ ጆሮ ዳባ ልበስ እንዳሉ ነበሩ፡፡ በቤተ ክርስቲያን የሚያገኟቸውን ጎረቤቶቻቸውን ስለሚወራው ወሬ ጠይቀው ምንም እንዳልተፈጠረ ሲነገራቸው አምነው ተቀብለዋል፡፡ ጎረቤቶቻቸው ሃብት እና ንብረታቸውን ጥለው ከቀያቸው ሲሸሹ ከስጋት ያለፈ እውነት መሬት ላይ አለ ብለውም አላመኑም፡፡ ይህ ሁሉ ዝግጅት ሲካሄድ ‹‹የሰናፍጭ ቅንጣት የምታክል ጥርጣሬ እንኳን የላችሁም ነበር?›› ስንል ጥያቄ ያነሳንላቸው የአበርገሌ ነዋሪ የሆኑት እነታምራት አምባው የመለሱልን ምላሽ ሱር መንገድ እየሰራ ከመሆኑ ውጭ ያሉ መረጃዎችን አምነው አልተቀበሉም ነበር፡፡
ትህነግ በሽንፈቱ ማግስት፤ በሽሽቱ ንጋት በማይካድራ እና ሁመራ የፈፀመውን አስነዋሪ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ቢሰሙም ይህ በኒሯቅ ይደገማል ብለው ግን አልጠረጠሩም ነበር፡፡ የመረጃው መደጋገም ፍንጭ የሰጣቸው እና ስጋት የፈጠረባቸው የወረዳዋ የፀጥታ አካላት ጉዳዩን ከአካባቢው ርቆ ህግ በማስከበር ግዳጅ ላይ ላለው የሃገር መከላከያ ሰራዊት አደረሱ፡፡ ‹‹በማይካድራ የተፈፀመው ጭፍጨፋ በኒሯቅ እንዳይደገም በመስጋታችን መረጃውን ለመከላከያ ሰራዊት አደረስን›› ያሉን የአበርገሌ ወረዳ ፖሊስ ጽፈት ቤት ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ሲሳይ ካሴ መከላከያ ሰራዊት በአካባቢው ሲደርስ ግን የሱር ምሽግ በቀላሉ የሚሰበር ሆኖ አልተገኘም ነበር፡፡
ምስጋና ከራሳቸው ህይዎት በላይ ለህዝብ ሰላም እና ደኅንነት ለቆሙት የሃገር መከላከያ ሰራዊት ይሁንና ለወር በሱር ማሽነሪዎች ዝግጅት የተደረገበት ምሽግ በግማሽ ቀን ውጊያ የማይካድራዋ ሙሽራ ኒሯቅ ነፃ ወጣች፡፡ ነዋሪዎቿ ከስጋት ነፃ ሆነው ከጭንቃቸው ተገላግለው በተከዜ በኩል ከእገታ አምልጠው የመጡ የሰራዊቱን አባላት በክብር ተቀብለው ከጉዳታቸው እንዲያገግሙ ወገናዊ ፍቅራቸውን ያለስስት ሰጧቸው፡፡ ሙሉ በሙሉ ነፃ እስክንወጣም ከጎናችሁ ነን በሚል መልዕክት ለዳግም ግዳጅ አብቅተው በራሳቸው ተሸከርካሪ ሸኝተዋቸዋል፡፡ ኒሯቅዎች ‹‹ብቻችን አንሞትም ብቻችንም ነፃ አንወጣም፤ ኢትዮጵያዊያንም ወደቀደመ ፍቅራችን የምንመለስበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም›› ነው ያሉት፡፡



ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው -ከአበርገሌ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ