“ሕወሓትና ኦነግ ሸኔ በዓለም ላይ ያለ አሸባሪ የሚሠራውን ሁሉ ሠርተዋል፤ በአሸባሪነት ለመፈረጅም መረጃዎች ከበቂ በላይ ሞልተው ፈስሰዋል” የሕግ ምሁራን

480

“ሕወሓትና ኦነግ ሸኔ በዓለም ላይ ያለ አሸባሪ የሚሠራውን ሁሉ ሠርተዋል፤ በአሸባሪነት ለመፈረጅም መረጃዎች ከበቂ በላይ ሞልተው ፈስሰዋል” የሕግ ምሁራን

ባሕር ዳር: ኅዳር 22/2013 (አብመድ) መንግሥት ሕወሓትንና ኦነግ ሸኔን በአሸባሪነት ሊፈርጃቸው እንደሚገባ የሕግ ምሁራን መከሩ፡፡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ ልዩ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ እንዲሰጡባቸው ከምክር ቤት አባላት ከቀረቡ ጥያቄዎች መካከል ሕወሓትንና ኦነግ ሸኔን በአሸባሪነት መፈረጅ አንዱ ነው፡፡ ከምክር ቤት አባላት በጉዳዩ ላይ ተደጋግሞ የተነሳው ጥያቄ ተገቢና የሚጠበቅ መሆኑንም የሕግ ምሁራን ተናግረዋል፡፡
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምሕርት ቤት መምህር ተመስገን ሲሳይ እንዳሉት ኢትዮጵያ የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ያጸደቀችው አዋጅ ቁጥር 1176/2012 ሽብርተኝነትን በማያሻማ መልኩ አስቀምጦታል፡፡ የተቀመጡ የሽብር ድርጊቶች በሙሉ በኢትዮጵያ መፈጸመዋቸውንም አቶ ተመስገን ተናግረዋል፤ የድርጊቱ ባለቤት የሕወሓት መሪዎች መሆናቸውንም የመንግሥትን ተደጋጋሚ መግለጫ ዋቢ አድርገው አብራርተዋል፡፡
በወሎ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ሕግ መምህር ደጀን የማነ እንዳሉት ኦነግ ሸኔ ቦኮሀራም የተባለው የአሸባሪ ቡድን ናይጀሪያ ላይ እንደሚያደርገው የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ካገተ ቆይቷል፤ ንጹኃን ዜጎችን በተለይ ዘርን በመለየት አማራውን አሰቃይቷል፤ ገድሏል፤ ልዩ ልዩ የሽብር ድርጊቶችንም ፈጽሟል፡፡
ሕወሓት ደግሞ ኢትዮጵያን ባስተዳደረባቸው 27 ዓመታት መንግሥታዊ ሽብር መፈጸሙን በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ተናግረው ነበር፡፡ ከለውጡ በኋላም ብዙ ግፍና መከራን ፈጽሟል፤ በቅርቡም በማይካድራ ንጹኃን ላይ የተፈጸመው ጭፍጨፋ በዓለም አቀፍ ደረጃ አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው አይ ኤስ ኤስ በተለያዩ የዓለም ሀገራት ንፁሃንን ከገደለበት ይበልጥ ዘግናኝ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
በኢትዮጵያ ሽብርተኛን የመፈረጅ ስልጣን የተሰጠው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ ነገር ግን ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ቀድሞ ጉዳዮችን በማጣራት ቡድኖቹ በሽብርተኝነት እንዲፈረጁ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ሀሳብ ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤትም ጉዳዩን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀርባል፡፡ አቶ ተመስገን እንዳብራሩት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወደ ፍረጃ ከመግባቱ በፊት ለቡድኖቹ በመደበኛ መገናኛ ብዙኃን ጥሪ በማድረግ ጉዳዩን ያሳውቀዋል፡፡
አቶ ደጀን በሰጡት ማብራሪያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስልጣንና ተግባር ሕግ ማውጣትና ውሳኔ ማሳለፍ ቢሆንም አስፈጻሚ አካላት በጉዳዩ ላይ ቸልተኛ ከሆኑ ጥያቄ አንስቶ ያስፈጽማል፡፡ በምክር ቤት አባላቱ የተነሳው ጥያቄም ለዚህ ማሳያ እንደሚሆን አመላክተዋል፡፡ አቶ ደጀን “ሕወሓትና ኦነግ ሸኔ በዓለም ላይ ያለ አሸባሪ የሚሠራውን ሁሉ ሠርተዋል፡፡ በአሸባሪነት ለመፈረጅም መረጃዎች ከበቂ በላይ ሞልተው ፈስሰዋል” ብለዋል፡፡
በሽብር መፈረጅ ግልፅ የሆነ የሕግ መስፈርት እንዳለው በመጥቀስም ሁለቱ ቡድኖች ግን ከዚያ የዘለለ ዓለም አቀፍ የዘር ማጥፋት ወንጀሎችንና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መፈጸማቸውን አንስተዋል፡፡ መንግሥት በሽብርተኝነት ለመፈረጂ ያሳየው ዳተኝነትም ተገቢ እንዳልሆነ አመላክተዋል፡፡
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምሕሩ አቶ ተመስገን እደተናገሩት አስፈጻሚው አካል ለሕግ አውጪው ከማቅረቡ በፊት መረጃዎችን በተገቢው መንገድ በማጤን የተፈጸሙ ተጨባጭ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይኖርበታል፡፡ በሽብርተኝነት ለመፈረጅ መዘግየቱም ከአዋጁ የአሰራር ሥነ ሥርዓት እንደሆነ አመላክተዋል፡፡
የሽብር ድርጊቱ የተፈጸመ ቢሆንም የኢትዮጵያ መንግሥት ብቻ አሸባሪ ብሎ ቢፈርጅ ውጤታማነቱ እምብዛም ስለሚሆን በቂ ጊዜ ወስዶ የኢትዮጵያ ወዳጅ ሀገራትን የሚያሳምን ማስረጃ ማደራጀት እንደሚያስፈልግም መክረዋል፡፡
ይሁን እንጂ አቶ ደጀን እንደሚሉት ለሀር የሚጠቅም ውሳኔ እስከተላለፈ ድረስ የዓለም ዓቀፉ ማሕበረሰብ ጉዳይ በሁለተኛና በሦስተኛ ደረጃ የሚታይ ነው፡፡ መንግሥት የሚጠቅሳቸው ጥቂት ግለሰቦች በወንጀል የሚጠየቁ ቢሆንም ሕወሓት እንደ ድርጅት ምን እየሠራ ነው፣ ዓላማውስ ምን ነበር የሚለው ጉዳይ በደንብ ታይቶ በሽብርተኝነት መፈረጅ ይገባል ብለዋል፡፡
በአዲሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ መሰረት ኃይል የሚጠቀም፣ ወደ ብጥብጥ የሚገባና ሕገወጥ አካሄድን የመረጠ የፖለቲካ ፓርቲ ሕጋዊ ሰውነቱ ይሠረዛል፡፡ ይሁን እና የክልል የምርጫ ቦርድ አቋቁሞ ሕገወጥ ምርጫ ከማካሄድ ጀምሮ ርዮተ ዓለሙን በትጥቅ ለማሳካት በሞከረው ህውሀት ላይ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በዝምታ መመልከቱ ተገቢ እንዳልሆነም የሕግ ምሁሩ ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ ከሕጋዊ ፖለቲካ ፓርቲ ዝርዝር ውስጥ በመሠረዝ ፓርቲውን በሽብርተኝነት መፈረጅ እንደሚገባም መክረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleለክልል አቀፍ የስምንተኛ ክፍል ፈተና በቂ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡
Next articleየጁንታው ቡድን ለፍርድ እስኪቀርብ በላቀ ጀግንነት የጀመሩትን ትግል እንደሚቀጥሉ የአማራ ልዩ ኃይል አባላት ተናገሩ፡፡