ለክልል አቀፍ የስምንተኛ ክፍል ፈተና በቂ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

797

ለክልል አቀፍ የስምንተኛ ክፍል ፈተና በቂ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

ባሕር ዳር: ኅዳር 22/2013 (አብመድ) ተማሪ ጌጤ አየነው በባሕር ዳር የሰርፀ ድንግል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ናት፡፡ የመማር ማስተማር ሥራው ተቋርጦ የነበረ ቢሆንም ስታጠና መቆየቷን ተናግራለች፡፡

ተማሪ አማኑኤል ዘመኑ በበኩሉ “ሰፊ ጊዜ አለን፤ በዚህ ጊዜ ከተጠቀምንበት ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ እንችላለን” ሲል ሃሳቡን ገልጿል፤ ሌሎች ተማሪዎችም ጊዜቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ በመምከር፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ይልቃል ከፋለ (ዶክተር) ክልል አቀፍ የስምንተኛ ክፍል ማጠቃለያ ፈተና ከታኅሣሥ 12 እስከ ታኅሣሥ 14/ 2013 ዓ.ም ድረስ በሁሉም የክልሉ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደሚሰጥ ገልፀዋል፡፡
በ2013 የትምህርት ዘመን በክልሉ በሚገኙ 5 ሺህ 162 ትምህርት ቤቶች በመደበኛ፣ በግልና በማታ መርሀ ግብር የተማሩ 415 ሺህ 130 ተማሪዎች የስምንተኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና ይፈተናሉ፡፡
በ2012 ዓ.ም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወደ ሃገራችን መግባትን ተከትሎ ትምህርት መቋረጡ ይታወሳል፡፡ በዚህም የስምንተኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና እና የ12ኛ ክፍል ሀገረ አቀፍ ማጠቃለያ ፈተና በኅዳር ወር 2013 ዓ.ም ለመስጠት እቅድ ተይዞለት ነበር፡፡ እቅዱን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ ተግባራት ቢከናወኑም ሀገራችን በነበረባት ህግ የማስከበር ሥራ ድጋሚ መቋረጡን ትምህርት ቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
በተለይ በሰሜን ወሎ፣ በዋግኽምራ፣ ሰሜን ጎንደርና ማዕከላዊ ጎንደር አካባቢ የሚገኙ ትምህር ቤቶች ስጋት የነበረባቸው እንደነበሩ ጠቅሰዋል፡፡ በሃገሪቱ በተፈጠረው የተደራረበ ችግር ምክንያት በመማር ማስተማር ሥራው ላይ ተጽዕኖ ቢደርስም ለተማሪዎች የማካካሻ ትምህርት በመስጠት ማጠቃለያ ፈተና እንደሚሰጥ አስታውቀዋል፡፡
የትምህርት ቢሮ ኃላፊው ተማሪዎች በአጭር ጊዜ ትምህርታቸውን በመከለስና ራሳቸውን በማረጋጋት በራስ የመተማመን ስሜት መፍጠር አለባቸው ብለዋል፡፡ ተማሪዎች “ፈተናው ይከብደናል” የሚለውን አስተሳሰብ ከሃሳባቸው በማስወገድ ተገቢውን ዝግጅት ሊያደርጉ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ዶክተር ይልቃል ከፋለ መምህራን እና ሌሎች የትምህርት አመራሮች ተማሪዎች በዚህ አጭር ጊዜ ተገቢውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ፈተናውን የሚፈተኑበትን ሁኔታ ሊያመቻቹ ይገባል፤ ወላጆችም ተማሪዎችን ማበረታታትና መደገፍ አለባቸውም ብለዋል፡፡
ፈተናውን ለመስጠትም ተገቢ የሆኑ ቅድመ ዝግጅቶች መከናዎናቸውን፤ ፈተናውም ተዘጋጅቶ በክልሉ በሚገኙ በሁሉም ዞኖች መሰራጨቱን ዶክተር ይልቃል አስታውቀዋል፡፡
ሁሉም ወረዳዎች በፈተናው የሚሳተፉ መምህራንን በማዘጋጀት ላይ መሆናቸውን እና ፈተናውን የሚያስተጓጉሉ ነገሮች እንዳይፈጠሩከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጥምረት እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበከተሞች የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ስርጭት አማካይ 4 በመቶ መድረሱን የአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ አስታወቀ፡፡ ወጣቶች ለኤች አይቪ ያላቸው ግንዛቤ ዝቅተኛ እንደሆነም ቢሮው ገልጿል፡፡
Next article“ሕወሓትና ኦነግ ሸኔ በዓለም ላይ ያለ አሸባሪ የሚሠራውን ሁሉ ሠርተዋል፤ በአሸባሪነት ለመፈረጅም መረጃዎች ከበቂ በላይ ሞልተው ፈስሰዋል” የሕግ ምሁራን