ሐረማያ ፣ ድሬዳዋ እና ሠመራ ዩኒቨርሲቲዎች ተመራቂ ተማሪዎችን መቀበል መጀመራቸውን አስታወቁ፡፡

156

ሐረማያ ፣ ድሬዳዋ እና ሠመራ ዩኒቨርሲቲዎች ተመራቂ ተማሪዎችን መቀበል መጀመራቸውን አስታወቁ፡፡
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 03/2013 ዓ.ም (አብመድ) የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የህዝብ እና አለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ
አለምእሸት ተሾመ እንደተናገሩት 3 ሺህ 192 ተመራቂ ተማሪዎችን ለማስተናገድ እየተቀበሉ ነው።
ከህዳር 29 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ተማሪዎችን በመቀበል እስካሁን ከ85 በመቶ በላይ በዋናው ግቢና ሐረር ከተማ በሚገኘው
የጤናና ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ መግባታቸውን አስታውቀዋል።
የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል በወጣው መመሪያ መሰረት በአንድ የመማሪያ ክፍል 25 ተማሪዎች ትምህርት የሚከታተሉባቸውና
በአንድ መኝታ ክፍል ሁለት ተማሪዎች የሚኖሩባቸው ቦታዎች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ተማሪዎቹም የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል በማድረግ እና ርቀታቸውን ጠብቀው መስተናገድ እንደሚጠበቅባቸው
አመልክተዋል።
ኮሮናን በመከላከል ሠላማዊ የመማር ማስተማር ሥራን ለማጎልበት ወደ ተቋሙ ለገቡ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲው በየትምህርት
ክፍላቸው ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል ብለዋል።
የኮሮና ቫይረስን ጥንቃቄ ባደረገው የመማር ማስተማር ስራን ለማስጀመር ከኮሌጃቸው ተጠሪዎች ጋር ለአንድ ወር በሁሉም ዘርፍ
የዝግጅት ስራ ማከናወናቸውን የገለጸው ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የሐረር ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የተማሪዎች አቀባበል አስተባባሪ
ተመራቂ ተማሪ ደቻሳ ዳንደና ነው።
በአሁኑ ወቅትም በሠላማዊ መማር ማስተማር ስራ ዙሪያ ለተማሪው ግንዛቤ የመስጠት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግሯል።
ተመራቂ ተማሪ ፌቨን እንዳልካቸው በበኩሏ ከኮሮና ቫይረስ በመጠንቀቅ ትምህርቷን ለመጀመር መዘጋጀቷን ገልጻለች።
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር መገርሳ ቃሲም እንደተናገሩት ጥሪ ከተደረገላቸው ከ2 ሺህ
500 ተማሪዎች መካከል 2 ሺህ 300ዎቹ አምና በወረርሽኙ ሣቢያ ሣይመረቁ የቀሩ ናቸው።
ለሁለት ወራት በሚዘልቀው የተመራቂ ተማሪዎች የመማር-ማስተማር ሂደት ለመጀመር አስፈላጊ የቅድመ ዝግጅት መደረጉን
ተናግረዋል፡፡
ከተከናወኑት ስራዎች መካከል የመማሪያ ክፍሎች፣ ምግብ ቤቶች እና ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያግዙ ግብዓቶች
የማመቻቸት ሥራዎች ይገኙበታል ብለዋል።
በሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የተዘጋጀው የኮሮና ቫይረስን መከላከል መመሪያና ለተማሪዎች የሚያግዙ የሥነ-ልቦና
ስልጠናዎች መዘጋጀታቸውን ዶክተር መገርሳ አስረድተዋል፡፡
የተቀበሏቸው ተማሪዎች ትምህርታቸውን በመጪው ሰኞ እንደሚጀምሩ አስታውቀዋል፡፡
ወደ ዩኒቨርስቲው የገቡ ተማሪዎች ራሳቸውን ከኮሮና በመከላከል የመማር ማስተማር ሂደቱ ሠላማዊ ሆኖ እንዲቀጥል
ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡
ተመራቂ ተማሪ ታሬል ጃል ለዘጠኝ ወራት ከትምህርት ገበታ በመለየታቸው ምክንያት ላጋጠማቸው ሥነ-ልቦናዊ ጫና መፍትሄ
የሚሰጥ ስልጠና ዩኒቨርስቲው ማመቻቸቱ ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ እንደሚያግዛቸው ተናግሯል፡፡
ሌላው ተመራቂ ተማሪ ታከለ የሽጥላ በበኩሉ ወደ ትምህርት ገበታዬ እመለሳለሁ የሚለው ተስፋዬ ዕውን በመሆኑ ደስታዬ ወሰን
የለውም ብሏል፡፡
በዩኒቨርስቲ ቆይታው የመማር ማስተማር ሂደቱ ሰላማዊ እንዲሆን የድርሻውን እንደሚወጣ ገልጿል፡፡
ተማሪ ደብተር ወረታው በሰጠው አስተያየት የተደረገላቸው አቀባበል እንዳስደሰተው ተናግሯል፡፡
በተመሳሳይ ሠመራ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎችን ዛሬ መቀበል መጀመሩን የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት
ዶክተር አቡዱራሆማን ከድር አስታውቀዋል።
የተመራቂ ተማሪዎች መግቢያ ጊዜ እስከ ነገ ድረስ እንደሚቆይና ከ2 ሺህ በላይ ተማሪዎች እንደሚቀበሉ ለኢዜአ ተናግረዋል።
ተማሪዎቹ በቆይታቸው ራሳቸውን ከኮሮና ቫይረስ በመጠበቅ ትምህርታቸውን መከታተል እንዲችሉ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ
ጭንብልን ጨምሮ ሌሎችም ግብዓቶች መዘጋጀታቸውን አመላክተዋል።
ለተመራቂ ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲውና አካባቢው ማኅበረሰብና አቀባበል እያደረጉላቸው መሆኑ ተገልጿል።
ከዩኒቨርሲቲው ተመራቂ ተማሪዎች መካከል በእውቀቱ ምስጋናው በሰጠው አስተያየት የተቋሙ የሥራ ኃላፊዎችና የአካባቢው
ማኅበረሰብ ያደረጉልን አቀባበል አስደሳች ነው ብሏል።
ተማሪ አፀደ አበባው በበኩሏ በኮሮና ምክንያት ተቋርጦ የነበረው ትምህርታቸው በመጀመሩ መደሰቷንና ከኮሮና በመጠንቀቅ
ትምህርቷን በስኬት አጠናቃ ለመመረቅ መሰናዳቷን ገልጻለች።

Previous article‹‹ የሚጠልሁን ሰዎች ከማጥፋት የሚጠሉብህን ነገር አጥፋ››
Next article<< የሚጠቃና አንገቱን የሚደፋ ክልል እንዲኖረን አንፈልግም፤ በጠላቶቻችን መቃብር ላይ የጀግንነት ታሪካችን እንፅፋለን >> አቶ አብርሃም አለኸኝ