የጁንታው ቡድን ለፍርድ እስኪቀርብ በላቀ ጀግንነት የጀመሩትን ትግል እንደሚቀጥሉ የአማራ ልዩ ኃይል አባላት ተናገሩ፡፡

533

የጁንታው ቡድን ለፍርድ እስኪቀርብ በላቀ ጀግንነት የጀመሩትን ትግል እንደሚቀጥሉ የአማራ ልዩ ኃይል አባላት ተናገሩ፡፡

ባሕር ዳር: ኅዳር 23/2013 (አብመድ) የአማራ ልዩ ኃይል አባላት የጁንታው ቡድን የራስ ምታት፣ የአማራ ህዝብ ዳግም ትንሳኤ አብሪ ኮከብ፣ የሰሜን ኢትዮጵያ ህግ የማስከበር እርምጃ ክስተት እና ለግፉአን ፈጥኖ ደራሽ እንደሆኑ በርካቶች ያለልዩነት መስክረዋል፡፡ የልዩ ኃይል አባላቱ ትህነግ ለለኮሰችው ጦርነት የዓመታት ዝግጅት እንዳደረገች ቢያውቁም ከጦርነት ድግስ ይልቅ የጦር ስልት፤ ከትጥቅ ይልቅ ልብ እንደሚያስፈልግ ስለሚያውቁ ባልተዘጋጁበት አውደ ውጊያ ሁሉ ግቡ ሲባሉ ገብተው ጠብ አጫሪዋን ድባቅ መቷት፡፡
ከህግ ማስከበር ርምጃው ጎን ለጎን የክልሉን ሰላም በማስጠበቅ እና ከትህነግ አገዛዝ ነፃ በወጡ አካባቢዎች ማኅበረሰቡን በማረጋጋት፣ የቀሩ የትህነግ አባላትን በማፅዳት እና የፀጥታ ስጋት የሆኑ አካባቢዎችን በመለየት ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን አሁንም እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
የሰራዊቱ አባላትም የተሰማሩበትን ህግ የማስከበር ተልዕኮ በላቀ ብቃት እና ጀግንነት እንደተወጡ ገልጸው ህገወጥ ቡድኑ ሙሉ በሙሉ ለፍርድ እስከሚቀርብ ድረስ ትግላችን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡ በአማራ ልዩ ኃይል የጣና ብርጌድ አባል የሆነችው ምክትል ሳጅን ዓለምነሽ ብርሃኔ ለህዝብ ነፃነት እና ለሃገር ሉአላዊነት ሲባል የጁንታዉ ቡድን ለፍርድ እስኪቀርብ ድረስ እና ህግ የማስከበሩ ተልዕኮ ሙሉ በሙሉ እስከሚጠናቀቅ የተሰጣትን ግዳጅ በብቃት ለመወጣት ዝግጁ መሆኗን ነግራናለች፡፡ “ትግል እስከ ህይዎት መስዋዕትነት ድረስ ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑን እናውቃለን፤ ብንሞት እንኳን የምንሞተው መሞት ለሚገባን ህዝብ በመሆኑ ደስ እያለን ታግለናል፣ እንታገላለንም” ብላለች ምክትል ሳጀን ዓለምነሽ፡፡
ህግ የማስከበሩ ርምጃ ለኢትዮጵያዊያን የጋራ ጠላት በሆነው ህገወጥ ቡድን መክሰም ላይ ያነጣጠረ እንደነበርም ሃምሳ አለቃ ከድር አህመድ ነግሮናል፤ ለዚህም ግዳጃቸውን በአግባቡ እየተወጡ እንደሆነ አስረድቷል፡፡ “በርካታ ትግሎችን አልፈን የመጣን ነን፤ ወደፊትም ሃገር እና ህዝብ በፈለገን ግዳጅ ሁሉ ስኬታማ ሥራዎችን እንፈፅማለን” ነው ያለው፡፡
በአማራ ልዩ ኃይል የጣና ብርጌድ ምክትል አዛዥ ኮማንደር አበራ ጌታሁን የልዩ ኃይል አባላቱ ከጂምሩ እስከ አሁን ድረስ የተሰጣቸውን ግዳጅ በብቃት እየፈፀሙ መሆኑን ተናግረዋል፤ የአማራ ህዝብ እና መንግስት ለልዩ ኃይል አባላቱ ከትጥቅ እስከ ስንቅ ያደረጉት ድጋፍ ትልቅ ጉልበት እንደሆናቸውም ኮማንደር አበራ አንስተዋል፤ ቀሪ ህግ የማስከበሩን ርምጃ በብቃት ለማጠናቀቅም ሰራዊቱ በሙሉ አቅሙ ዝግጁ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡
በራያ አካባቢም ህግ በማስከበር ተልዕኮው ውስጥ የየአካባቢው ማኅበረሰብ ለሰራዊቱ ላለው ቀና ድጋፍ እና ትብብር አባላቱ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው -ከአላማጣ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“ሕወሓትና ኦነግ ሸኔ በዓለም ላይ ያለ አሸባሪ የሚሠራውን ሁሉ ሠርተዋል፤ በአሸባሪነት ለመፈረጅም መረጃዎች ከበቂ በላይ ሞልተው ፈስሰዋል” የሕግ ምሁራን
Next article“ተማሪዎች፣ መምህራንና የትምህርት ቤት አስተዳደሮች የኮሮና ቫይረስን በመከላከል አርዓያ መሆን አለባቸው” ዶክተር ሙሉነሽ አበበ