
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 26/2013 ዓ.ም (አብመድ) ዘመን ከተቆጠረ፣ ምድር ከተፈጠረ፣ የሰው ልጅ በምድር እንዲኖር ከተደረገ ጀምሮ በኢትዮጵያ ሰው ይኖር ነበር ይባላል፡፡ ኢትዮጵያ የሰው ልጅ የመጀመሪያ እናትና አባቶች የኖሩባት ቅድመ ሀገር እንደሆነች ይነገራል፡፡ በኃላም የሰው ልጅ በፈጣሪው ህግ አልገዛ አለ፣ ፈጣውን አሳዘነው፣ የጥፋት ዘመን መጣ፣ ጌታም ምድርን በንፍር ውሃ ሊያጠፋት ወደደ፡፡ በዚህም ጊዜ ፍጥረትን ሁሉ እንዲያተርፍ አስቀድሞ የተዘጋጄ፣ የዘመኑ በደል ያልነካካው፣ ከእውነተኛው ህግና ስርዓት ያልወጣ አንድ አባት ነበር፡፡ ታላቁ ኖህ፡፡ ይሄም ሰው እንደ ወላጆቹ ሁሉ በኢትዮጵያ ይኖር ነበር ይባላል፡፡
የጥፋት ዘመን ደረሰ፣ ምድር በንፍር ውሃ ተያዘች፤ ኖህ ፍጥረታትን በየፆታው መርጦ፣ በተመረጡ እንጨቶች ወደተሰራችው መርከብ ገባ፡፡ ክፉ ሰራዎች እስከነ ሰሪዎቻቸው ጠፉ፣ ምድር በመርከብ ውስጥ ከሚገኙት ፍጥረታት በስተቀር ምንም ምን አልነበራባትም፤ የንፍር ውሃ ጎደለ፣ መርከቧ ለምድር እየቀረበች ሄደች፣ በአራራት ተራራም አረፈች፣ አራራት ተራራም ከጣና ራስጌ የሚገኜው የአሁኑ ዘጌ ነው ይላሉ አባቶች፡፡ የታላቁ የዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም ደሴት የተቀመጠበት በአምሳለ ኖህ መርከብ ነው ይላሉ ሊቃውንት፣ የጎንደር ታላቁ ቤተ መንግሥትም የተሰራው የኖህ መርከብን መስሎ ነውም ይባላል፡፡ እንግዲህ ኢትዮጵያዊያን ከሁሉ አስቀድመው የነበሩ፣ ያሉ፣ የሚኖሩ ሕዝቦች ናቸው፡፡
ዘመን፣ ዘመንን ተካ፣ በመርከብ ያልሞላው ሕዝብ‹‹ ብዙ ተባዙ ምድርን ሙሏት›› እንዳለ እየበዛ ምድርን ይከባት ጀመር፡፡ በመርከብ አልሞላ ብሎ የነበረው የሰው ልጅ ሲበዛና በምድር በተለያዬ ስፍራ ሲኖር ዘር ይቆጥር ጀመር፡፡ ሁሉም የሰው ልጅ መጀመሪያዎቹ አዳምና ሄዋን(አደምና ሃዋ) ከሚባሉ እናትና አባት እንደመጣ ያምናል፡፡ ዝቅ ሲል ግን ዘራችን አንድ አይደለም፤ ብሔራችን ይለያያል፤ እያለ ይናቆር ጀመር፡፡ የብሔር ቆጠራው ደግሞ በኢትዮጵያ ላይ ከፍ እያለ መጣ፡፡
ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያ በምትባል የማትናወጥ ቀደምት ቤት፣ ኢትዮጵያዊነት የሚባል የማይጠወልግ የክብር ካባ ለብሰው ለዘመናት ኖረዋል፣ እየኖሩ ነው፣ ወደፊትም ይኖራሉ፡፡
የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ሳይጀመር፣ ብሔር እንደ ልዩነት ሳይቆጠር ኢትዮጵያዊያን ልዩነታቸውን እንደጌጥ ተጠቅመው በጋራ ቤታቸው፣ ለጋራ ቤታቸው ኖረዋል፡፡ እነዚህ ቀደምት፣ ድንቅና ኩሩ ሕዝቦች አሁን ላይ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን እያሉ የሚያከብሩትን በዓል ዘላለም ይኖሩታል አንድ ቀን ያከብሩታል፤ ለዘላለም በጋራ ኖረዋልና፤ የብሔር ብሔረሰቦች ቀንም የጋራ ኖሯቸውን እና በመካከላቸው ያለውን ልዩ ጸጋ ለዓለም የሚያስተዋውቁበት እንጂ በሌላው ዓመት ተለያይተው በክብረ በዓሉ የሚገናኙበት ቀን አይደለም፡፡ ለዚህም ነው ዘላለም የሚኖሩትን አንድ ቀን የሚያከብሩት፤ ኢትዮጵያን ልብ ብሎ ላያት፣ ሕዝቧቿን ለተመለከታቸው በየቀኑ የብሔር ብሔረሰቦች በዓል አለ፡፡ ቡና ሲፈላ የተለያዬ ቋንቋ የሚናገሩ፣ የተለያዬ እምነት፣ የተለያዬ ባሕል ያላቸው ሰዎች በጋራ ይጠጣሉ፣ ዓመት በዓል ሲደርስም ይህንኑ ያደርጋሉ፡፡ በአጭሩ ኢትዮጵያዊያን ውህዶች ናቸው፡፡
ለመሆኑ ብሔር ማለት ምን ማለት ነው? ሊቁ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ብሔር የሚለውን ቃል ‹‹ ቦታ፣ ሰፈር፣ ስፍራ በሀገር ውስጥ ያለ ታናናሽ ክፍል፤ ብሔር፡- ጥቡል፣ ወፍራም፣ ስብ፣ ውሃማ መሬት ለተክል የተመቸ፡፡ ብሔር፡- ሥዑር፣ ሣራም፣ የሣር ቦታ፣ መስክ፣ ጨፌ፣ ክልክል ፤ ብሔር፡- ምድር፣ ሀገር፣ ከተማ፣ ገጠር፣ አውራጃ፣ ግዛት፣ ታላላቅ ክፍል፣ በስምና በሹም፣ በወሰን፣ በደንብር የተለየ ፡፡ ብሔር፡- ሰው፣ ወገን፣ ነገድ፣ ሕዝብ፣ አሕዛብ፣ በቋንቋ በመንግሥት፣ በሕግ በሥርዓት የተለየ፡፡ ብሔር፡- ሰማይና ምድር፣ ሰማይ ከነግሡ፣ ምድር ከነልብሱ፣ መላው ዓለም ላዩም ታቹም፣ የአንድ አምላክ ግዛት ስለሆነ በምሳሌ ብሔር ተብሏል›› ብለውታል፡፡ እንግዲህ ስሙንና አምልኮታችን እንለያዬው ካልሆነ በስተቀር አብዛኛዎቻችን አንድ አምላክ አለ ብለን እናምናለን፡፡ ኢትዮጵያዊያን ደግሞ አማኞች ናቸው፡፡ የቆመንበት ምድር፣ የተጠለልንበት ሰማይ፣ በምድርና በሰማይ ያሉ፣ ከምድርም በታች፣ ከሰማይ በላይ ያለው ሁሉ የአንድ ፈጣሪ ግዛት ስለሆነ የአንድ ግዛት ሕዝቦች ነን ማለት ነው፤ አለቃ ኪዳነ ወልድ ይሄ ሁሉ ግዛት ነው ብሔር ተብሏል ያሉት፡፡
የኢትዮጵያዊያን የብሔር ብሔረሰቦች ቀን አከባበር ምን አይነት አንድምታ አለው ? በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር አበበ ይርጋ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን መከበር መጥፎ ነገር የለውም፤ ጥያቄው ግን አከባበሩና የአካባበሩ ዓላማ ላይ ነው ያሉት፡፡ ካሁን ቀደም የበዓሉ አከባበር አደባባይ ወጥቶ ደስታን መግለጽ ካልሆነ በስተቀር ለብሄር ብሄረሰቦች የባሕል እድገት፣ ለመብታቸው፣ ለኢኮኖሚና ፖለቲካ ተጠቃሚነታቸው ተፅዕኖ የፈጠረላቸው ነገር የለም ነው ያሉት፡፡ በጋራ ቢያከብሩትም ሃገራዊ ውሳኔ ላይ የሚሳተፉት ግን የታወቁና ጥቂቶች እንደነበሩም ተናግረዋል፡፡
ቀኑ ሲከበር ብሔር ብሔረሰቦች መብታቸውን ያረጋገጡበት፣ ከጨቋኙ ስርዓት የወጡበት፣ ነጻነት ያገኙበት ነው ይላል የሚሉት የፖለቲካ መምህሩ ማነው ጨቋኙ ተብሎ ሲጠዬቅ ደግሞ አዕምሮ ውስጥ እንዲቀረፅ የተደረገው የአማራ ገዢዎች ጋር ነው ብለዋል፡፡ በተለይም ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ አድራጊ ፈጣሪ የነበረው ትህነግ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ሲከበር ከአማራ ገዢነት ነፃ የወጡበት ነው ብሎ በማሰብ ቀኑ እንዲከበር እንደሚያደርገውም ተናግረዋል፡፡
የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ሲከበርም ለአማራ ሕዝብ ብዙ ጠላት የሚበጅለት፣ ሌሎች ብሔረሰቦች ደግሞ አማራ ጠላታችሁ ነው፣ አማራ ጨቋኝ ነው ተብለው ትምህርት እንዲወስድ የሚደረግበት እንደነበርም ተናግረዋል፡፡ ትህነግ በዚህ ሽፋን እኔ ገዢያችሁና ነጻ ያወጣኋችሁ ነኝ በማለት መልዕክት የሚያስተላልፍበት ነበርም ብለዋል፡፡
የትህነግ መነሻና መድረሻ አማራን ከሌላው ብሔር ጋር መነጠል መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በትክክለኛው አላማ ለእኩልነትና ለአንድነት ተጠቅሞበት ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያ ላይ ያጋጠመው ችግር አይፈጠርም ነበር ብለዋል፡፡ የብሔር ብሔረሰቦችን መብታችሁን አክብሬያለሁ ብሎ አደባባይ መውጣት ብቻ ሳይሆን እኩል ተጠቃሚ ማድረግ ዋናው ጉዳይ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡
ትህነግ በሌሎች ክልሎች የነበረው ጣልቃ ገብነት የብሔር ብሔረሰቦችን ቀን አከበርኩ የሚለውን ሽፋን መሆኑን የሚያመላክት መሆኑን ነው ጠቅሰዋል፡፡ ትህነግ ብሔር ብሔረሰቦችን ለአጀንዳው ማስፈፀሚያነት ሲጠቀምባቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ትክክለኛውን የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ለማክበር ከክብረ በዓሉ የነበረው ትርክትና ክፋት መጥፋት አለበት ያሉት መምህሩ ማንም ብሔር ማንንም ጨቁኖ አለማወቁም መታወቅ አለበት ነው ያሉት፡፡
ትህነግ በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ሲፈፅም የኢትዮጵያ ሕዝብ የትህነግ እኩይ ድርጊት በማውገዝና ለሰራዊቱ ድጋፍ በመስጠት የተባበረበት መንገድ አንድ የሆነ ሕዝብ መሆኑን የሚያሳይ ነውም ብለዋል፡፡ የሕዝቡን መልካም እሳቤ ማጎልበት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ሀገር ላይ የሚያተኩሩ፣ የብሔር ብሔረሰቦችን ልዩነት ውበት መሆኑን የሚያሳዩ የመገናኛ ብዙኃን ከተበራከቱ በዓሉ ጎብኚ የሚሳብበት፣ አንድነት የሚጠናክርበት፣ መልካም እሳቤዎች የሚሰፉበት ይሆናልም ብለዋል፡፡
በታርቆ ክንዴ