
“ደስታን ለመግለፅ ተጨማሪ ህይወትን መቅጠፍ፣ የህዝብን እንቅልፍ መንሳትና ንብረትን ማውደም አያስፈልግም” ምክትል ኮሚሽነር ሙሉ ሁነኛው
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 28/2013 ዓ.ም (አብመድ) በግፍ እና በበደል አስተዳደር ለዘመናት በጭቆና ቀንበር ስር የቆየ ማኅበረሰብ የተጫነው ቀንበር ሲነሳለት ምን እንደሚሰማው መገመት አያዳግትም፡፡ ከ40 ዓመታት በላይ ከማህፀኑ የወጣ የራሱን ህዝብ ጨምሮ የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ደም እንደ ባሕር ውኃ ሲያፈስ የነበረው ተስፋፊው፣ ወራሪውና አሸባሪው ትህነግ በዕድሜ ዘመኑ የሠራው ግፉ አንሶት በመቀበሪያው ሰዓት እንኳ እሜያቸው ለትጥቅ ያልበቁ ህፃናትን ህይወት እንዲገብሩ ዳርጓቸዋል፡፡
እንዲህ አይነቱ አሸባሪ፣ አረመኔና የሰው ፍጡር የማያደርገውን ያደረገ ትህነግ ተቀበረ ሲባል በእርግጥ ደስታን መቆጣጠር ሊከብድ ይችላል፡፡ ወይዝሮ ፀገነት ገዳሙ የሚኖሩት በባሕር ዳር ከተማ ነው፡፡ የሀገር መከላከያ ሰራዊት የጁንታው መቀመጫ የሆነችውን የመቀሌ ከተማን ሲቆጣጠር በባሕር ዳር ከተማ ከጦርነት ባልተናነሰ መልኩ የተኩስ ድምፅ በመሰማቱ እንቅልፋቸውን አጥተውና ተረብሸው እንዳደሩ ተናግረዋል፡፡
ደስታን ለመግለፅ ተብሎ የተተኮሰው ጥይት አዳራቸውን በጩኸት ከመረበሹም በላይ ለሰው ህይወት መጥፋት ምክንያት መሆኑንም ሰምተዋል ታድያ “በጦር ሜዳ ህይወት መጥፋቱ ሳያንስ እዚህ ደግሞ ደስታን ለመግለፅ ሲባል ለምን የሰው ህይወት ይጠፋል?” ያሉት ወይዝሮ ፀገነት መንግሥት ህግና ሥርዓትን ማስጠበቅ አለበት ብለዋል፡፡
አቶ አለማየሁ መንግሥቴ ደግሞ ትናንት የጁንታው መሪ ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በቁጥጥር ስር ዋለ ተብሎ ሲወራ በጥይት ድምጽ የህዝብን ሠላም ለማወክ ጅማሮ እንደነበረ ተናግረዋል፡፡ በእኔ አካባቢ ያሉ ሰዎች በተኩስ ህዝብን እንዳይበጠብጡ በመምከር እና በመለመን እንዳይተኩሱ አድርጌያለሁ ያሉት አቶ አለማየሁ ሁሉም ማኅበረሰብ ድስታን በተኩስ ከመግለፅ ሊቆጠብ ይገባል ብለዋል፡፡
ኅዳር 19/2013 ዓ.ም የሀገር መከላከያ ሰራዊት መቀሌን መቆጣጠሩ ሲሰማ መላው የኢትየጵያ ህዝብ ደስታውን አሰምቷል፣ በአማራ ክልል በሚገኙ ከተሞችም ህዝቡ ደስታውን ገልጿል፡፡
ይሁንና ደስታቸውን ለመግለጽ ጥይት የተኮሱም ነበሩ ታድያ ይህ በጥይት ደስታን መግለፅ ለሰው ህይወት መጥፋትና ለአካል መጉደል ምክንያት መሆኑን ነው የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ ወንጀል መከላከልና ትራፊክ ምክትል ዘርፍ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ሙሉ ሁነኛው የገለጹት፡፡
ጁንታውን መቆጣጠር የሚያስደስት ቢሆንም ደስታን በተኩስ መግለጽ ወንጀል እና በሕግ የሚያስጠይቅ በመሆኑ ሕገ ወጥ ሰዎች ከመሰል ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ኮሚሽነር ሙሉ ሁነኛው አሳስበዋል፡፡
“የጥይት ድምጽ የሚውለው ለደስታ ሳይሆን ለጦርነት ነው:: ደስታን ለመግለፅ ተጨማሪ ህይወትን መቅጠፍ፣ የህዝብን እንቅልፍ መንሳትና ንብረትን ማውደም አያስፈልግም” ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ ማንኛውንም ደስታ ለመግለጽ ጥይት መተኮስ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡
ደስታን በተኩስ ለመግለጽ የሚሞክሩ ሰዎች ካሉ ኮሚሽኑ በተቀመጠው ሕግ መሰረት ተጠያቂ እንደሚያደርግ ምክትል ኮሚሽነር ሙሉ ሁነኛው አስጠንቅቀዋል፡፡
ዘጋቢ ፡- ብሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ