
‹‹ እንደ ምኒልክ አይነት ሩህሩህ የለም›› ታዬ ቦጋለ፡፡
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 03/2013 ዓ.ም (አብመድ)
ስለ ኢትዮጵያና ስለ ኢትዮጵያዊነት መሥማት ልቡ የወደደ ሁሉ ይከተላቸዋል፡፡ ኢትዮጵያን የሚወድ ሁሉ ይወዳቸዋል፡፡
ኢትዮጵያዊነት ጠላቱ የሆነ ደግሞ አምርሮ ይጠላቸዋል፡፡
ባገኙት አጋጣሚ በደረሱበት ሁሉ ስለ ኢትዮጵያና ስለ ኢትዮጵያዊነት ይናገራሉ፡፡ ይመሰክራሉ፡፡ የኢትዮጵያዊያንን ታሪክ በእውነት
ሚዛን ይመዝናሉ፡፡ ወገንተኝነታቸው ለእውነት ነው የታሪክ መምሕሩና የመራራ እውነት ደራሲው ታዬ ቦጋለ፡፡
ከዘመናት በፊት በዘመነችው፣ ከቀደሙት በፊት በቀደመችው ፣ የታሪክ ሀብታም በሆነችው ኢትዮጵያ ይመካሉ፡፡
ምኒልክና እውነተኛ ፌደራሊዝም ስርዓትን በተመለከተ ከአብመድ ጋርቀ ቆይታ አድርገዋል፡፡
ምኒልክ ሶስት አይነት የዘመቻ ምዕራፍ ነበሯቸው ነው ያሉት፡፡ የመጀመሪያው የሸዋ ንጉሥ በነበሩበት ወቅት የሸዋ አማራና የሸዋ
ኦሮሞ የጦር አበጋዞቻቸውን ይዘው በሰላማዊ መንገድ ግዛቶቻቸውን አስፍተው ነበር፡፡ በእነዚህ ሰላማዊ ዘመቻዎቻቸው ጅማን
ጨምሮ በርካታ አካባቢዎችን ይዘዋል፡፡
በእነዚህ ቦታዎች ሁሉ ገዥ የመደቡት የአካባቢውን ተወላጆች ነው፡፡ ትክክለኛ የሆነውን ፌደራሊዝም የጀመሩና አሁን ላይ የብሔር
ፌደራሊዝም የሚባለውን እሳቸው እስከ ታች ድረስ በተግባር ያሳዩ መሆናቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ዜጎች በቋንቋቸው እንዲተዳደሩ
ያደርጉ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡
ሁለተኛው ዘመቻቸው ደግሞ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ከሆኑበት ጊዜ እስከ አድዋ ጦርነት ባለው ጊዜ ነበር፡፡ በዘመቻቸው
አብዛኛውን ቦታ የያዙት በሰላማዊ መንገድ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
ሶስተኛው የዘመቻ ምዕራፍ ደግሞ ከአድዋ ድል በኋላ እንደነበር አንስተዋል፡፡ የምኒልክ ዘመቻ አንድም ኢትዮጵያዊያንን በጋብቻ
የማስተሳሰር፤ ሌላኛው በየአካባቢው ራሱን እንዲያስተዳድር የማድረግ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ትህነግ የሚመካበትና አሁን ላይ ያለው ፌደራሊዝም ግን የይስሙላህ መሆኑን ነው ያመላከቱት፡፡ እንደፈለገ የሚያሽከረክርበት
ፌደራሊዝም ነው ያሉት የታሪክ ምሁሩ የምኒልክ ፌደራሊዝም እውነተኛ፣ በጣም ዘመናዊ፣ በዚያ ዘመን ውስጥ ሊታሰብ የማይችል
የፌደራሊዝም ስርዓት ነበር ብለዋል፡፡
ምኒልክ አፍሪካን ወራሪዎች እየገቡባት እንደሆነ ያውቁ ስለ ነበር ከወገኖቻቸው ጋር ከመጋጨት ይልቅ በዙሪያቸው ጠላት እንዳለ
በመናገር በፍቅር ለመኖር ጥረት ያደርጉ እንደነበርም ነው የተናገሩት፡፡
ያለፉት ሶስት አስርት ዓመታት የኢትዮጵያ ታሪክ ችግሩ በፈጠራ የተመሰረተና የኦነግን፣ የወያኔንና ኢትዮጵያን ለማፍረስ
የሚፈልጉትን ሰዎች ዓላማ የያዘ መሆኑን ነው የታሪክ ምሁሩ ያስረዱት፡፡
‹‹እንደ ምኒልክ አይነት ሩህሩህ የለም›› ሲሉም ስለ ምኒልክ የሚወራው የሀሰት ትርክት መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡ ከሰው መሀል
አልቆ ሲያስገዛህ በሰው መጨከን አይገባም፣ ለሰው ሲያዝኑ እግዚአብሔር እድሜ ይሰጣል፣ የሚሉት ምኒልክ የባርያ ንግድ
የሚባለውን ተግባርና አስተሳሰብ አጥብቀው ይቃወሙ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡
ምኒልክ አይደለም ለወዳጅ ለካዳቸውና ሊገድላቸው ለተዘጋጄ ጭምር ይቅርታ የሚያደርጉ ሰው እንደነበሩም ተናግረዋል፡፡ ትልቅ
ቁም ነገራቸውና ትልቅ ራዕያቸው ከዘመን የቀደመ መሆኑንም ነግረውኛል፡፡ ምኒልክ ሕዝቤ በባዶ እግሩ እየሄደ እኔ በጫማ
አልሄድም ብለው የወርቅ ጫማቸውን አውልቀው በባዶ እግራቸው የሚሄዱ መሪ እንደነበሩም ምሁሩ አስታውሰዋል፡፡
ምኒልክ የስልጣኔ አውራና ጠቢብ ናቸው ያሉት አቶ ታዬ ቦጋለ ስለ እሳቸው የሚወራው በሙሉ ለፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ካልሆነ
በስተቀር እንደዚያ አይነት ሥነ ልቦና ያላቸው አይነት ሰው አልነበሩም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያዊያን በአንድነታቸው እንዲቀጥሉ የማያግባቡ ትርክቶች ሲኖሩ በማቆምና የሌላው ዓለም ተሞክሮ ምን ይመስላል
የሚለውን ማዬት ተገቢ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ በትምህርት ዓለማ መሄድና ሁሉንም ሰው በእኩል ማዬት ተገቢ እንደሆነም
ጠቅሰዋል። ወደሰፈር ከመውረድ በአንድነታችን ላይ መስራት እንደሚገባንም ነው ያሳሰቡት፡፡
የሰው ልጅ ለእንስሳት መብት በሚቆምበት ዘመን ያልተፈለገ ነገር ውስጥ መግባት እንደማይገባም አሳስበዋል፡፡ ውይይት፣
አዳዲስ ስርዓተ ትምህርት መቅረፅ፣ ቀናነትን፣ ሰውነትን መያዝ፣ በእምነት መራመድ፣ በዘመናት ውስጥ የነበረንን መስተጋብር
ማንሳት ይገባልም ብለዋል፡፡
መገናኛ ብዙኃን ታላላቅ የታሪክ አዋቂዎችን በማቅረብ ሰውን ከብዥታ ማውጣት እንደሚገባቸውም ተናግረዋል፡፡ ‹‹ዓለም
የምትጠፋው ከመጥፎዎች እኩይ ድርጊት ይልቅ በመልካሞች ዝመታ ነው›› እንዲሉ መልካሞች ዝም እንዳይሉ ማድረግ
ይገባልም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ ተነካች በተባለበት ሁሉ አብሮ በሚወድቀው በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ እንያት፤ እኛ የአንድ እናት ልጆች
ነን፤ ሰው በሞራል፣ በሃይማኖትና በሰውነት መኖር መቻል አለበትም ብለዋል፡፡
ሰው ሰው መሆኑን ቢያውቅና ለምን ዓላማ እንደተፈጠረ ቢገነዘብ፣ እመነት ቢኖረውና በእመነቱ ህግጋት ቢሄድ፣ በኢትዮጵያዊነት
ሥነ ምግባርና ሞራል ታንፆ ቢያድርግና የሚያደረግው ድርጊት ውጤቱ ምንድን ነው የእኔን ማሕበረሰብ ይጠቅማል ወይ
የሚለውን ቢረዳ መልካም እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
እንደ ኢትዮጵያ አንድ ላይ መታገል እንደሚገባም መክረዋል፡፡ ወደዚህ ምድር ፈልጎ የመጣ የለም፤ ወደዚህ ምደር ሌላውን ጠልቶ
ሌላውን ፈልጎ የመጣ ሰው ባለመኖሩ ሰውነቱን ልናከብረው እንጂ ልንጠላው አይገባም ነው ያሉት የታሪክ ምሁሩና የመራራ
እውነት ደራሲው ታዬ ቦጋለ፡፡
ዘጋቢ፡-ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m