በወልቃይት ጠገዴ ሁመራ ባለፉት ዓመታት በአማራ ህዝብ ላይ ብዙ የማይካድራ ጭፍጨፋዎች መፈጸማቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

857
በወልቃይት ጠገዴ ሁመራ ባለፉት ዓመታት በአማራ ህዝብ ላይ ብዙ የማይካድራ ጭፍጨፋዎች መፈጸማቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 05/2013 ዓ.ም (አብመድ) ለዘመናት የትህነግን ሴራ ሲታገል የነበረው የወልቃይት አማራ ህዝብ ነፃ መውጣቱን ተከትሉ ደስታውን በአደባባይ መግለፅ ጀምሯል። የወልቃይት ጠገዴ ወፍ አርግፍና አካባቢው ነዋሪዎችም አደባባይ በመውጣት ያሳለፏቸውን የመከራ ዓመታት በማሰብ ዳግም እንዳይመለስ በጽናት ለመታገል አቋም ይዘዋል።
ኢትዮጵያ እንደ ሀገር በከሃዲው ትህነግ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2010 ዓ.ም በመንግስታዊ መዋቅር እየተመራች ህዝቦቿ ብዙ እንግልት ቢደርስባቸውም በተለይ የወልቃይት ጠገዴ አማራ ህዝብ ለአርባ አመታት ያሳለፈው መፈናቀል፣ ስደት፣ ድብደባና ሞት የከፋ ነበር።
ይህ ህዝብ አማራ በመሆኑና አማራ ነኝ በማለቱ ብቻ የዘር ማጥፋት ተፈፅሞበታል። ላለፉት አርባ አመታት ብዙ የማይካድራ አይነት ጭፍጨፋዎችን አይተናል የሚሉት የወልቃይት ጠገዴ አማራዎች የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ በኢትዮጵያዊነቱና በአማራነቱ ብቻ ሲፈናቀል፣ በቋንቋው እንዳይማር እንዲሁም ባህሉን እንዳይገልፅ ተከልክሎ እንደኖረ አስረድተዋል።
ትህነግ በአማራ ላይ ከፈፀማቸው ግፎች በወልቃይት ጠገዴ አማራ ህዝብ ላይ የፈጸመው ግፍ ረቂቅና የቡድኑን ሰው በላነትና የጭካኔ ጥግ ያሳየ ነው። ከአምስት መቶ ሺህ በላይ ህዝብ የተፈናቀለበት ይህ የወልቃይት ጠገዴ አማራ ህዝብ በአማራዊ ማንነቱ የሚኮራና ለዚህም ማንነቱ ዋጋ የከፈለ ህዝብ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች አረጋግጠዋል።
ከትህነግ የግፍ አገዛዝ ነፃ መውጣትን ተከትሎም የወልቃይት ጠገዴ ወፍ አርግፍ ከተማ ነዋሪዎች ህዝባዊ ማዕበል በታየበት ሰላማዊ ሰልፍ ደስታቸውን በአደባባይ ገልፀዋል። ነዋሪዎቹ ያየግፍ ጊዜ እንዳይመለስና ለዘመናት የታገሉለት የማንነት ጥያቄ እንዲከበርና ማንም በኃይል ሊጨፈልቅ የሚያስብ አካል ካለ ከድርጊቱ ሊቆጠብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ወጣት ፍሬወይኒ የኋላሸት በዚህ እድሜዋ ብዙ የትህነግን አማራ ጠልነት ስለማየቷ ገልፃለች። በአማርኛ መማር፣ አማርኛ ሙዚቃ ማድመጥ እንዲሁም አማራነትን የሚገልፁ የባህል ልብሶችን መልበስ በትህነግ አገዛዝ ወንጀል እንደነበር ተናግራለች። አሁን ግን የፈለገችውን መናገርና መልበስ በመቻሏ ያሳለፈችውን ጭቆና ዳግም ማየት እንደማትፈልግ ተናግራለች።
የወልቃይት ጠገዴ ጊዜያዊ አስተዳዳሪ አቶ አህመድ አብዱልቃድር ለህዝብ ባሰሙት ንግግርም የእስካሁኑ ግፍ ዳግም በአማራ ላይ እንዲፈፀም ምንም አይነት እድል መስጠት የለብንም ብለዋል። የትግራይ ህዝብ እህትና ወንድማችን ነው ያሉት ጊዜያዊ አስተዳዳሪው ለማንነታችን በምናደርገው ትግል ከጎናችን ሆኖ ሊደግፈን ይገባል ሲሉም ሃሳባቸውን ገልፀዋል።
ለዘመናት የዘር ማፅዳት ወንጀል በወልቃይት ጠገዴ ህዝብ ላይ ተፈፅሞብናል ያሉት አቶ አህመድ አብዱልቃድር ከዚህ በኋላ ዳግም በማንነታችን ሊያጠቃን የሚፈልግ አካል ካለ ትንኮሳውን እስከመጨረሻ ለመዋጋት ዝግጁ ነን ብለዋል።
ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ በበኩላቸው ባለፉት ዘመናት ማንነትን መሰረት ያደርገ ጭቆናና ዘር ማፅዳት በወልቃይት ጠገዴ አማራ ህዝብ ላይ መፈፀሙን ገልፀዋል። ዘራፊው ትህነግ በጉልበት ይዞብን የቆየው እርስታችን በመመለሱ ነፃነታችን ተረጋግጧል፣ ይህን ነፃነትም ማንም ሊቀማን አይችልም ብለዋል።
ዘጋቢ: አስፋው ሙቀት ከወፍአርግፍ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበኩር ጋዜጣ ታኅሣሥ 05/2013 ዓ/ም ዕትም
Next articleከ140 በላይ በሚሆኑ ተሸከርካሪዎች ላይ የተጫኑ ተተኳሾችን መያዙን የሃገር መከላከያ ሰራዊት አስታወቀ፡፡