
አርሶ አደሮች የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ በመሰብሰብ ሊያጋጥም የሚችለውን የምርት ብክነት ሊከላከሉ እንደሚገባ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አሳሰበ፡፡
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 05/2013 ዓ.ም (አብመድ) በወቅቱ ሰብልን አለመሰብሰብ እስከ 30 በመቶ የምርት ብክነት እንደሚያጋጥም ከአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡ የድህረ-ምርት ብክነት በአብዛኛው የሚከሰተው በአጨዳ ወቅት፣ በውቂያና በጎተራ ገብቶ ለገበያ እስከሚቀርብ ባለው ጊዜ ነው። አርሶ አደሮች የመኸር ምርትን ሲሰበስቡ ብክነት እንዳያጋጥም የግብርና ባለሙያዎችን ሙያዊ እገዛ ሊያገኙ ይገባል፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት ባለሙያ እንየ አሰፋ እንደገለጹት በአማራ ክልል በ2012/13 የምርት ዘመን 4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በሰብል በመሸፈን 127 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ ነበር፡፡ በዚህም የእቅዱ 96 ነጥብ 7 በመቶ በዘር ተሸፍኗል፡፡ እስከዚህ ወቅት ድረስ 3 ሚሊዮን ሄክታር ሰብል ተሰብስቧል፡፡
በምርት ስብሰባ ወቅት ብክነት እንዳይገጥም የክላስተር ሰብል ባለባቸው አካባቢዎች በኮማባይነር እየተሰበሰበ ይገኛል፡፡ እስከዚህ ወቅትም 19 ሺህ ሄክታር መሬት ሰብል በ104 ኮምባይነሮች መሰብሰብ መቻሉን ባለሙያዋ ገልጸዋል፡፡
አርሶ አደሩም የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ በመሰብሰብ እና ወዲያውኑ መውቃት እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡ ከተወቃ በኋላም በነቀዝ እና ሌሎች ተባዮች እንዳይጠቃ ተባይ መከላከያ በማሕበራት በኩል እየቀረበ እንደሚገኝ ነግረውናል፡፡
ሰብሉን በፍጥነት ወቅቶ ወደ ጎተራ ማስገባት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ አርሶ አደሮችም የተባይ መከላከያዎችን እና የብረት ጎተራዎችን በመጠቀም ሊደርስ የሚችለውን የምርት ብክነት መከላከል ይገባልም ብለዋል፡፡



ዘጋቢ፡-ዳግማዊ ተሰራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ