‹‹ልጆቻችሁን ያርዳል፣ ከብቶቻችሁን ይነዳል፣ እምነት እና መሬት ይነጥቃል የተባለው ጦር ከተነገረለት በተቃራኒ ቆሞ አገኘነው›› የኦፍላ ወረዳ አርሶ አደሮች

331

ባሕር ዳር፡ ኅዳር 29/2013 ዓ.ም (አብመድ) ኮረምን በግራው አላማጣን በቀኙ አድርጎ መካከል ላይ በኩራት እና ግርማ ሞገስ የተሰየመ ጠመዝማዛ ተራራ ነው፤ ግራ ካሶ፡፡ ግራ ካሶ ታሪኩ ከግርማ ሞገሱ ይገዝፋል፡፡ የግራ ካሶ ታራራ ኮረም ላይ ሆኖ ላየው ደጀን አላማጣ ሆኖ ለተመለከተው ደግሞ ውበት ነው፡፡

ግራ ካሶ በ1980ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ለአምስት ቀናት እልህ አስጨራሽ ጦርነት ተካሂዶበታል፡፡ በእድሜ የገፉ የአካባቢው ነዋሪዎች ስለዛ ዘመን መናገር ቀርቶ ማሰብ እንኳን አይፈልጉም፤ ያሳለፉትን መከራ ያውቁታልና፡፡ ኦፍላ ጥንታዊት የወሎ ጠቅላይ ግዛት የዋግ አውራጃ አንድ ወረዳ ነበረች፡፡

አሁን በዚህ ሰሞን የጦርነት ነጋሪት ይዞ ሲጎስም የባጀው የትህነግ አንጃ ለድል ከተመካባቸው የጦር አውድማዎች መካከል ግራ ካሶ አንዱ ነበር፡፡ ይመጣል ያለውን ጦር እንደፎከረው በአማራ መሬት ላይ ለመደምደም ግራ ካሶ ቁልፍ ቦታ ተደርጎም ተወስዷል፡፡ በእርግጥ መቀሌን ለመያዝ ከተከፈለው ዋጋ ይልቅ ግራ ካሶን ለማስለቀቅ የነበረው ትንቅንቅ እልክ አስጨራሽ ነበር፡፡

ያንን ጠመዝማዛ ተራራ እንደ ፍልፈል በየቦታው ጭሮ ምሽግ የቆፈረው ወራሪው፣ ተስፋፊውና አሸባሪው ትህነግ እንዳለመታደል ሆኖ ያ ሁሉ ጥረቱ ወደ መቃብር ከመውረድ ግን አልታደገውም፡፡ ያውም በዚህ ዘመን መሰረተ ልማት እንደሚሰራ መንግስት ዶዘር እና ኤክስካቫተር ወደተራራው ጫፍ አስገብቶ ምሽግ የቆፈረው ህገ-ወጡ ቡድን በሽሽቱ ዋዜማ ደግሞ በአሳፋሪ ሁኔታ አስፓልት ቆርጦ እና አፈራርሶ ምሽጉን ለቀቀ፡፡ 10 ዓመታትን ያዋጋል የተባለለት ምሽግ በጥምር ጦሩ ዶግ አመድ ሆነ፡፡ የአማራ ልዩ ኃይል ጀብዱ ግራ ካሶ ተራራ ላይ በድል ብስራት ህብረ ዝማሬ ተደመደመ፡፡ ዛሬ የግራ ካሶ ተራራ እና አካባቢው ወደሰላማዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ከገቡ ቀናት አልፈዋል፡፡

ለመሆኑ ትህነግ ምን በሚል ፕሮፖጋንዳ ነበር ሚሊሻውን የሰበከችው? ስንል በአካባቢው ነዋሪ የሆነ አንድ ሚሊሻ አነጋገርን፡፡ ሚሊሻ ታደሰ ምስጉን በግራ ካሶ ቆንጮ ላይ ከምትገኘው ጽሊያ አካባቢ ነዋሪ ነው፡፡ ትህነግ መሳሪያ እና 15 ጥይት ሰጥታ ወደጦርነቱ ልታሰማራው ስትዘጋጅ መሳሪያውን፣ ስድስት ልጆቹን እና እመጫት ባለቤቱን ይዞ ወደሃውላ ተራራ እና ገና ማሪያም ጫካ ሸሸ፡፡

ከማን ጋር ነው የምንዋጋው? ለሚለው ጥያቄው በቂ መልስ ያላገኘው ሚሊሻ ታደሰ እንደሰይጣን ከፍቶ በምዕናብ ከተሳለው ጦር ጋር ከሚጋፈጥ ሽሽት አማራጭ ነው ብሎ አሰበ፡፡

ሚሊሻ ታደሰ ከአምስት ቀናት የጫካ ውስጥ ሽሽት በኋላ ወደቀየው ሲመለስ የአማራ ልዩ ኃይል አካባቢውን ተቆጣጥሮት አገኘ፡፡ ሚስቶቻችሁን ይደፍራል፣ ልጆቻችሁን ያርዳል፣ ከብቶቻችሁን ይነዳል፣ እምነት እና መሬት ይነጥቃል የተባለው ጦር ከተነገረለት በተቃራኒ ቆሞ ባለቤቶቻቸው ጥለዋቸው የሸሹ ከብቶች በረት ውስጥ ታጉረው ተገኙ፡፡

ማንነቱን ተጠየቀ፤ ሚሊሻ እንደነበረ መለሰላቸው፤ ከትህነግ የተቀበለውን መሳሪያ እንዲያስረክብ ጠየቁት፤ አንድ መሳሪያ እና 15 ጥይት አስረከበ፤ ዛሬ ከከብቶቹ ጋር በግራ ካሶ ተራራ ከእኛ ጋር በድንገት ተገናኘን፤ አካባቢው ወደሰላማዊ እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ መግባቱንም ነገረን፡፡

ሌላው አስተያየት ሰጭ አቶ ሃብቶም ረዳ በግራ ካሶ ተራራ ውስጥ የነበረውን የከባድ መሳሪያ የተኩስ ልውውጥ ሲሰሙ ነበር ቤተሰባቸውን ይዘው አካባቢውን ለቆው በሽሽት ቀናትን ያሳለፉት፡፡ ‹‹እግዚያብሔር ይመስገን ምህረቱ በጎ ነው›› ያሉን አቶ ሃብቶም እንደአጀማመሩ እና ትህነግ እንደነገረቻቸው ጦርነቱ በአጭር ተጀምሮ በአጭር የሚጠናቀቅ አልመሰላቸውም ነበር፡፡ ጦርነቱ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ ተጠናቋል ያሉት አስተያየት ሰጭ ከሽሽት መልስ ከቤተሰባቸው ጋር ጤፍ እየወቁ ነበር ያገኘናቸው፡፡

አቶ ሃብቶም አሁን ላይ ከሐይማኖት አባቶች፣ ከሃገር ሽማግሌዎች እና ከአካባቢው ነዋሪ ጋር ውይይት ተደርጎ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ተጀምሯል ብለውናል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው -ከኮረም

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous article“ደስታን ለመግለፅ ተጨማሪ ህይወትን መቅጠፍ፣ የህዝብን እንቅልፍ መንሳትና ንብረትን ማውደም አያስፈልግም” ምክትል ኮሚሽነር ሙሉ ሁነኛው
Next article“ባለፉት 27 ዓመታት በንግዱ ዘርፍ እኩል የሆነ የተሳትፎ ዕድል አልነበረም ” አቶ ክቡር ገና የአፍሪካ ንግድ ምክር ቤት ሥራ አስኪያጅ