‹‹ከሃገር በላይ ክብር የለምና ሞቴን መርጨ ወደ ሚሳኤል ማስወንጨፊያው ግዳጅ አልገባም አልኳቸው›› ሻለቃ ዘላለም ብዙነህ

454

‹‹ከሃገር በላይ ክብር የለምና ሞቴን መርጨ ወደ ሚሳኤል ማስወንጨፊያው ግዳጅ አልገባም አልኳቸው›› ሻለቃ ዘላለም ብዙነህ

ባሕር ዳር፡ ኅዳር 28/2013 ዓ.ም (አብመድ) ወታደር ለሃገር ክብር ዘብ፣ ለሕዝብ ፍቅር መስዋዕት እና ለቃል ኪዳን ፅናት የሚከፈልለት ሙያ ነው፤ ወታደር ሃገር እንጂ ብሔር የለውም፤ ወታደር የሃገር መሃል ገነት እንዲሆን ዳር ድንበሩን በእሳት የሚያጥር መከታ ነው፤ ወታደር ስለተከፈለው ሳይሆን ሀገር ስላለው ብቻ ህዝብን የሚያገለግል የሉዓላዊነት ዘብ ነው፤ ወታደር ሲኖር ቤት የለውም፤ ሲሞት መቃብሩ አይታወቅም፤ ወታደር ከመለዮው በላይ ቀኝ አጁን ከፍ አድርጎ ቃለ መሀላ ሲፈፅም ያኔ ህይዎቱ ከፍላጎቱ ውጭ ለሕዝብ ደኅንነት እና ለሀገር ክብር ሲባል ተላልፎ ተሰጥቷል፡፡
ሻለቃ ዘላለም ብዙነህ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ውስጥ አባል ከሆነ ሁለት አስርት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ በዚህ ወቅትም በኢትዮጵያ አየር ሃይል ሰሜን ምድብ የአየር መከላከል እቅድ እና ስልጠና ቡድን መሪ ሆኖ እያገለገለ ነው፡፡ የአየር ሃይል ሰልጣኞችን ያስተምራል በሙያው የተካኑ ተኪዎችንም ያፈራል፡፡ የኢትዮጵያን የአየር ሃይል የበላይነት ማስጠበቅ፣ ለምድር ሃይሉ ሽፋን መስጠት እና ከጥቃት የመከላከል ኃላፊነት ለሻለቃ ዘለላም ብዙነህ እና ጓዶቹ ሃገር የሰጠቻቸው ግዳጅ ነው፡፡
ብሔር ሳይሆን “ሃገር አለኝ” ብሎ የሚያምነው ሻለቃ ዘላለም ለዓመታት ሙያውን አክብሮ ከትውልድ ቀየው ርቆ እየሰራ ነው፡፡ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በአሸባሪው ትህነግ ቡድን የተፈፀመውን ክህደት የሰማውም በመኖሪያ አካባቢያቸው መዝገብ እየተገለጠ፣ ብሔር እየተጠቀሰና እየታደኑ ሲታሰሩ ነበር፡፡
ክብር ባለው ሙያ ለሃገሩ ክብር እድሜ ዘመኑን የገፋው ወታደር ክብረ ነክ ስድቦችን እያስተናገደ ለአራት ተከታታይ ቀናት ባዶ ሲሚንቶ ወለለል ላይ ውሎ እንዲያድር ተገደደ፡፡ የኢትዮጵያ አየር ሃይልን ጠንካራ፣ ተደጋጋሚ እና ዒላማውን የጠበቀ ምት መቋቋም የተሳናቸው እና ድንብርብራቸው የወጣው የጁንታው ቡድን አባላት ሲጨንቃቸው መላ ዘየዱ፡፡
በተለያየ አቅጣጫ እስከ 25 ኪሎ ሜትር ጥቃት አድራሾቹን ሚጎች በሚሳኤል መትቶ ለመጣል ወሰኑ፡፡ ዳሩ የዘረፉት መሳሪያ እና ገንዘብ እንጂ ሙያዊ ክህሎቱ በበላይነት የኖሩበትን ዘመን ያክል ያልነበራቸው የጁንታው አባላት ሙከራቸው ሁሉ እንዳልተሳካላቸው ያጫወተን ሻለቃ ዘላለም በመጨረሻም ግዳጅ ውስጥ ግባ ተባለ፡፡
ሚሳኤል አስወንጭፎ የጦር አውሮፕላኖችን እንዲጥል ትዕዛዝ ተሰጠው፡፡ በተደጋጋሚ እየተዘዋወሩ አርዕድ አንቀጥቅጥ ምቶችን የሚያዘንቡትን የጦር ጀቶች ሚሳኤል አስወንጭፎ እንዲመታ ታዘዘ፡፡ “ከሃገር በላይ ክብር የለምና ግዳጅ አለመቀበሌ የሚያስከትለውን ባውቅም ሞቴን መርጨ አልገባም አልኳቸው” አለ ሻለቃ ዘላለም፤ እምቢታውን ተከትሎ ከአሸባሪው መሪዎች የተሰነዘረበትን ክብረ ነክ እና ፀያፍ ስድብ፣ ዘለፋ እና ዛቻ በተሰበረ ልብ ሲናገረው እምባ ይተናነቀዋል፡፡
ለተደጋጋሚ ጊዜ ሞሶቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ አካባቢ ወዳለው የሚሳኤል ማስወንጨፊያ ጣቢያ እንዲገባ የተለመነው ታማኝ ወታደር በእምቢታው ሲፀና ተደጋጋሚ ድብደባዎችን አስተናገደ፡፡ ከዱላው በላይ የሚያመው ግን ለደብዳቢዎች ትዕዛዝ የሚሰጡት የሙያ አጋሮቹ ሲሆኑ ትዕዛዝ ፈፃሚዎቹ ደግሞ የሚሊሻ አባላት መሆናቸው ነው፡፡
“በትግል ሜዳ ወድቆ የተነሳ ለሃገር እና ሕዝብ ክብር ራሱን አሳልፎ የሰጠ ሻለቃ በተራ ሚሊሻ መደብደብ ያማል” ሲል የግፋቸውን ጥግ ገልጿል፡፡ ከድብደባው ሳይርቁ፣ በአይነ ቁራኛ ሲከታተሉ እና ስቃይ ሲፀናበት ግዳጁን ይወጣል ያሉት ሻለቃ የመጣውን ሁሉ እንዳመጣጡ እየተቀበለ በሃገር ፍቅሩ ጸና፤ ከሃገር ሚዛን ሳይጎድል እና ሃገሩን ሳይክድ ያልፋል ያላለው መከራ ያልፍ ዘንድ እንደተመኘው መቀሌ በመከላከያ ሠራዊት ቁጥጥር ስር መዋሏን ተከትሎ አሳዳጆቹ ተሳዳጆች ሲሆኑ በህይዎት ኖሮ ማየት ቻለ፡፡ ያሳለፈው ስቃይ መራር፣ የልብ ስብራቱ ጠሊቅ ቢሆንም ለ20 ዓመታት የታገለለትን ዓላማ በስህተት ሳይደመድም “ነገ ለኢትዮጵያ የተሻለ ቀን ይሆናል” አለን፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው – መቀሌ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበኩር ጋዜጣ ኅዳር 28/2013 ዓ/ም ዕትም
Next article“ደስታን ለመግለፅ ተጨማሪ ህይወትን መቅጠፍ፣ የህዝብን እንቅልፍ መንሳትና ንብረትን ማውደም አያስፈልግም” ምክትል ኮሚሽነር ሙሉ ሁነኛው