በአማራ ክልል የሚገኙ ከተሞች በከተማ አስተዳደርነት እንዲመሩ መወሰኑ ለከተሞቹ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ዕድገት መፋጠን አስተዋጾ እንዳለው የሞላሌ እና የሻሁራ ከተማ የሥራ ኃላፊዎች ተናገሩ፡፡

937
በአማራ ክልል የሚገኙ ከተሞች በከተማ አስተዳደርነት እንዲመሩ መወሰኑ ለከተሞቹ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ዕድገት መፋጠን አስተዋጾ እንዳለው የሞላሌ እና የሻሁራ ከተማ የሥራ ኃላፊዎች ተናገሩ፡፡
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 23/2013 ዓ.ም (አብመድ) በአማራ ክልል 23 ከተሞች በከተማ አስተዳደርነት እንዲመሩ መወሰኑ በከተሞች የሚስተዋለውን የመሰረተ ልማት እና የስራ ዕድል ፈጠራ ችግር ለመቅረፍ እንደሚያስችል ተገልጿል፡፡
በ1999 ዓ.ም የተደረገው የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ውጤት እንደሚያሳየው በሃገሪቱ የከተማ ነዋሪው ሕዝብ ብዛት 11 ነጥብ 9 ሚሊዮን ነው፡፡ ይህም ከጠቅላላው የሀገሪቱ ህዝብ 16 ነጥብ 1 በመቶ እንደሆነ ነው የተገለጸው፡፡
የዓለም ባንክ በ2008 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት ደግሞ ቁጥሩ ከ20 ሚሊዮን በላይ መሆኑን ያመላክታል፡፡ ይህ የአከታተም ደረጃ አሁን ካለው ከአፍሪካ አማካኝ 37 በመቶ እንደሆነ አመላክቷል፡፡ ሆኖም በኢትዮጵያ ባለፉት አስር ዓመታት የከተማ ነዋሪዎች ቁጥር ፈጣን እድገት እያሳየ ነው፡፡
በአማራ ክልል በከተሞች የሚስተዋለውን ችግር ለመቅረፍ 23 ከተሞች በከተማ አስተዳደርነት እንዲመሩ ተወስኗል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ሞላሌ እና ሻሁራ ከተሞች ይገኙበታል፡፡
በሰሜን ሸዋ ዞን መንዝ ማማ ምድር ወረዳ የሞላሌ ከተማ መሪ መዘጋጃ ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ ከተማ ሻረው እንደገለጹት የከተማዋን መሰረተ ልማት ችግሮች ለመፍታት ወደ ከተማ አስተዳደር እንዲያድግ ጥያቄ ሲቀርብ ቆይቷል፡፡ በተለይም ደግሞ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በከተማዋ እየጨመረ ከመጣው የህዝብ ቁጥር ጋር ተያይዞ ጥያቄ በተደራጀ መንገድ መቅረቡን ዋና ስራ አስኪያጁ ነግረውናል፡፡ በዚህም በክልል ባለሙያዎች አጠቃላይ የከተማዋ ኢኮኖሚያዊ፣ ማሕበራዊ እና የሕዝብ ቁጥር በማጥናት ወደ ከተማ አስተዳደርነት ማደጉን ነግረውናል፡፡ ይህም ለከተማዋ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ዕድገት መፋጠን ሚናው ጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በከተማዋ የሚስተዋለውን የስራ ዕድል ፈጠራ ችግር ለመፍታትም ያስችላል፡፡ ማሕበረሰቡም የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኝ ያስችላል ብለዋል፡፡ በአካባቢው ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ሚናው የጎላ እንደሚሆንም ተናግረዋል፡፡
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የአለፋ ወረዳ የሻሁራ ከተማ መሪ ማዘጋጃ ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ ጋሻው አጣናው እንደተናገሩት ደግሞ ከ 8 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው ጥያቄ ምላሽ መሰጠቱ ለከተሞች ዕድገት ትኩረት መሰጠቱ ማሳያ ነው፡፡ ይህም ከተሞች የራሳቸውን አደረጃጀት በማዋቀር በከተሞች የሚታየውን የመሰረተ ልማት እና የስራ ዕድል ፈጠራ ችግር ለመፍታት ትልቅ እድል እንደሚኖረው ነግረውናል፡፡
በአማራ ክልል 23 ከተሞች በከተማ አስተዳደርነት እንዲመሩ መወሰኑን የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት ህዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም ባካሄደው 5ኛ ዙር 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ስብሰባ ውሳኔውን ማስተላለፉ ይታወቃል፡፡ በከተሞች የአደረጃጀት ፈርጅ መወሰኛና ማቋቋሚያ ደንብ ቁጥር 65/2001 መሰረት መስፈርቱን አሟልተው የተገኙ 23 ከተሞች በከተማ አስተዳደርነት ለመመራት በክልሉ ከተማ ልማትና ቤቶች ኮንስትራክሽን ቢሮ አጥንቶ ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ተቀብሎ ነው ምክር ቤቱ ያጸደቀው፡፡
ምክር ቤቱ በጉዳዩ ላይ በስፋት መክሮ የከተሞችን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ከመፍታትና ወደ ፊት ያላቸውን የመልማት ዕድል የተጠቀሱ ከተሞችን የደረጃ ሽግግር አጽድቋል፡፡ በዚህም መሰረት ከደቡብ ጎንደር ዞን ወገዳ፣ ሀሙሲት እና እብናት፣ ከአዊ ብሄረሰብ ዞን አዲስ ቅዳም፣አገው ግምጃ ቤት፣ ፈንድቃ፣ ከምስራቅ ጐጃም ዞን ደብረ ወርቅ፣ ሉማሜ፣ አማኑኤል እና ግንደ ወይን፣ ከምዕራብ ጐጃም ዞን ሽንዲ እና ጅጋ ከተሞች ይገኙበታል ፡፡ ከደቡብ ወሎ ዞን ከላላ፣ ቱሉ አውሊያ፣ ሀርቡ፣ አቀስታ፣ ደጎሎ፣ ከሰሜን ሽዋ ዞን ደብረሲና፣ ሞላሌ፣ እነዋሪ፣ ከሰሜን ወሎ ዞን ጋሸና እንዲሁም ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን ደግሞ ቆላድባ እና ሻሁራ የከተማ መስፈርቱን ያሟሉ ሆነው በመገኘታቸው በከተማ አስተዳደር እንዲመሩ ተወስኗል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሰራ
Previous articleኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስወነጨፈቻትን ˝ኢት አር ኤስ ኤስ 1˝ ሳታላይት በይፋ ከቻይና ተረከበች፡፡
Next articleሴቷ ወታደር የጁንታውን ተላላኪ ኮሌኔል በቁጥጥር ሥር አዋለችው፡፡