
ከ80 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሃብት አስመዝጋቢዎች የመጀመሪያ ደረጃ እና ዳግም ምዝገባ ማከናወኑን የአማራ ክልል ሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 30/2013 ዓ.ም (አብመድ) ሙስናና ብልሹ አሰራርን አስቀድሞ ለመከላከል ተሿሚዎች፣ ተመራጮች እና የመንግስት ሰራተኞች የሃብት ማሳወቅ እና ምዝገባ እዲያከናውኑ በህግ ተደንግጓል፡፡
በአማራ ክልል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የሃብት ማሳወቅ እና ምዝገባ ዳይሬክተር ዘላለም ህብስቱ እንደገለጹት በክልሉ ከ2005 እስከ 2012 ዓ.ም ከ65 ሺህ በላይ ሃብት አስመዝጋቢዎች የመጀመሪያ ደረጃ ምዝገባ ተከናውኗል፤ ከ15 ሺህ በላይ ደግሞ የዳግም ምዝገባ ተካሂዷል፡፡
በአሁኑ ወቅት ደግሞ ሶስተኛ ዙር ምዝገባ መጀመሩን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡ አንድ ሃብት አስመዝጋቢ በመንግስት ስራ ከተቀጠረ በ45 ቀናት ውስጥ ያለውን ሃብት ማስመዝገብ እንዳለበት አዋጁ ያዛል፡፡
አስመዝጋቢዎች በተቀመጠው ጊዜ ሃብታቸውን ካላስመዘገቡ 1ሺህ ብር መቀጫ ከፍለው በ30 ቀን ውስጥ እንዲያስመዘግቡ አዋጁ አስቀምጧል፡፡
ይሁን እንጂ በተቀመጠው ተጨማሪ 30 ቀን ውስጥ የሃብት ምዘገባ አለማካሄድ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 417 በተደነገገው መሰረት ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት እንደሚያስቀጣ ተቀምጧል፡፡ ይሁን እንጂ በተቀመጠው ህግ መሰረት ቀርቦ በማስመዝገብ በኩል እጥረት እዳለ ነው አቶ ዘላለም የተናገሩት፡፡
የአማራ ክልል ሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ሃብት አስመዝጋቢዎችን ከመመዝገብ ባለፈ ያላቸው ሃብት ከገቢያቸው ጋር የማይጣጣም አስመዝጋቢዎችን በክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ምርመራ እዲካሄድ እያደረገ ነው፡፡ በዚህ ዓመትም የሃብት አስመዝጋቢዎች በተወለዱበት እና በሰሩበት ተቋም መረጃ የማሰባሰብ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ አቶ ዘላለም ገልጸዋል፡፡
የተገኘው መረጃ ሀብት አስመዝጋቢዎች በምዝገባ ቅጽ ከሞሉት መረጃ ጋር የማይጣጣም ከሆነ በፖሊስ ኮሚሽን ምርመራ አንደሚደረግ አብራርተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሰራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ