
በጎ ፈቃደኛ መምህራን ለሀገራዊ ጥሪ ምላሽ በመስጠት ሀገር ወዳድነታቸውን በተግባር እያሳዩ ነው፡፡
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 25/2013 ዓ.ም (አብመድ) በዓለም አቀፍ ደረጃ በሰወች ሁለንተናዊ ኑሮ ላይ እንቅፋት የፈጠረው የኮሮናቫይረስ በሀገራችንም የዜጎች እንቅስቃሴ ላይ ተጽኖ ሲያደርስ ቆይቷል፡፡ አሉታዊ ተፅኖ ካሳደረባቸው ዘርፎች ውስጥ የትምህርት አሰጣጡ አንዱ ነው፡፡ በዚህ ምክንያትም ተማሪዎች እርቀታቸውን ከመጠበቅ ባለፈ በአንድ ክፍል ቁጥራቸው ከተለመደው ዝቅ እዲል በማድረግ የተያዘው ዓመት ትምህርት እዲሰጥ ተወስኖ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡
ለዚህ እዲያግዝም ተጨማሪ አስተማሪዎች አስፈልገው ነበር፡፡ መንግስት የገጠመውን የመምህር እጥረት ለመፍታትም በበጎ ፈቃደኝነት ማስተማር የሚችሉ ዜጎች እዲሳተፉ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡
በአማራ ክልል ከሚገኑ 15 ዞኖች ውስት በስምንት ዞኖች ብቻ 1 ሺህ 386 መምህራን መንግስት ላቀረበው ሀገራዊ ጥሪ ምላሽ በመስጠት አለኝታነታቸውን እያሳዩ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል፡፡
ለሀገራዊ ጥሪው ምላሽ ከሰጡ በጎ ፈቃደኞች መካከል መምህር እዮብ ጌታቸው አንዱ ናቸው፡፡ የኮረናቫይረስ ያሳደረውን ተፅእኖ ለመቋቋም የበኩሌን ለመወጣት በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር በሽንብጥ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በበጎ ፈቃደኝነት በማስተማር ላይ እገኛለሁ ሲሉ ገልፀዋል፡፡
መምህር ታዲወስ አባይም ሌላው በከተማዋ በፀሀይ ግባት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በበጎ ፈቃደኝነት በማስተማር ላይ የሚገኙ መምህር ናቸው፡፡ መምህር ታዲወስ እንዳሉት መንግስት የመምህር እጥረት እደገጠመው በሚዲያ ከሰሙ በኋላ በፈቃደኝነት በማስተማር ላይ ናቸው፡፡
በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የመምህራንና የትምህርት አመራር ልማት ዳይሬክተር ብርሃኑ አዲስ እንደተናገሩት በጎ ፈቃደኛ መምህራኑ የዲፕሎማ፣ የመጀመሪያ ዲግሪና የሁለተኛ ዲግሪ የትምህርት ደረጃ ያላቸው ሲሆኑ ከመደበኛ መምህራን ጋር እኩል ሀላፊነት ተሰጥቷቸው ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን በመወጣት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በበጎ ፍቃደኝነት እያገለገሉ የሚገኙት መምህራን፣ በትምህርት ሙያ የተመረቁበና ሥራ የሌላቸው፣ በመምህርነት ሲያገለግሉ ቆይተው ጡረታ የወጡ፣ በትምህርት ሙያ ተመርቀው በሌላ ሴክተሮች ውስጥ የሚያገለግሉ የሀገር ወዳድ ዜጎችን ወደ ሥራ እንዲሰማሩ መደረጉን አቶ ብርሃኑ አብራርተዋል፡፡
እነዚህ መምህራን እስከ ትምህርት ዘመኑ መጨረሻ ድረስ የሚቆዩ ሲሆን በመጨረሻም የክልሉ መንግሥት ምሥጋናና እውቅና እንደሚያበረክትላቸው ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ብሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ