
በወራሪው፣ ተስፋፊውና አሸባሪው የትህነግ ቡድን በቀን እስከ 25ሺህ የሀሰት መረጃዎች በትዊተር ሲሰራጭ እንደነበር
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ገለጸ፡፡
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 03/2013 ዓ.ም (አብመድ) ወራሪው፣ ተስፋፊውና አሸባሪው የትህነግ ቡድን የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን
በመጠቀም ከፍተኛ የሆነ የስነ-ልቦና ጦርነቶችን ሲያከናዉን እንደነበር የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ምክትል ዋና
ዳይሬክተር አቶ ከፍያለዉ ተፈራ ገለጹ፡፡
ሃገሪቷን ወደ ለየለት ትርምስ ለማስገባት አሸባሪው ቡድን የሳይበር ምህዳሩን በመጠቀም ከፍተኛ የማወናበድ ስራ ሲሰራ
እንደነበርም ሃላፊዉ ተናግረዋል፡፡
ቡድኑ ዲጂታል ወያኔ የተባለ የሃሰት መረጃዎችን የሚያሰራጭ ቡድን በማቋቋም በበላይነት ሲመራ እንደነበር ሃላፊዉ
አመላክተዋል፡፡ የሳይበር ተፋላሚዎችን በመቅጠርም የኦሮሞ ብሄር ተወላጅ መስለው አማራን፤ የአማራ ብሄር ተወላጅ መስለው
ደግሞ የኦሮሞን ስም ሲያጠለሹ መቆየታቸዉን አንስተዋል፡፡
ወራሪው፣ ተስፋፊውና አሸባሪው የትህነግ ቡድን ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ከማድረሱ በፊት
ከመሃል ሃገር የሚደረጉ ግንኙነቶች እንዳይኖሩ የመገናኛ ስርዓቱን ከጥቅም ዉጪ ማድረጉንም አቶ ከፍያለው አስገንዝዋል፡፡
ቡድኑ ትዊተርን በመጠቀም የሃሰት መረጃ በማሰራጨት ከፍተኛ የሆነ የስም ማጥፋት ዘመቻዎችን ሲያከናውን መቆየቱንም
ገልፀዋል፡፡
የሃሰት ፕሮፖጋንዳውን ከተለያዩ ብሄር ጽንፈኛ የሆኑ ደጋፊዎቻቸዉን እና የዉጭ ዜጋ ሆነዉ ከዚህ ቀደም የጥቅም ትስስር
የነበራቸዉን አካላትን በማደራጀት የዘመቻዉ አካል እንዳደረጓቸዉም ምክትል ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል፡፡
በፕሮፓጋንዳው ዘመቻም በቀን እስከ 25 ሺህ ሃሰተኛ ትዊቶችን እንዲሁም የሃሽታግ አካዉንቶችን በመክፈት ደግሞ በቀን
ከ13ሺህ እስከ 18ሺህ ሃሰተኛ መረጃዎችን ሲያሰራጩ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
በዚህ የሃሰት ፕሮፖጋንዳም የህግ ማስከበር ሳይሆን ግዛት ማስፋፋት ተግባር አድርጎ የማቅረብ፣ በጦርነቱ ንጹሃን በከፍተኛ ሁኔታ
እየተጨፈጨፉ እንደሆኑ የማስተጋባት፣ በትግራይ ተወላጆች ላይ የዘር ማጥፋት ዘመቻ እየተፈጸመ እንደሆነና በመላዉ ሃገሪቱ
የትግርኛ ተናጋሪዎች ተነጥለዉ የጥቃት ዒላማ እንደሆኑ በማስመሰል መዘገብ ይገኙበታል ብለዋል፡፡
መንግስት በወራሪው፣ ተስፋፊውና አሸባሪው የትህነግ ቡድን ላይ የህግ ማስከበር ተግባር መጀመሩን ተከትሎ የተለየ የሳይበር
ጥቃት እንዳልተከሰተ ያነሱት አቶ ከፍያለዉ ሆኖም በዓለም ላይ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ ብዙዎቹ በቤታቸው
ሆነው በኦንላይን እየሰሩ ባለበት ሁኔታ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተጠበቀዉ በላይ በ3 እጥፍ የሳይበር ጥቃት መጨመሩን
ጠቅሰዋል፡፡
በህግ ማስከበር ዘመቻዉ ወቅት የህወሃት ጁንታው ቡድን የድምፀ ወያነ እና የትግራይ ቴሌቪዥን ፍላይ አዌይ ስርዓትን
በመጠቀም ግዙፍ የሃገሪቱን የሚዲያ ተቋማት አገልግሎት ለማቋረጥ ሙከራ እንዳደረገ ጠቁመዋል፡፡
የዚህ ጥቃት ኢላማ ከነበሩ ሚዲያዎች መካከልም ኢቢሲ߹ ዋልታ እና ኦ ቢ ኤን ዋናዎቹ እንደነበሩ የጠቀሱት ምክትል ዳይሬክተሩ
ፋና እና ሌሎች ሚዲያዎችን ስርጭት የማቋረጥ ተግባር የመፈጸም አዝማሚያ እንደነበር ሃላፊዉ አስታውሰዋል፡፡ ሆኖም
ኤጀንሲዉ በወሰደዉ ቅድመ መከላከል በመገናኛ ብዙኃኑ ላይ ሊደርስ የታሰበውን የጠለፋ ተግባር ለማክሸፍ መቻሉን
አስረድተዋል፡፡
ከዲጂታል ወያኔ በተጨማሪ ሌሎች የጥቅም ተጋሪዎች በጥፋት ዘመቻዉ ተሳታፊ ነበሩ፤ በግለሰቦች ደረጃ ከ50 እስከ 500
የሚደርሱ ሰዎችን በስራቸዉ በማሰማራት እና ክፍያ በመፈጸም ጥቃት ለማድረስ መሞከሩንም አመላክተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዉስጥም አንድ ለአምስት እና አንድ ለሃያ አደራጅተዉ አጀንዳ እየሰጡ ብሄርን ከብሄር ህዝብን ከህዝብ ሲያጋጩ
የሚዉሉ ኃይሎች መኖራቸው እንደተደረሰበት አቶ ከፍያለዉ ገልፀዋል፡፡
በዉጭ ሃገራት ከሚገኙ ጽንፈኛ ቡድኖች እና ሚዲያዎች ጋር በመናበብ የተለያዩ የጥፋት እንቅስቃሴዎችን ሲያከናዉኑ ነበር፤
ለአብነትም ኦ.ኤም.ኤን ቴሌቪዥንን ጨምሮ ኢትዮ-360 ከሚባል የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ጋር ሲሰሩ መቆየታቸዉን አስታውቀዋል፡፡
ኅብረተሰቡ የሳይበር ምህዳሩን በመጠቀም ከሚሰራጩ የሀሰተኛ መረጃዎች እራሱን በመጠበቅ ትክክለኛዉን መረጃ
ከሚመለከተዉ አካል ብቻ ለማግኘት መሞከር እንዳለበት ማሳሰባቸውን ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ የተገኘ መረጃ
ያመላክታል፡፡