“በጦር ግንባር ያገኘነውን ድል በኢኮኖሚ ልንደግመው ይገባል” የአማራ ክልል ምክትል ርዕስ መስተዳድር ፋንታ ማንደፍሮ (ዶ.ር)

247

ባሕር ዳር፡ ኅዳር 24/2013 ዓ.ም (አብመድ) በአማራ ክልል የመስኖ ልማት ንቅንቄ በክረምት ወራት የጎርፍ መጥለቅለቅ ከደረሰባቸው ዞኖች በአንዱ በደቡብ ጎንደር ዞን ደራ ወረዳ ተጀምሯል። ንቅናቄውን ያስጀመሩት የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ፋንታ ማንደፍሮ (ዶክተር) በሀገር ብሎም በአማራ ክልል ላይ ያነጣጠረውን ጥቃት ከመመከት በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማምጣት ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በኢኮኖሚው ዘርፍ የሚመዘገብ እድገት ለተጨማሪ ድል እንደሚያግዝ ካደጉት ሀገራት መማር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ “ለሀገራችን አንድነት የማንሰስተውን ድል በኢኮኖሚው ዘርፍ መድገም ካልቻልን በሌሎች እጃችን መጠምዘዙ እንደማይቀር ማሰብ አለብን” ብለዋል። ለዚህም በክልሉ የሚገኘውን ተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
ደቡብ ጎንደር ዞን ደራ ወረዳ ከ1977 ዓ. ም ጀምሮ የሩዝ ምርት ማምረት ጀምሯል፤ ዘመናዊ የአመራረት ስልት ግን እየተከተለ አይደለም፤ በቀጣይ የግብርና ባለሙያዎች እና ተመራማሪዎች ትኩረት ሰጥው ሊሰሩ እንደሚገባ ፋንታ ማንደፍሮ (ዶክተር) አሳስበዋል። “‘ውኃ በላን’ ሲል የነበረው የአካባቢው ማኅበረስብ ‘ውኃው አበላን’ እንዲል የመስኖ ልማትን ዘመናዊ በማድርግ ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ አለበት” ብለዋል ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፡፡ የሽንኩርት ክላስተርን በመስኖ በመዝራት የጎርፍ መጥለቅለቅ ያጋጠመውን ኪሳራ ለማካካስ እየተሰራ እንደሆነም አስታውቀዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ መለስ መኮንን (ዶክተር) ለአንደኛ ዙር የመስኖ እርሻ ወቅት ውኃ ቆጣቢና ዘመናዊ መስኖ መጠቀም፣ የተሻሻለ ዘር እና የፀረ ተባይ ኬሚካል ለማቅረብ እየተሰራ ነው ብለዋል። በአንደኛ እና በሁለተኛ ዙር የመስኖ እርሻ 392 ሺህ 040 ሄክታር ማሳ በማረስ 37 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት መታቀዱን የቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል። ይህም ከባለፈው ዓመት የመስኖ እርሻ ምርት በ23 በመቶ ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል፡፡
የደቡብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አዲስ ጌታሁን ዘንድሮ በተለየ ሁኔታ የገጠሙ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥዊ አደጋዎች በተለይም የኮሮናቫይረስ ወረርሽን፣ አንበጣ፣ የትህነግ ጁንታ ቡድን ትንኮሳ፣ የጎርፍ አደጋ ያስከተሉትን የምርት መቀነስ ለማካካስ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleሴቷ ወታደር የጁንታውን ተላላኪ ኮሌኔል በቁጥጥር ሥር አዋለችው፡፡
Next articleከመንግስት ጎን በመቆም ለከተማዋ ዘላቂ ሰላም እንደሚሰሩ የኮረም ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡