ሴቷ ወታደር የጁንታውን ተላላኪ ኮሌኔል በቁጥጥር ሥር አዋለችው፡፡

1379

ሴቷ ወታደር የጁንታውን ተላላኪ ኮሌኔል በቁጥጥር ሥር አዋለችው፡፡

ባሕር ዳር፡ ኅዳር 23/2013 ዓ.ም (አብመድ)
ሐገር ለማፍረስ ሴራ የተቀበለው ኮሌኔል በሴት ጠባቂው ወታደር በቁጥጥር ሥር ውሏል፡፡
ኢትዮጵያ መንታ ልጆች ወልዳ አሳይታናለች፡፡ አንደኛው እናቱን የሚገድል ሌላኛው ለእናቱ የሚሞት፡፡ በእናታቸው የተጣሉት ሁለቱ ልጆቿ ለእናቱ የሚሞተው አሸንፎ እናቱን ታድጓል፡፡
የትህነግ ጁንታ ወልዳ ያሳደገችውን፣ አሳድጋ ለወግ ማዕረግ ያበቃችውን መተኪያ የለሽ ኢትዮጵያን በጀርበዋ ወግቷታል፡፡
ዳሩ ጀግና ልጆች አሏትና የተወጋባትን ቀስት ነቅላ ከወጊው ላይ በመጣል ድሉን የራሷ አድርጋለች፡፡ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን የሚመኩበት ጀግና የመከላከያ ሠራዊት አላቸው፡፡ በትህነግ ተክዶ ሳይወድ በግድ ጦርነት የገጠመው የመከላከያ ሠራዊት አጀብ የሚያሰኝ ጀብዱ ፈፅሟል፡፡
‹‹ እንኳን ኢትዮጵያ ባለቤትየው ጣልያንም ቀና አንድ ቀን ባዬው›› እንዳለ የቀድሞ ፎካሪ በወታደሩ ጀግንነት ኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆኑ ዓለም ግሩም ድንቅ ብሏል፡፡ ከዚሁ ጀብደኛ ወታደር አንድ አስደናቂ ጀግንነት ተሰምቷል፡፡የኢፌድሪ መከላከያ ሰራዊት ዛሬ ያወጣውን መረጃ እንዲህ አሰናድተናዋል፡፡
ምክትል አስር አለቃ ገበያነሽ ደባልቄ ትባላለች፡፡ ስምን መላዕክ ያወጠዋል እንዲሉ የደባልቄ ልጅ ጠላቷን ደባልቀዋለች፡፡ ጀግናዋ ወታደር ኮሌኔሉን ማንቁርቱን ይዛ አስረክበዋለች ነው ያለው ሚኒስቴሩ ባወጣው መረጃ ።
20ኛ ቃሉ ክፍለ ጦር ሰሜን ዕዝ ካሏት የጦር ክፍሎች ውስጥ አንዱ ነው። ምክትል አሥር አለቃ ገበያነሽ በዚህ ክፍለ ጦር 1ኛ ብርጌድ 1ኛ ሻለቃ አባል ናት፡፡ ምክትል አስር አለቃ ገበያነሽ ደባልቄ የሻለቃው አዛዥ ኮሎኔል ሰለሞን ገብረ ዮሃንስ አጃቢ ናት ። ጀግናዋ በታማኝነት የተሰጣትን አደራ መወጣት እንጂ አለቃዋ ምን እንደሚያስብ አታውቅም፡፡
ትህነግ የእብሪት ርምጃውን ከመጀመሩ ከሶስት ቀናት በፊት ሰራዊቱ የምግብና መጠጥ አገልግሎት የሚያገኝባቸውን መንገዶች በመዝጋት ሰራዊቱን ለከፍተኛ ርሃብና ጥም ዳርጓል ። ይሄም ላቀዱት ጦርነት አዳክሞ ለመቆዬት ነበር፡፡
በዚህ ወቅት አዛዡ ሁሉም የሰራዊት አባል የግል ትጥቁን በአንድ ክፍል በማስቀመጥ በህብረተሰብ የድጋፍ ስራዎች ላይ እንዲረባረብ ማድረጉን ታስታውሳለች ።
በተለይም ጥቃቱ የተጀመረበት ጥቅምት 24 ቀን
2013 ምሽት ላይ ሁሉንም የጥበቃ ቦታዎች በትግራይ ተወላጅ የሰራዊት አባላት እንዲሸፈኑ ተደረገ፡፡ የከሃዲው ቡድን ልዩ ሃይልና ሚሊሻ ለጥቃት ተዘጋጅተዋል፡፡ የሰራዊቱ አባላት በበኩሉ ሀገር አማን ብሎ ዝም ብሏል፡፡ የተዘጋጄው ከሃዲው ቡድን ዝግጅትና ትጥቅ ባልነበረው ሰራዊት ላይ ከፍተኛ ተኩስ መደረጉን ጀግነዋና ታስታውሰዋለች ።
‹‹ሆኖም ታላቅ ጀግንነትና ኢትዮጵያዊ ማንነትን የወረሰው ጀግናው ሃይላችን የማይታሰቡ ጀብዶችን ጭምር በመፈፀም ወደ ኤርትራ በመሸሽ ራሱን ማዳን ቻለ›› ነው ያለችው ምክትል አስር አለቃ ገበያነሽ፡፡
በዚህ ሁሉ ግፍና በደል መሃል የሻለቃዋ ዋና አዛዥና ለዘመናት የመራቸውን የሃገር መከላከያ ሰራዊት አባላት የካደው ኮሎኔል ሰለሞን ገብረ ዮሃንስ ራሱን መፀዳጃ ቤት ውስጥ በመደበቅ በጁንታው የተሰጠውን ተልዕኮ መፈፀም እንደጀመረ ጀግናዋ ተመለከተች፡፡ ሁኔታውን በሃዘን ስሜት ውስጥ ሆና አስታውሳለች ።
የቀድሞ አለቃዋን እንዴት እንደያዘችው ስትናገር “… ሰራዊታችን በታፈነበት ጥቅምት 24 ምሽት 2 ሰዓት ላይ በከባድ መሳሪያ የታጀበ ተኩስ ወደ ካምፓችን ተተኮሰ፤ በዚህ ሰዓት ወደ መፀዳጃ ቤት ራሱን የደበቀው ካሃዲው አዛዥ ተብየውን እኔ በትግራይ ሚሊሻና ልዩ ሃይል ጥይት ከምሞት አንተን ገድየ ራሴን አጠፋለሁ አልኩት፣ ተኩሱ በርትቷል፣ ሁሉም ራሱን ለማዳን ወደህሊናው የመጣለትን አማራጭ እየተጠቀመ ይሯሯጣል፡፡
በመጨረሻም ከተደበቀበት መፀዳጃ ቤት እንዲወጣና እኔ የምለውን ብቻ እንዲፈፅም አዘዝኩት፡፡ እሽ የማይል ከሆነ ግን እንደምገድለው አስጠነቀኩት፤ እሱም በፍርሃት ውስጥ ሆኖ ከተደበቀበት ቦታ ወጥቶ ወደነገርኩት ቦታ መጣ፤ ሽጉጡንና ማዕረጉን እንዲሰጠኝ አደረኩ፤ ከዛም ጫማውን እንዲያወልቅ አድርጌ በየመንገዱ ከማገኛቸው የሰራዊት አባላት ጋር በመተባበርና ሙሉ ለሊት የእግር ጉዞ በማድረግ ኤርትራ ይዤው በመግባት ታማኝ እና ሙሉ ኢትዮጵያዊ ለሆኑ አመራሮች አስረከብኩ ” በማለት ታስታውሰዋለች፡፡
ሰራዊታችን በራሱ ወገኖች የደረሰበትን ግፍና በደል ተሸክሞ ቂምን ሳይሆን ኢትዮጵያዊ ፍቅር አስቀድሞ ለድል በመብቃቱ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማትም ምክትል አስር አለቃ ገበያነሽ ደባልቄ ተናግራለች ።
አዛዡ ሀገሩን ሲክድ ታዛዣ ቃሏን አፀናች፡፡ ኢትዮጵያን የሚያሳስባትን ለኢትዮጵያ የምታስበው ጀግና ስትጠብቀው ኖረች፡፡ ነገር ግን ቃሏን፣ ሀገሯንና ማንነቷን አተረፈች እንጂ አልከዳችም፡፡
ኢትዮጵያ በመከራ ዘመን ከምትመካባቸው የቁርጥ ቀን ልጆች መካከል ምክትል አስር አለቃ ገባያነሽ ደባልቄ አንደኛዋ ናት፡፡
አዘጋጅ፡- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበአማራ ክልል የሚገኙ ከተሞች በከተማ አስተዳደርነት እንዲመሩ መወሰኑ ለከተሞቹ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ዕድገት መፋጠን አስተዋጾ እንዳለው የሞላሌ እና የሻሁራ ከተማ የሥራ ኃላፊዎች ተናገሩ፡፡
Next article“በጦር ግንባር ያገኘነውን ድል በኢኮኖሚ ልንደግመው ይገባል” የአማራ ክልል ምክትል ርዕስ መስተዳድር ፋንታ ማንደፍሮ (ዶ.ር)