ሳምሪ የማይካድራዎቹ አካዙ !

427

ሳምሪ የማይካድራዎቹ አካዙ !

ባሕር ዳር፡ ኅዳር 30/2013 ዓ.ም (አብመድ) በዓለም አቀፍ ደረጃ በዘር ጭፍጭፋ ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች ዛሬ ታስበው ይውላሉ፡፡
በተለያዩ ሃገራት በስልጣን ላይ ያሉ ጽንፈኛ ፖለቲከኞች፣ አክራሪ የጎሳ መሪዎች፣ አማጽያን እና ሌሎች በፈጸሟቸው የዘር ማጥፋት ወንጀሎች የበርካታ ንጹኃን ሕይወት ተቀጥፏል፡፡
ግዛት ማስፋፋት፣ ባላንጣ ተብሎ የሚታሰብ አካልን ማዳከም፣ ጥላቻ፣ የፖለቲካና የሀይማኖት ዓላማን ለማሳካት እንዲሁም ሌሎች ምክንያቶች ለዘር ማጥፋት ወንጀሉ እንደ ቅድመ ሁኔታ ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡
ጀርመን ላይ ናዚ አይሁዶችን በአሰቃቂ ሁኔታ የጨፈጨፈበት፣ በቱርክ አርሜኒያዎች በሚዘገንን መልኩ ለእልቂት የተዳረጉበት፣ በአሜሪካ ቀይ (ሬድ) ሕንዳውያን ላይ የተፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀሎች በታሪክ ከሚታወሱ መጥፎ ክስተቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ከጀርመኑ የናዚ አጸያፊ ጭፍጨፋ በኋላ በሌሎች ሀገራት የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዳይከሰት ለመከላከልና ሀገራት ለወንጀሉ ከበድ ያለ የቅጣት ሕግ እንዲያወጡ እ.አ.አ 1948 ዓለም አቀፍ ስምምነት ቢደረግም ሕልቆ መሳፍርት ንጹሃንን በግፍ የሚያጠፋው ወንጀል መቋጫ አላገኘም፡፡
በ1994 በአፍሪካዊቷ ሩዋንዳ በ100 ቀናት ውስጥ በተካሄደ የዘር ማጥፋት ወንጀል 800 ሺህ ሰዎች ውድ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ሃገሪቱን ሲመሩ በነበሩ ጽንፈኛ የሁቱ ጎሳ ፖለቲከኞች፣ በደጋፊዎቻቸውና በታጠቁ ሚሊሻዎች በቱትሲ ጎሳ አባላት ላይ አሰቃቂ የዘር ማጥፋት ወንጀል፣ የጦር ወንጀልና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈፅመዋል፡፡
ዓለም ካስተናገደቻቸው መጥፎ ሁነቶች መካከል ተመሳሳይ ቋንቋና ባሕል ያላቸው፣ በሀይማኖት የሚመሳሰሉና ተሰበጣጥረው በሚኖሩ ሰዎች ላይ የተፈጸመው እልቂት በቀዳሚነት ይነሳል፡፡
ሕዝብን ያሳተፈ፣ መጠኑም ሰፊ የሆነና በአጭር ቀናት ብዙ ቀውስ ያስከተለ እጅግ ዘግናኝ እና አሰቃቂ ድርጊት ነው፡፡ ግድያው ያነጣጠረው በቱትሲ የጎሳ አባላት ይሁን እንጂ ለዘብተኛ አቋም የነበራቸው ሁቱዎችም ከገፈቱ ቀምሰዋል፡፡ አክራሪ የሁቱ ፖለቲከኞች፣ ልሂቃንና ወጣቶች ኢ-መደበኛ አደረጃጀት በመፍጠር የቱትሲ ጎሳ አባላትን ለማጥፋት የራዲዮ ጣቢያ በማቋቋም፣ ዕቅድ በማዘጋጀትና ሊገደሉ የሚገባቸው ሰዎች ዝርዝር በማዘጋጀት የዘር ፍጅቱን ለሚፈፅሙ ታጣቂዎች መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ለ100 ቀናት በቆየው የዘር ማጥፋት ወንጀል ከ800 ሺህ በላይ ንጹሃን ተገድለውበታል፡፡
“የዘር ማጥፋት ወንጀል እንደ ተላላፊ በሽታ እየተቆጠረ ነው” ያሉት የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የስነጽሁፍ መምሕር መዘምር ግርማ በኢትዮጵያ ያለው የዘር ማጥፋት እንቅስቃሴ አስመልክቶ ለአብመድ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
መምህር መዘምር ስለ ሩዋንዳ የዘር ማጥፋትና የፍጅቱን አሰቃቂነት ለማሳየት ኢማኪዩሌ ኢሊባጊዛ እና ስቲቭ ኤርዊን የጻፉትን ‹ሁቱትሲ› የተሰኘ መጽሐፍ ወደ አማርኛ ተርጉመው ለኢትዮጵያውያን አንባቢ አብቅተዋል፡፡
መጠኑና ባህሪው የተለዬ ቢሆንም በኢትዮጵያ የዘር ማጥፋት ወንጀሎች መፈጸማቸውን ተናግረዋል፡፡ በሀገሪቱ ለዘር ማጥፋት የሚጋብዝ ሕገመንግሥታዊ ሽፋንና መዋቅራዊ ድጋፍ ያለው የጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ሥርዓትና የክልል አወቃቀር መዘርጋቱን ያነሳሉ፡፡ በዚህም በተለይ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍል የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች በማንነታቸው ብዙ ግፍና መከራን ተቀብለዋል፡፡
የአማራን ስነልቦና በማዳከም የበላይነትን የመያዝ ሕልም ይዞ የተነሳው ጽንፈኛው የትህነግ ቡድን በስልጣን ዘመኑ በጉራፈርዳ፣ በምዕራብ ወለጋ፣ በመተከል፣ በቅርቡ ደግሞ በማይካድራ ዘር ተኮር ጥቃቶች እንዲፈጸሙ የነበራቸው የአጋፋሪነት ሚና ከትውልዱ አዕምሮ የማይፋቁ ማሳያዎች ናቸው፡፡ በተለይ የማይካድራው ዘር ተኮር ጭፍጨፋ የግዛት ማስፋፋትን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን መምሕር መዘምር አንስተዋል፡፡ ይሕም የሕዝብ አሰፋፈርን ለመለወጥ በአማራ ላይ ለዘመናት ሲፈጽመው የነበረው የመግደል፣ የማፈናቀል፣ የማሰቃዬት እንዲሁም አካላዊና ስነልቦናዊ ጉዳት አካል ነው ብለዋል፡፡
ለሩዋንዳው የዘር ፍጅት ከ1957 ጀምሮ ዝግጅት እንደተደረገው ሁሉ ትህነግ ገና ከምስረታው ጀምሮ አማራ በጠላትነት በመፈረጅ ከተነሳ በኋላ በስልጣን ላይ በቆየባቸው ዓመታት በጉራፈርዳ፣ በበደኖ፣ በመተከል፣ በምዕራብ ወለጋ እና በሌሎችም አካባቢዎች በአማራ ላይ ግድያ ፈጽሟል፡፡ ትህነግ በወልቃይትና አካባቢው በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አማራዎችን ሲገድል ከ500 ሽህ የሚበልጡ ደግሞ እንዲፈናቀሉ አድርገዋል፡፡ አካዙ የተባሉ የሁቱ ፅንፈኞች በቱትሲዎች ላይ እንደፈጸሙት ግፍ ሁሉ ትህነግ ሳምሪ የተሰኘ ህገወጥ ቡድን በማደራጀት በማይካድራ ንፁሃን ላይ አሰቃቂ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈፅሟል፡፡
የወራሪው፣ ተስፋፊውና አሸባሪው የትህነግ ቡድን ከ‘ሳምሪ’ የወጣቶች አደረጃጀት በተጨማሪ ታጣቂዎችንና የፖሊስ አካላትን በማሳተፍ ጭምር ዜጎችን ገድሏል፡፡
የዘር ማጥፋት ወንጀልን ለመከላከልና ሃገራት ይህንን ታሳቢ ያደረገ ጠንካራ የቅጣት ሕግ እንዲኖራቸው የወጣውን የ1948 ስምምነት ኢትዮጵያ በ1949 አጽድቃለች፤ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጓም እንደየሁኔታው የሚለያይ ቢሆንም ከአምስት ዓመት እስከ እድሜ ልክ የሚያስቀጣ አድርጋለች፡፡ ይሁን እንጂ ተግባራዊ ከማድረግ ይልቅ ለዘር ተኮር ጥቃቱ መዋቅራዊና ስልታዊ ድጋፍ አግኝቶ ተተግብሯል፡፡ ይህም ሰብዓዊ ቀውስ፣ ፖለቲካዊ ኪሳራ፣ ኢኮኖሚያዊ ማሕበራዊና ስነልቦናዊ ጫና አሳድሯል፡፡ አሁንም ማስቆም ካልተቻለ የባሰ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ሃገሪቱ ያጸደቀችውን ዓለም አቀፍ ስምምነት መተግበር እንዳለባት መክረዋል፡፡
መንግሥት ለሕዝቡ አስተማማኝ የሕግ ከለላ ሊያደርግ ይገባል፡፡ መሰል ድርጊት እንዳይፈጸም ወንጀሉን በመሩና በፈጸሙ አካላት ላይ አስተማሪ ርምጃ መውሰድ ይገባል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሕዝቡ እንደዚህ አይነት ድርጊቶችን በንቃት መከታተልና መከላከል እንደሚኖርባቸውም መክረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleያልተቀበረ ሞት፤ ያልተለቀሰለት ሃዘን!
Next articleለአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት እድገት አስተዋፅኦ ያበረከቱ መሪዎች ተሸለሙ፡፡