
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 29/2013 ዓ.ም (አብመድ) ባለፉት 27 ዓመት በነበረው የንግድ ሥርዓት የህወሓት ጁንታው ንብረት የሆኑ ድርጅቶች ባልተገባ መልኩ ተወዳዳሪ የሚያደርጋቸውን ድጋፍ ያገኙ ነበር፤ ይህም እኩል የሆነ የተሳትፎ እድል እንዳይኖር ሲያሰረግ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
በተለይ ባለፉት 27 ዓመታት የነበረው ሃገራዊ የኢኮኖሚ ሥርዓት ፍትሐዊ ተሳትፎ ያላቸው የንግድ ድርጅቶች እንዲፈጠሩ ምቹ ሁኔታ አልፈጠረም ይላሉ አቶ ክቡር ገና።
ጉዳዩ ዛሬ እንደ አዲስ ይነሳ እንጂ በጉዳዩ ላይ ብዙ ተብሏል፡፡ ለሕዝብም አዲስ ነው ብለው እንደማያምኑና እርሳቸው ቀድሞ የንግድ ምክር ቤት በአሁኑ ደግሞ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ተብሎ በሚጠራው ተቋም ፕሬዝዳንት ሆነው ሲያገለግሉ በማህበራቸውም ሆነ በተለያየ አጋጣሚ ሁሉ ለግሉ ዘርፍ ከአድሎ ነጻ የሆነ አሰራር እንዲኖር ክፍተቶችን በማሳየት ብዙ ርቀት መሄዳቸውን አስታውሰዋል። ሰሚ ባለመኖሩ እኩል ተሳትፎ ሳይፈጠር ቆይቷል ነው ያሉት፡፡
ለንግድ ድርጅቶች መቋቋም ዋና መሰረቱ አድሎ የሌለበት ምቹ አሰራር መዘርጋት እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ክቡር፤ የትህነግ (ህወሓት) ጁንታ ቡድን ንብረት የሆኑ ድርጅቶች ባልተገባ መልኩ ተወዳዳሪ የሚያደርጋቸውን ድጋፍ ያገኙ እንደነበር አመላክተዋል።
በቦርድ ስም የሚሰየሙ የመንግሥት ኃላፊዎች እነዚህ የንግድ ድርጅቶች፣ መረጃ እንዲያገኙ፣ ከባንክ በፈለጉ ጊዜ መበደር እንዲችሉ፣ ብድር በወቅቱ ለመመለስ እንዳይገደዱ የሚያደርግ አሰራር የተዘረጋበት ሥርዓት እንደነበር ገልጸዋል። ይህ አይነቱ አሰራር ለብዙዎች አዲስ እንዳልሆነና ሲተችም እንደነበር ያመለከቱት አቶ ክቡር ፣ ይህም የግሉን ዘርፍ ክፉኛ እንደጎዳውና ከውድድር እንዳስወጣው አስታውቀዋል።
የንግዱ ማኅበረሰብ ከራሱ አልፎ ለሃገርም ሚናውን እንዲወጣ ከተፈለገ ፍትሐዊ አሰራርን ማስፈን እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
በችግሮች ዙሪያ በተለያዩ ወቅቶች በሚመቻቹ መድረኮች ማህበሩ የሚሰጣቸው ምክረ ሀሳቦች ተቀባይነት እንደሌላቸውና የሚደመጥም እንዳልነበር ያመለከቱት አቶ ክቡር አንዳንዶች ከሚፈልጉት ጋር ተነጋግረው ባሻቸው መንገድ ጉዳያቸውን ማስጨረስ የሚችሉበት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ማኅበራትም ሆኑ መንግሥታት ሚናቸው የንግዱ ማኅበረሰብ ፍትሀዊ በሆነ መንገድ ለክፍተቶች መፍትሄ መስጠት እንደሆነ ጠቁመው ባለፉት 27 ዓመታት ይህ ሲሆን አልታየም ፤ የንግድ ድርጅቶች ባልተገባ መንገድ ከውድድር ውጪ መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡ የንግድ ድርጅቶች ከማነቆ የተላቀቁ አለመሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡ የዘገበው የኢትዮጵያ ፕረስ ድርጅት ነው፡፡