ያልተቀበረ ሞት፤ ያልተለቀሰለት ሃዘን!

641

ባሕር ዳር፡ ኅዳር 29/2013 ዓ.ም (አብመድ) የችግሩ ፅንሰት ‹‹የደርግ ወታደር›› ከሚለው የተንሸዋረረ ስያሜ ይጀምራል፡፡ ለእናት ሃገሩ ዘብ የቆመ የአንድ ሃገር ወታደር እንዴት በሥርዓት አራማጆች ስያሜ ተጠራ ቢባል ከሴራ የዘለለ ቀናዔ ምላሽ አይኖረውም፡፡ የፀናውን መናድ የነበረውን ማፍረስ መታገያው ያደረገው ትህነግ ላለፈው ስህተት ይቅርታ ለቀደመው ጥረት እውቅና የመስጠት እንጥፍጣፊ ሞራል አልነበረውም፡፡ በመጨረሻ የክፋቱን ጥግ ያሳየው ይህ ህገወጥ ቡድን ከጂምሩ የቀደመውን ሁሉ ዐይንህን ላፈር ማለት እና ሁሉንም ከምንም ለመጀመር መታበይ ዋና ተግባሩና ባህሪው ነበር፡፡

ወጣቱ ረዳ በለው መረሳ በ102ኛ የአየር ወለድ ክፍለ ጦር 7ኛ ብርጌድ 72ኛ ሻለቃ አየር ወለድ ሆኖ በዘመነ ደርግ ሃገሩን ለሦስት ዓመታት በውትድርና አገልግሏል፡፡ ገና በልጅነት እድሜው ለብሔራዊ ውትድርና የዘመተው አየር ወለዱ ረዳ ከሦስት ዓመታት የኤርትራ በርሃ ወታደራዊ ግልጋሎት በኋላ በጉልበቱ ላይ በደረሰ ጉዳት በጡረታ ከሰራዊቱ ተሰናብቶ ወደትውልድ ቀየው አላማጣ ተመለሰ፡፡ ረዳ ወደ ትውልድ ከተማው ከተመለሰ በኋላ ለአንድ ዓመት ያክል የእናቱ ጎረቤት ሆኖ እና የንግዱን ዓለም ተቀላቅሎ ህይዎትን በአዲስ መምራት ጀምሮም ነበር፡፡

ረዳ በአንድ ዓመት የትውልድ ቀየው ቆይታ ትዳር ይዞ ወንድ ልጅ ወለደ፡፡ ህፃኑ በተወለደ በ40ኛ ቀኑ ቅባ ቅዱስ ሲቀምስ የረዳ ህይዎት ያልታሰበ እና አስደንጋጭ ክስተትን በምሽት አስተናገደ፡፡ አካባቢውን ከደርግ ከተቀበለ ዓመት ያልሞላው ትህነግ የኢትዮጵያ አየር ሃይል በተደጋጋሚ ባደረሰው የአየር ድብደባ ረዳን በማያውቀው ነገር ወነጀለው፡፡ ረዳ ከሦስት ጓደኞቹ ጋር ለአየር ኃይል መረጃ በመስጠት እያስደበደባችሁን ነው በሚል ውንጀላ በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡

ስለተወነጀሉበት ጉዳይ ምንም ነገር የማያውቁት ረዳ እና ጓደኞቹ ከዛሬ ነገ የፍትህ ብርሃን ትወጣልናለች ብለው ቢጠብቁም ፍትህ በባለጊዜዎች ተዳፍና ወደ ኮረም ለእስር ግዞት ወሰዷቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር ፍትህ ተስፋ አልባ መሆኗን የተረዱት የረዳ ጓደኞች ከእስር አምልጠው የተሰወሩት፡፡ በውትድርና ዘመኑ በጉልበቱ ላይ ጉዳት የደረሰበት ረዳ ግን ያነክስ ነበርና ሩጦ ማምለጥ እንደማይችል ሲረዳ ባለበት ተቀመጦ የሚመጣውን ሁሉ ለመቀበል ተዘጋጀ፡፡ ክፉውን ዘመን በሽሽት ካመለጡት ሦስት የረዳ ጓደኞች ውስጥ ሁለቱ ከጊዜ በኋላ አላማጣ ተመለሱ፤ ረዳን የበላው ጅብ ግን ፈፅሞ አልጮህ አለ፡፡

ልጃችንን ወዴት አደረሳችሁት? እያሉ የሚጠይቁት እናቱ ወይዘሮ ዙፋን ታረቀኝ እና ቤተሰቦቹ ከባለጊዜዎቹ የሚያገኙት ምላሽ ‹‹የእጁን አግኝቷል›› የሚል እብሪት ሆነ፡፡ ‹‹ሞቶም ከሆነ እንደሃገር አልቅሰን እርማችን እናውጣ፤ በህይዎት ካለም እንወቅ›› የሚሉት የረዳ ቤተሰቦች ተደጋጋሚ ውትዎታ በትህነግ አንጃዎች ጥርስ ውስጥ አስገባቸው፡፡ ተደጋጋሚ ዛቻ፣ የማያባራ ማስፈራሪያ፣ አስተዳደራዊ መገለል እና ወከባ በጥያቄው ለመግፋት የህልውና ስጋት ከፊታቸው ደቀነ፡፡

ታናሽ ወንድሙ በወንድሙ ረዳ የውሃ ሽታ መሆን አንገቱን የደፋው ሳያንሰው ሹማምንቱ ሰበብ እየፈጠሩ ያሸማቅቁታልና ጥቃቱ የእርግ እሳት ሆነበት፡፡ የገፈኞቹ ልክ ያጣ ብልግና ወንድማችሁን የት እንዳለ እናሳያችኋለን በሚል ፌዝ ጉዳታቸው ሳያንስ ገንዘብ ከረዳ ታናሽ እህት ተቀበሉ፡፡ ባገኙት ሰበብ ሁሉ ስለልጃቸው የሚያለቅሱት እናት ዙፋን የልጃቸውን ስም ጠርቶ ማልቀስ ተጨማሪ ዋጋ የሚያስከፍላቸው ድፍረት ተደርጎ ተቆጠረ፡፡ ሞተ ብለው እንዳያለቅሱ መረጃውን የት አገኘሽው? የሚለው የካድሬዎች ጥያቄ መዘዙ ብዙ ነው፡፡ ልጃቸው በህይዎት አለ ብለው እንዳያስቡ ከ30 ዓመታት በላይ መጠበቅ ከሰዋዊነት የወጣ ሆነባቸው፡፡

የአብራክ ክፋይ ልጃቸውን ሞት አልቅሶ እርምን ማውጣት ብርቅ የሆነባቸው እናት ዛሬ ቀን ሲወጣ ፎቶውን ከሳጥን አውጥተው ታቅፈውት ይውላሉ፡፡ ‹‹ለሃገር ማገልገል ወለታው ይሄ ነው!›› የሚሉት እናት ዙፋን አንጀታቸው ሲያር ለዓላማ መሞት የማያውቅ ወንበዴ የሰው ልክ የለውም ይላሉ፡፡ አየር ወለዱ ረዳ በለው ያልተቀበረ ሞትን፤ እናት ዙፋን ታረቀኝ እና ቤተሰቦቹ ደግሞ ያልተለቀሰለትን ሀዘን ለ30 ዓመታት በጉያቸው ታቅፈዋል፡፡ ልጃቸው በህይዎት ይኖራል የሚል ተስፋ የሌላቸው ወይዘሮ ዙፋን በደሌን የኢትዮጵያ ህዝብ ይወቅልኝ፤ ውጋቴን የኢትዮጵያ እናቶች ይስሙልኝ ይላሉ፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው -ከአላማጣ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleበመተከል ላይ እየተፈጸመ ያለው ግፍ እንዲቆም ከፌዴራል መንግስት ጋር በቅንጂት እየተሰራ መሆኑን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ፡፡
Next articleሳምሪ የማይካድራዎቹ አካዙ !