
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪ ተመራቂ ተማሪዎችን ማስተማር ጀመረ።
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 05/2013 ዓ.ም (አብመድ) አለም አቀፍ ወረርሽኝ በሆነው የኮሮና ቫይረስ ምክንያት ከ2012 ዓ.ም መጋቢት ወር ጀምሮ የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ተዘግቶ መቆየቱ ይታወሳል።
ባለፈው ዓመት ተመራቂ የነበሩ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በተደረገላቸው ጥሪ ወደ ግቢ ተመልሰዋል። ዩኒቨርሲቲው ለተመራቂ ተማሪዎች ዛሬ ትምህርት መስጠት ጀምሯል።
በአፄ ቴዎድሮስ እና በማራኪ ግቢዎች ተዘዋውረን የትምህርት አጀማመሩን ለማየት እንደሞከርነው ተማሪዎች በመማሪያ ክፍላቸው ተገኝተው እየተከታተሉ ነው ።
በትምህርት አጀማመሩ የዛሬ ውሎ ተማሪዎችና መምህራን እንደወትሮው ሁሉ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርገው ነበር የመማር ማስተማር ሲከውኑ ያገኘናቸው፡፡
አስተያየት የሰጡን ተማሪዎች ከስምንት ወራት በላይ ትምህርት አቋርጠው በመቆየታቸው ይደርስባቸው የነበረውን ስነ ልቦናዊ ጫና በማስታወስ አሁን ግን በአዲስ መንፈስ መማር እንደጀመሩ ነግረውናል።
ዩኒቨርሲቲው መማር ማስተማሩን ውጤታማ ለማድረግ በሚገባ ተዘጋጅቶ መቆየቱን ገልፀዋል።
መምህራን ለተመራቂ ተማሪዎች የተሰጠው ጊዜ አጭር በመሆኑ ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ተገቢውን የመማር ማስተማር ስራ ጀምረናል ብለውናል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አስራት አፀደወይን (ዶ.ር) የማካካሻ ትምህርቱን ውጤታማ ለማድረግ ተገቢ የጊዜ መርሃ ግብር ድልድል እንደወጣ ተናግረዋል፡፡
ተማሪዎች ወደ ዪኒቨርስቲው ሲገቡ ጀምሮ ጥሩ አቀባበል እንደተደረገላቸውና በትምህርት መጀመሪያ ቀኑም በስኬት ማስተማር መጀመሩን ገልፀዋል።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ተገቢው ዝግጅት መደረጉን ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ፍፁምያለምብርሃን ገብሩ – ከጎንደር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ