
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዛሬም በንጹሃን ዜጎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
ባሕር ዳር: ኅዳር 23/2013 (አብመድ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በማንዱራ ወረዳ ቁጥር ሁለት ቀበሌ በተደራጁ ኃይሎች ህዳር 23/2013 ዓ.ም ከጥዋቱ 2፡00 ገደማ በንጹሃን ላይ ባደረሱት ጥቃት የሰው ህይወት ማለፉን እና አካል ጉዳት መድረሱን ከጉዳቱ የተረፉ ሰዎች ለአብመድ ገልጸዋል፡፡
ጥቃቱ የተፈጸመው በአንድ የጭነት እና በሁለት የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ላይ ተሳፍረው ሲጓዙ በነበሩ ንጹሃን ላይ መሆኑን ነው ከጥቃቱ የተረፉት ሰዎች የገለጹት፡፡
ጥቃቱ በደረሰበት ወቅት የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉን እና በሌሎች ተሳፋሪዎች ላይ ደግሞ ከባድ እና ቀላል ጉዳት መድረሱን ነግረውናል፡፡
ጉዳት ከደረሰባቸው ውስጥ 8 ተሳፋሪዎች በፓዊ አጠቃላይ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑንም ከሆስፒታሉ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የመተከል ዞን ኮማንድፖስት ሰብሳቢ ኮሎኔል አያሌው በየነ አካባቢው የምርት መሰብሰቢያ ወቅት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ባልተጠበቀ ቦታ ጥቃት ደርሷል ብለዋል፡፡
ኮሎኔሉ ከሰሞኑ በአካባቢው ሲንቀሳቀሱ በነበሩ ጸረ ሰላም ሃይሎች ላይ ርምጃ መወሰዱን ጠቅሰው በጥቃት አድራሽ ኃይሎች ላይ ርምጃ ለመውሰድ ኃይል መሰማራቱን ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ዳግማዊ ተሰራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ