<< የሚጠቃና አንገቱን የሚደፋ ክልል እንዲኖረን አንፈልግም፤ በጠላቶቻችን መቃብር ላይ የጀግንነት ታሪካችን እንፅፋለን >> አቶ አብርሃም አለኸኝ

754

<< የሚጠቃና አንገቱን የሚደፋ ክልል እንዲኖረን አንፈልግም፤ በጠላቶቻችን መቃብር ላይ የጀግንነት ታሪካችን እንፅፋለን >> አቶ
አብርሃም አለኸኝ
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 03/2013 ዓ.ም (አብመድ) ከአብመድ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት
ኃላፊ አቶ አብርሃም አለኸኝ እንደተናገሩት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን በየዘመኑ ድሎችን እያስመዘገቡ የመጡ ናቸው፤ በትህነግ
ላይ የተገኘው ድል በታሪካችን ሁሉ አስገራሚ የኅብረተሰብ ትግል ውስጥ የተገኜ ድል ነው ብለውታል፡፡
ትህነግ ባለፉት ዓመታት እንደ ሀገር መግባባት እንዳይኖር፣ በተለይ የአማራ ሕዝብ ግፍ እንዲሰራበት ሲሰራ እንደነበር ነው
የተናገሩት፡፡ ከ1966 ዓ.ም ወዲህ የአማራ ሕዝብ በተወሳሰበ ዳገት ውስጥ መምጣቱንም ተናግረዋል፡፡ ሕዝቡ ተለይቶ እየተጠቃ
የመጣ፣ የአማራ ልኂቃን እየታደኑ የተገደሉበት፣ የአማራ እሴት ላይ የተበላሸ አተያይ የነበረበት መሆኑንም አንስተዋል፡፡ በተለይም
ከ1983 ዓ.ም ወዲህ ትህነግ ግልጽ አደረጃጀት ፈጥሮ የአማራን የጥንካሬ ቦታዎች እየፈለገ በደል ያደረሰበት መሆኑን ነው
የተናገሩት፡፡
ትህነግ የአማራ የገዢ መደቦች የኢትዮጵያን ሕዝብ ሲጨቁኑ እንደነበርና ሌሎች ብሔር ብሄረሰቦች ሲጨቆኑ የአማራ ሕዝብ ግን
ሳይጨቆን የኖረ ሕዝብ ነው የሚል አሳፋሪ ትርክት ፈጥሮ ሲሰራ የነበረ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በ2010 ዓ.ም ትህነግ ወደ መቀሌ ሲገባ የአማራ ሕዝብ ፈታኝ ጊዜያትን እንዳሳለፈም አስታውሰዋል፡፡ ከለውጡ ወዲህ ባሉት
ዓመታት የአማራ ሕዝብ በተገኘበት የሚገደልበት፣ የሚፈናቀልበትና ሃብትና ንብረቱ ሲዘርፍ የቆየ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ይህ
ደግሞ በታሪክ አጋጣሚ ትልቁ ስብራት ነው፤ የአማራ ሕዝብ የሚሞትበት ብቸኛው ሐጥያት አማራ መሆን ብቻ እንደሆነም
አንስተዋል፡፡
ትህነግ ወደ መቀሌ ከኮበለለ በኋላ የአማራን ሕዝብ ማጥፋት፣ ኢትዮጵያን ዳግመኛ መቆጣጠር ከቻሉ ደግሞ ሀገር የማፈራረስ
አላማ እንደነበራቸውም አንስተዋል፡፡
የትህነግ እኩይ ዓላማ እንዳይፈፀም በተደረገ ርብርብ ወደ ትክክለኛው የኃይል አሰላለፍ በመምጣት ዓላማውን ማክሸፍ
መቻሉንም ገልፀዋል፡፡
‹‹ ማንም እንደሚያውቀው እኛ እየሰራን ያለነው ራሳችንን ለመከላከል እንጂ ለማንም ስጋት ለመሆን አይደለም›› ያሉት አቶ
አብርሃም ‹‹ የሚጠቃና አንገቱን የሚደፋ ክልል እንዲኖረንም አንፈልግም›› ብለዋል፡፡
የአማራ ሕዝብ ትናንት፣ ዛሬና ነገ ለኢትዮጵያ ዋስትና እንጂ ስጋት አይሆንም፤ የአማራ ፖለቲካም ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊያን
ዋስትና ዘብ እንጂ ስጋት አይሆንም ነው ያሉት፡፡ ልዩ ኃይሉና ሚሊሻው ያደረገው ተጋድሎም ይህንኑ ያረጋገጠ ነው ብለዋል፡፡
የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ምርኮኛን በእንክብካቤ የሚይዝ፣ ቁስለኛን የሚያክም እንጂ በቀለኛ አለመሆኑንም ተናግረዋል፡፡ አማራ
ነን ስንል ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን ፈፅሞ አንዘነጋም ያሉት አቶ አብርሃም የእኛ ትግላችን በእኩልነት መኖር ነውም ብለዋል፡፡
እኛ ጨፍጫፊዎችን እየለዬን እንታገላለን እንጂ ጨፍጫፊዎቹ የወጡበትን ማኅበረሰብ አንረብሽምም ነው ያሉት፡፡ የአማራ ትግል
ፊት ለፊትና ግልፅ የሆነ እንጂ መሰሪ የሆነ ትግል የለንም ብለዋል፡፡
ልዩ ኃይሉና ሚሊሻው የሰራው ጀብዱ ለዘላለም በታሪክ የሚቀመጥ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው ጀብዱው ኢትዮጵያን ከመበታተን
ታድጓል ነው ያሉት፡፡ የተፈፀመው ጀብዱ ኢትዮጵያ እንድትቀጥል የሚያደርግና የአባቶቻችን ውል የተፈፀመበት ነውም ብለዋል፡፡
አማራ የመስፋፋት ታሪክ የለውም ነገር ግን ያለ እዳው ዘማች ሆኖ ተስፋፊና አህዳዊ እየተባለ ሲቀጠቀጥ ኖሯል፤ ይህ አሁን ላይ
ማብቃት አለበት ነው ያሉት፡፡
የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ተጋድሎ የአማራ ሕዝብ ቀና ብሎ እንዲሄድ ያደረገና በየቦታው በግፍ የፈሰሰውን የአማራ ደም የካሰ
መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ አሁንም የአማራን ሕዝብ ሊሰብሩ የሚጥሩ የትህነግ ፍርስራሾች መኖራቸውን የተናገሩት አቶ አብርሃም
በእርግጠኝነት እናሸንፋቸዋለን፤ ከጠላቶቻችን መቃብር ላይ የጀግንነት ታሪካችን እንጽፋለን ብለዋል፡፡
የመበቃቀል ታሪክ ማቆምና መጥፋት እንደሚገባውም አሳስበዋል፡፡
የአማራ ከፍታ፣ ሰብዓዊነት፣ የሞራል ልዕልና እና የኢትዮጵያዊነት ጥግ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በኃላ ወደ ከፍታ መገስገስ
እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ

 

Previous articleሐረማያ ፣ ድሬዳዋ እና ሠመራ ዩኒቨርሲቲዎች ተመራቂ ተማሪዎችን መቀበል መጀመራቸውን አስታወቁ፡፡
Next article‹‹ እንደ ምኒልክ አይነት ሩህሩህ የለም›› ታዬ ቦጋለ