
በጁንታው አባላት የታገቱት የሰሜን እዝ ኦፕሬሽን ምክትል አዛዥ ብርጋዴል ጄኔራል አዳምነህ መንግሥቴ በአገር መከላከያ ሠራዊት እና በፌዴራል ፖሊስ አባላት አስደናቂ ኦፕሬሽን ነጻ መውጣታቸውን ገለጹ።
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 03/2013 ዓ.ም (አብመድ)
በህወሃት ጁንታ አባላት ክህደት ተፈጽሞባቸው ከእገታ በአገር መከላከያ ሠራዊት እና የፌዴራል ፖሊስ አባላት ነጻ የወጡት የሰሜን እዝ ኦፕሬሽን ምክትል አዛዥ ብርጋዴል ጄኔራል አዳምነህ መንግሥቴ “ቤታችን ነን ባልንበት ሰዓት ክህደት ተፈጽሞብናል” ብለዋል።
“ክህደት በተፈጸመብን ወቅት ከ40 ቀናት በላይ በስቃይ ከመቆየታችን በተጨማሪ ረጅም የእግር ጉዞ እና አስቸጋሪ ሁኔታዎችን አሳልፈናልም፣ ሆኖም በጁንታው ኃይል ላይ የመከላከያ ሠራዊታችንና የፌዴራል ፖሊስ አባላት ከፊት እና ከኋላ በመሆን፣ የተለያዩ ቴክኒኮችን በመጠቀምና ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ጠላትን ከወገን የለየ አስደናቂ ኦፕሬሽን ፈጽመው ነጻ ወጥተውናል” ብለዋል ብርጋዴል ጄኔራል አዳምነህ።
“እንዲህ ዓይነት የክህደቶችን ተቋቁመን ነፃ በመውጣት አገራችን ያለችበት ሁኔታ በማየቴ ደስተኛ ነኝ” ያሉት ደግሞ የ20ኛ ክፍለ ጦር አዛዥ ብርጋዴል ጄኔራል ኑሩ ሙዘይን ናቸው።
በመከላከያ ሠራዊትንና በፌደራል ፖሊስ አባላት የጋራ አሰሳና ኦፕሬሽን ነጻ ከወጡ በኋላ በሰጡት አስተያየት “የጁንታው ኃይል የክህደት ተግባር ከፈጸመብን በኋላ በርካታ አስቸጋሪ ጊዜያቶችን አሳልፈናል፤ እኛ ተስፋ በመቁጥ ለአገራችን ልንሰዋ ነበር፤ መከላከያ ሠራዊታችንና ፌዴራል ፖሊስ አባላት በአስደናቂ ሁኔታ በሰሩት የተቀናጀ ኦፕሬሽን ነጻ አውጥቶውናል እንኳን ደስ አለን ልል እፈልጋለሁ” በማለት ተናግረዋል።
በመጨረሻም አገር ላይ ክህደት በፈጸመው ጁንታ ቡድን ላይ ያሳየነውን አንድነት በልማት እና በዕድገት ስራዎቻችን ላይ በማሳየት አኩሪ ተግባር መፈጸም ይኖርብናልም ሲሉ ከገለፁ በኋላ መንግሥት እና የኢትጵዮያ ሕዝብ ላደረጉላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል። መረጃው የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ነው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ