
ከመንግስት ጎን በመቆም ለከተማዋ ዘላቂ ሰላም እንደሚሰሩ የኮረም ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 25/2013 ዓ.ም (አብመድ) የግራ ካሶ ተራራን ደጀን፣ የአሸንጌ ሃይቅን ተገን፣ ማይጨውን ጎረቤት፣ አላማጣን እህት አድርጋ የከተመችው ታሪካዊቷ የኮረም ከተማ ከትህነግ የጉልበት አገዛዝ ነፃ ከወጣች ቀናትን አስቆጥራለች፡፡
ኮረም የግዞት ማንነት በተውሶ ሳይጫንባት ወሎ ክፍለ ሃገር ዋግ አውራጃ ውስጥ የምትገኝ ከተማ እንደነበረች ይነገራል፡፡ ዛሬም ስለዚያ ዘመን የሚተርኩ አዛውንቶቿ ከአሁኑ ይልቅ ከቀደመው ጋር የጠበቀ ትዝታ እና ቁርኝት አላቸው፡፡
ያለፉት ሦስት አስርት ዓመታት የትህነግ የግፍ አስተዳደር ዳፋ ካጎሳቆላቸው ከተሞች አንዷ ኮረም ናት፡፡ ትህነግ እራሷ ቆስቁሳ በተለበለበችበት የሰሞኑ ጦርነት ሳትዎድ በግድ ከለቀቀቻቸው የጦርነት አውድማ ቦታዎች ግራ ካሶን ተገን ያደረገው የኮረም አካባቢ አንዱ ነው፡፡ ሰራዊቱ አይቀጡ ቅጣት ቀጥቶ ምሽጎቿን መቀበሪያዋ እስኪያደርገው ድረስም የጎበዝ አለቆቿ ጥርሳቸውን ነክሰው ተዋግተውበታል፡፡ ምንም እንኳን ድል የማታ ማታ ወደ እውነት ማዘንበሏ ባይቀርም፡፡
ባለፈው የአስተዳደር ዘመን የኮረም ከተማ በግዳጅ ወደ ትግራይ ክልል መካለሏ ሳያንስ ነዋሪዎቿ የግፍ ዘመንን እንዲያሳልፉ ተገደው ነበር የሚሉት የከተማ ነዋሪ አቶ አርአያ ካህሳየ ናቸው፤ በመረጥነው ቋንቋ እንዳንጠቀም፣ ባህላችን እንዲጠፋ እና ማንነታችን እንዲታፈን በተደራጀ መንገድ ሲሰራ ቆይቷል ነው ያሉት፡፡
ኮረም በግዳጅ የተሰጣት ማንነት አልጠጋት ብሎ ቆይቷል ያሉት አስተያየት ሰጭው የኮረም ከተማ ዛሬ የትናንቱ የጨለማ ድባብ ተላቋት የብርሃን ጭላንጭል ማየት ጀምራለች፡፡
ሌላው አስተያየት ሰጭ ወጣት ጀማል ሰይድ እንዳለው ኮረም ባለፉት ጥቂት ሳምንታት የትህነግ የጦርነት ነጋሪት ሲያደነቁራት ሰንብቷል፤ የመከላከያ ሰራዊት የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ በድል ወደ ከተማዋ መግባቱን ተከትሎ አንፃራዊ የሰላም አየር እየነፈሰባት እንደሆነ ነግሮናል፡፡
የተደራጀ የዘር ፖለቲካ፣ የዘመድ አዝማድ አስተዳደር እና የልዩነት አስተሳሰብ በከተማዋ የፍርሃት ድባብ እንዲሰፍን አድርጎት እንደነበርም ገልጾልናል፡፡
ያለፉት ሳምንታት በኮረም ከተማ ለሰው ልጅ በተለይም ለእናቶች የጭንቅ ጊዜያት ነበሩ ያሉን ሌላዋ አስተያየት ሰጭ ወይዘሮ መብራት ግርማይ ናቸው፤ “ያለፈውን እንኳን እኛ ልጆቻችን ዳግም ባያዩ ምኞታችን ነው” ብለዋል፡፡
መለያየት ለሰው ልጅ የሚበጅ አይደለም ያሉት ወይዘሮ መብራት ካለፈው ስህተታችን ተምረን የተሻለ ጊዜ እንዲመጣ መስራት የከተማዋ ነዋሪዎች እና የመንግስት ድርሻ እንደሆነ ተናግረል፡፡
ከሰሞኑ በነበረው ጦርነት የተቋረጡት የመብራት፣ የውሃ፣ የስልክ እና የማኅበራዊ አገልግሎቶች በአፋጣኝ እንዲስተካከሉ አስተያየት ሰጭዎቹ ጠይቀዋል፡፡ ለከተማዋ ዘላቂ ሰላም መስፈን ከመንግስት ጎን በመቆም የድርሻቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል፡፡
ነዋሪዎቹ በከተማዋ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲኖር እና ጦርነቱ በከተማዋ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ እንዲጠናቀቅ ላደረጉት የሃገር መከላከያ ሰራዊት፣ ለአማራ ክልል ልዩ ኃይል እና ለአካባቢው ሚሊሻ አባላት ያላቸውን አጋርነት ገልፀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው – ኮረም
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ