
የብፁዕ ዶክተር አቡነ ገብርኤል ስርአተ ቀብር ተፈጸመ።
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 27/2013 ዓ.ም (አብመድ)
የሲዳማ ጌዲዮ እና ቡርጂ ዞኖች አህጉረ ስብከትን በሊቀ ጳጳስነት ያገለገሉት ብፁዕ ዶክተር አቡነ ገብርኤል ስርአተ ቀብር በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጸመ።
በቀብር ስነ-ስርአቱ የአዲስ አበባ ከተማ አፈ-ጉባኤን ጨምሮ የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ብፁዕ ዶክተር አቡነ ገብርኤል ከካህን አባታቸው ከመምህር ገብረሕይወት እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ብርነሽ በወሎ ክፍለ ሀገር በዋግ አውራጃ በ1933 ዓ.ም እንደተወለዱ የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል።
የወሎ ክፍለ ሀገር ሊቀ ጳጳስ ከነበሩት ብፁዕ አቡነ ይሥሓቅ ማዕረገ ዲቁናን፣ በደብረ ሊባኖስ ገዳም ከቆሞስ ሊቀ ምርፋቅ ኤርሚያስ ሥርዓተ ምንኵስናን በ1958 ዓ.ም እንዲሁም ሥልጣነ ቅስናን ከወለጋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ በ1959 ዓ.ም ተቀብለዋል፡፡
መንፈሳዊ ትምህርታቸውን ከመጀመሪያ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ በአገር ውስጥና በውጪ አገር ተከታትለዋል።
በመንፈሳዊ እውቀታቸው በመምህርነትና በተለያዩ የሃላፊነት ቦታዎች አገልግለዋል።
የልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ በነበሩበት ወቅት በልዩ ልዩ ገዳማት የልማት ሥራዎችን አከናውነዋል፡፡
በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤት የመንፈሳዊ አገልግሎት መምሪያ መጋቤ ካህናት ሆነው ተሹመው ከፍተኛ አገልግሎት አበርክተዋል፡፡
ብፁዕ ዶክተር አቡነ ገብርኤል የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ኤጲስ ቆጶስ በመሆንም አገልግለዋል።
በኤርትራ፣ በድሬዳዋ፣ በደቡብ ሸዋ፣ በምዕራብ ሸዋ፣ በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም፣ በሰሜን አሜሪካ ሐዋርያዊ መንፈሳዊ አገልግሎት ሰጥተዋል።
በመጨረሻም የሲዳማ ቡርጂ እና ጌዲዮ ዞኖች አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመሆን ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
ብፁዕነታቸው ባደረባቸው ህመም ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ80 ዓመታቸው ዓርፈዋል።
ስርዓተ ቀብራቸው የእምነት አባቶች፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና የዕምነት ልጆቻቸው በተገኙበት ዛሬ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል። ዘገባወ የኢዜአ ነው::
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ