
ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ኢንጂነር አክሱማዊት አብርሃ በጎንደር ከተማ በ1 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር የመማሪያ ህንጻዎች አስገንብተው አስመረቁ።
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 27/2013 ዓ.ም (አብመድ)
በጎንደር ከተማ በቀይ አምባ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ኢንጂነር አክሱማዊት አብርሃ በ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነቧቸውን ሁለት ብሎክ የመማሪያ ህንጻዎች ዛሬ አስመረቁ፡፡
ኢንጂነሯ በውጪ ሀገር የሚገኙ የአካባቢው ተወላጆችን በማስተባበር በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ የመማሪያ ብሎኮቹን ገንብተው ማስረከባቸውን ተናግረዋል።
በመጪው የካቲት ወር በከተማው በሚገኙ ሌሎች ሁለት ትምህርት ቤቶች ውስጥ የመማሪያ ህንጻዎችንና ቤተ-መጻህፍት በመገንባት ደረጃቸውን ለማሻሻልም ቃል ገብተዋል፡፡
የጎንደር ከተማ ከንቲባ ሞላ መልካሙ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፤ የከተማ አስተዳደሩ በዚህ አመት የ45 ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል አቅዶ በአምስቱ የማስፋፊያ የግንባታ ስራ ጀምሯል።
ኢንጂነር አክሱማዊት የተማሩበትን ትምህርት ቤት በማስታወስ ተነሳሽነቱን ወስደው የቀድሞ ተማሪዎችን በማስተባበር ላደረጉት አስተዋጽኦ አመስግነዋል።
የቀይ አምባ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር አቶ ምህረት ይመር “ኢንጅነሯ በእንጨትና ጭቃ የተሰሩ የመማሪያ ክፍሎችን ደረጃ በማሻሻል ለተማሪዎች ምቹ የትምህርት አካባቢ መፍጠር ችለዋል” ብለዋል።
የተገነቡት ሁለት ብሎኮች በአንድ ፈረቃ 400 ተማሪዎችን የማስተናገድ አቅም እንዳላቸው ጠቅሰዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ለትምህርት ቤቱ የህንጻ ግንባታ መሳካት አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦች የእውቅና ምስክር ወረቀት የሰጠ ሲሆን ለኢንጅነር አክሱማዊት ደግሞ የምስክር ወረቀትና የካባ ሽልማት አበርክቷል፡፡
ኢዜአ እንደዘገበው በ1974 ዓ.ም የተመሰረተው የጎንደር የቀይ አምባ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በከተማው ከሚገኙ አንጋፋ የመንግስት ትምህርት ቤቶች አንዱ ነው፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ