የጎንደር ከተማ አስተዳደር የመስሪያ ማሽን ያላቸው ባለሀብቶች ፈጥነው ወደሥራ እንዲገቡ ለማስቻል የተሟላ ሸድ ማዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡

349
የጎንደር ከተማ አስተዳደር የመስሪያ ማሽን ያላቸው ባለሀብቶች ፈጥነው ወደሥራ እንዲገቡ ለማስቻል የተሟላ ሸድ ማዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 02/2013 ዓ.ም (አብመድ) የመስሪያ ማሽን እያላቸው ወደ ሥራ ለመግባት የተቸገሩ ባለሀብቶችን በፍጥነት ሥራ ለማስጀመርና በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ሚናቸውን እንዲወጡ መሠረተ ልማት የተሟላላቸው አምስት የክላስተር ማዕከላት መዘጋጀታቸውን የጎንደር ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት አስታውቋል፡፡
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ታሪክና የአሁኗ የቱሪዝም ማዕከል ጎንደር የኢንቨስትመት እንቅስቃሴዋ ቀዝቃዛ ሆኖ ለዘመናት ቆይቷል፡፡
የሀገርና የውጪ ሃገራት ባለሀብቶች መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈስሱ ባለመሠራቱ እስከ 2008 ዓ.ም በከተማዋ የነበሩት ኢንዱስትሪዎች ውስን ነበሩ፡፡ በዚህ ምክንያት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ ሊያነቃቁ የሚችሉ እንደ ሰሊጥ፣ ኑግና ሌሎች በአካባቢው የሚመረቱ የግብርና ምርቶች በጥሬ ለውጪ ገበያ ቀርበው፤ ተቀነባብረውና እሴት እየተጨምሮባቸው በውድ ዋጋ ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ፡፡
ከሦስት ዓመታት ወዲህ ግን በከተማዋ ተስፋ ሰጪ ጅምር የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ አለ፡፡ ለ1 ሺህ ገደማ ሰዎች ሥራ ዕድል የፈጠሩ 44 መካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ምርት ጀምረዋል፡፡ ምርት የጀመሩት አብዛኛዎቹ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች ናቸው፡፡ ምርታቸውን ለገበያ በማቅረብ ውጤታማ መሆናቸውንም አብመድ ያነጋገራቸው አምራች ኢንዱስትሪዎች አስታውቀዋል፡፡
ግብዓት አምራች አርሶ አደሮችን በሚጠቅም መልኩ ዕሴት ጨምረው ለገበያ በማቅረብ ለኢኮኖሚው መነቃቃት ሚና እየተጫወቱ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ከነዚህ መካከል በጸሐይ ሁለገብ የገበሬዎች ሕብረት ሥራ ዩኒየን አማካኝነት ተገንብቶ በ2011 ዓ.ም ማምረት የጀመረው የዘይት ፋብሪካ ተጠቃሽ ነው፡፡
በቀን 10 ሺህ ሊትር የማምረት አቅም ያለው ይህ ፋብሪካ የአካባቢውን የዘይት ፋላጎት ይሸፍናል፡፡ 149 አባል ሕብረት ሥራ ማሕበራትና 131 ሺህ ባለቤት አርሶ አደሮችም ለፋብሪካው ግብዓት ያቀርባሉ፡፡
የዘይት ፋብሪካውን ጨምሮ ሌሎችም የሥራ ዕድል ከመፍጠር፣ ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን ተክቶ የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ከመሸፈንና የውጪ ምንዛሬን ከማስቀረት ባለፈም ምርታቸውን ለውጪ ገበያ ለማቅረብ በትኩረት እየተሠራ ነው፡፡ ለዚህም አርሶ አደሮችን ከኢንዱስትሪ ጋር የማስተሣሠር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ኢንዱስትሪና ኢንቨስመንት መምሪያ ኃላፊ ተወካይ ደሴ መኮንን ተናግረዋል፡፡
ምርት ከጀመሩት በተጨማሪ 178 ፋብሪካዎች በግንባታና በቅድመ ግንባታ ሂደት ላይ ይገኛሉ፡፡ 78 አዲስ የኢንቨስትመንት ጥያቄዎችም የመንግሥትን ውሳኔ በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡
አቶ ደሴ እንደተናገሩት ከተማ አስተዳደሩ ኢንቨስትመንቱን ለማሳደግ የመሠረተ ልማት ሥራዎች አከናውኗል፤ እያከናወንም ይገኛል፡፡ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ይነሳ የነበረው የኃይል አቅርቦት ማነስ ለመፍታት የአቅም ማሳደግ ስራ ተከናዉኗል፤ ለአምስት የኢንዱስትሪ መንደሮች ትራንስፎርመር ለማስገባት እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ፈጣን እና ቀልጣፋ አገልግሎት መሥጠት ኢንቨስትመንቱን ለማበረታታት ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል ናቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ከተማ አስተዳደሩ በቂ የኢንቨስትመንት ቦታ ከሦስተኛ ወገን ነጻ አድርጎ ባለሀብቶችን እየተጠባበቀ ነው፡፡ በተለይ የመስሪያ ማሽን ያላቸው እና ሥራ ለሚጀምሩ ለዝቅተኛና መካከለኛ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሟላ መሠረተ ልማት ያላቸው አምስት የክላስተር ማዕከላት ተዘጋጅቷል፡፡ እነዚህ ማዕከላት እስከ 300 ካሬ ሜትር የወለል ስፋት ያላቸው ሸዶች አላቸው፡፡ በሌላ በኩል በቂ የኢንቨስትመንት ቦታ ወስደው ሥራ ያልጀመሩ ባለሀብቶችን ቦታ በመቀማት ፈጥነው ለሚያለሙ የማስተላለፍ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡
ባለፈው የ2012 በጀት ዓመት ብቻ ፈጥነው ማልማት ካልቻሉ 30 ባለሀብቶች መሬት በመውሰድ 25 የሚሆኑት ለተሻለ አልሚዎች ተላልፈዋል፡፡ ቀሪዎቹንም የማስተላለፍ ስራ ይሠራል ነው ያሉት፡፡ አሁን ላይ በከተማዋ ያሉ ሁሉም ኢንቨስትመንቶች በጥሩ እንቅስቃሴ ላይ እንደሆኑ አመላክተዋል፡፡
በከተማ አስተዳደሩ ብዙ የኢንቨስትመንት አማራጭ መኖራቸውን የጠቀሱት አቶ ደሴ ባለሀብቶች ጎንደር ላይ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈስሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
Previous articleየሚኒስትሮች ምክር ቤት በተለያዩ ጉዳዩች ላይ ዉሳኔዎች አሳለፈ፡፡
Next articleመንግሥት በትግራይ ክልል የሚያከናውነውን የመልሶ ግንባታ ምዕራፍ ቻይና እንደምትደግፍ የቻይና ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴንግ ሊ አስታወቁ።