ሰይጣን ምድራዊ ተልዕኮውን ያጠናቀቀ ይመስላል!

892

ሰይጣን ምድራዊ ተልዕኮውን ያጠናቀቀ ይመስላል!

ባሕር ዳር፡ ኅዳር 26/2013 ዓ.ም (አብመድ)
ከተነገረው ያልተነገረው ይበዛል፣ አንዱ የክፋት ጥግ ሌላኛውን የተንኮል ድርጊት ያስንቃል፣ የፈፃሚው ሰው እኩይ ማንነት የግፍ በረዶ ተቀባዩን ብርታት ላየ ‹‹ላያስችል አይሰጥም›› የሚለውን የቀደምት አባባል ያፀናል፡፡ የግፍ ጥጉን ሁሉ ለሰማ ፈፃሚዎቹ ከሰማይ በታች ዓላማቸው ምን ውድ ነገር ቢሆን ነው እንዲህ ያስጨከናቸው? ያስብላል፡፡
በዓለም ላይ እልፍ አምባገነን መንግስታት ታይተዋል፡፡ የአገዛዝ ዘመናቸው ጭካኔ መገለጫ የሆኑ በዙ ጥፋቶችንም ፈፅመው አልፈዋል፡፡ ነገር ግን እጅ የሰጠን ሰው ታንክ በላዩ ላይ አልነዱበትም፡፡
ወራሪው፣ ተስፋፊውና አሸባሪው ወያኔ ግን ይህን ለሰሚው የሚዘገንን አረመኔያዊ ድርጊት በሰሜን ዕዝ 11ኛ ክፍለ ጦር ላይ ስለመፈፀሙ ከእሳት በተአምር የወጡ ወታደሮች ይናገራሉ፡፡ ምዕናባዊ ትርክት የነበረው ‹‹አኖሌ›› ተግባራዊ ሆኖ የሴት ወታደር ጡት ለመቁረጥ ቀነ ቀጠሮ ተይዞለትም ነበር፤ አሀዱ የልዩ ዘመቻዎች ኮማንዶ ቀድማ ባትደርስ ኖሮ፡፡
ዓመት ላልሞላው ህፃን ነፍሱ ላለፈ አስከሬን ሳይቀር ብሔር የሚሰጠው አሸባሪው ወያኔ ፅንፍ የወጣውን የብሔር ፖለቲካ ዳፋ የኢትዮጵያ ህያው ሉዓላዊነት መገለጫ ዘብ ለቆመው ወታደር ሳይቀር ሰጥቶ ለመከፋፈል ብዙ ተጉዟል፡፡
መከፋፈሉ በፈለገው ልክ አልሄድ ሲለው ደግሞ በአንድ ምሽግ አብሮ የተዋጋውን፣ አንድ አስቃጥላ ተካፍሎ የበላውን፣ ሲወድቅ ያነሳውን፣ በሰላም ጊዜ ለልማት በችግር ጊዜ ለጦርነት የተዘጋጀውን ወታደር ትጥቁን ፈትቶ በተኛበት በገዛ ጓደኛው ጥቃት ፈፀመበት፡፡
በበርካታ ቦታዎች በካፕ ውስጥ እያሉ ህይዎታቸው ያለፈው ወታደሮች ከጎናቸው ባለ ጓዳቸው እንደተሰው ቀሪዎቹ የዐይን ምስክር ሆነው ይናገራሉ፡፡
አስር አለቃ ቤተልሄም ቤዛ በሃገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ 11ኛ ክፍለ ጦር 2ኛ ብርጌድ 1ኛ ሻለቃ አባል ነች፡፡ አስር አለቃ ቤዛ ስለድርጊቱ ስትናገር ጦርነቱ በተዘጋጀ እና ባልተዘጋጀ፣ ግንዛቤ በተፈጠረለት እና ብዥታ ውስጥ ባለ፣ ቀድሞ ቦታ በያዘ እና ትጥቁን ፈትቶ በተኛ፣ በአግባቡ በተደራጀ እና በተበተነ፣ በየቀኑ ለሴራ በተሰባሰበ እና በየቀኑ ዋርድያ በሚውል እንዲሁም ለእኩይ ተልዕኮ በቆመ እና ለሃገር ዘብ በቆመ ወታደር መካከል የሚካሄድ ነበር ትላለች፡፡
ብሔርን መሰረት ያደረገ አፈንጋጭ አስተሳሰብ በአባሉ ውስጥ መታየት ከጀመረ ውሎ ቢያድርም እንዲህ አሳፋሪ ድርጊት ይፈፅማሉ ብሎ ያሰበ እንዳልነበር ነው ቤዛ የምትናገረው፡፡
ነገር ግን ያ ተዓምራዊ ሌሊት 5 ስዓት ከ30 ደቂቃ ገደማ ሲጀመር ወታደራዊ ከምፓቸውን የከበበው ሚሊሻ እና ልዩ ኃይል ከውጭ ሽፋን ሰጭ የራሳቸው ጓዶች ደግሞ ለቆሙለት እኩይ ዓላማ ሲሉ ጓዶቻቸውን የሚወጉ ሆነው ተገኙ፡፡ የተሰዋው ተሰውቶ በህይዎት ያሉ ወታደሮች ግን በጀግንነት ሲዋጉ አድረው ረፋዱ ላይ እጅ ስጡ ሲባሉ እጅ እንደማይሰጡ አረጋገጡ፡፡
አሸባሪው ወያኔ ለሴራ ተልዕኮ ማራማጃ ከደመና በታች የማይጠቀመው ነገር የለምና ረፋዱ ላይ የሐገር ሽማግሌዎችን እና የሐይማኖት አባቶች ያለቻቸውን ሰዎች ለድርድር ወደቦታው ላከ፡፡ በድርድሩም ወያኔ የሚፈልገው መሳሪያ ብቻ መሆኑን ጠቅሳ ከወታደሩ ጋር ጠብ የለኝም የሚል መልዕክት ጨምሮ ላከ፡፡
በአራቱም አቅጣጫ የተከበቡት እነዚህ ጀግኖች ከሚፈላባቸው የጠይት በረዶ ሌላ ውሃ ጥም እና ርሃብ ፈትኗቸዋል፡፡ ነገር ግን ለሃገራቸው የገቡትን ቃል አስበው በሃገራቸው አንደራደርም አሉ፡፡ ‹‹ስኳር እና ግፊት ያለባቸው ዓባላት ፈተናው አየለባቸው›› የምትለው አስር አለቃ ቤተልሄም ከአቅም በላይ ሲሆንባቸው ተኩስ አቁመው ወያኔ እና አንጃዎቹ ካምፑን ተቆጣጠሩት፡፡
አስር አለቃ ቤተልሄም ቀጣዩን ሃሳብ ስትናገር እምባ በዐይኗ ይሞላል፡፡ ለሃገሩ ዘብ ቆሞ ሲታኮስበት በነበረው ታንክ እጅ የሰጠ ወታደር በህይዎት እያለ ታንክ በላዩ ላይ አሽከረከሩበት፡፡ የሰራዊቱ በየደረጃው ያሉ መሪዎች ብሔራቸው እየተለየ ታፍነዋል፡፡ ሴቶች ተለይተው ከአንዱ ቦታ ወደሌላ ቦታ በኦራል አጭቀው አንከራተዋቸዋል፡፡
በመጨረሻ ደግሞ ለዘመናት የአማራ እና የኦሮሞ ህዝቦችን በፈጠራ ትርክት ሲያባሉ የነበሩበትን ‹‹የአኖሌ›› ድራማ በአማራ፣ ኦሮሞ እና ደቡብ ብሔር ሴት ወታደሮች ላይ ህዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም ሊፈፅሙ ቀነ ቀጠሮ ይዘው እንደነበር ምርኮኛ የትግራይ ልዩ ኃይል አባላት ተናግረዋል፡፡
የወያኔ አንጃ ቡድን ለዘመናት ህይዎታቸውን እረክዘው ዘብ የቆሙላቸውን ሴት ወታደሮች ወለታ ሲከፍሉ ስልካቸውን፣ ኤቲኤም ካርዳቸውን፣ የትምህርት ማስረጃቸውን፣ ልብሳቸውን እና ያገኙትን ጥሬ ገንዘብ ዘርፈው የተውሏቸው ነገር ቢኖር ወታደራዊ የደንብ ልብሳቸውን ብቻ ነበር፡፡
ስድቡ፣ ማስፈራሪያ እና ዛቻው አጥንት ይሰብራል የምትለው አስር አለቃ ቤተልሄም ደም ለለገሰ፣ አንበጣ ላባረረ፣ ትምህርት ቤት ለሰራ እና ህይዎቱን ለገበረ ወታደር መሰል ውለታ የተከፈለው ከኢትዮጵያ ውጭ ሌላ ሃገር አይኖርም ትላለች በእርግጠኝነት፡፡
በመጨረሻም የከሀዲውን ወያኔ እኩይ ዓላማ ያልተቀበለው የኩያ ተወላጅ ትግራዋይ የሆነው የ4ኛ መካናይዝድ ታንክ ተኳሽ ወታደር ‹‹በጓዶቸ ላይ አልተኩስም እኔ የኢትዮጵያ ወታደር ነኝ›› ሲል በጀግንነት ተዋግቶ በከሃዲው ቡድን ወታደሮች የተገደለውን ወንድማቸውን የሚያስቡበት ሃገር እንዳላቸው ሲናገሩ በተሰበረ ልብ ነበር፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው -መቀሌ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article‹‹ ዘላለም ይኖሩታል አንድ ቀን ያከብሩታል››
Next articleየብፁዕ ዶክተር አቡነ ገብርኤል ስርአተ ቀብር ተፈጸመ።