
በከተሞች የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ስርጭት አማካይ 4 በመቶ መድረሱን የአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ አስታወቀ፡፡ ወጣቶች ለኤች አይቪ ያላቸው ግንዛቤ ዝቅተኛ እንደሆነም ቢሮው ገልጿል፡፡
ባሕር ዳር: ኅዳር 22/2013 (አብመድ) ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ እየጨመረ እንደሚገኝ ከአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ ያገኘነው መረጃዎች ያመላክታል፡፡ ለዚህ ደግሞ በየጊዜው በሚፈጠሩ ግጭቶችና የሰላም መደፍረስ ለኤች.አየ.ቪ.ትኩረት አለመስጠት በምክንያትነት ተነስቷል፡፡
የአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከል እና መቆጣጠር ዕቅድ ክትትል ባለሙያ አቶ መልካም ዳኛው እንደገለጹት በሀገሪቱ ባለፉት ዓመታት በተከሰተው የጸጥታ ችግር ምክንያት ለኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ትኩረት ሰጥቶ ለመስራት አስቸግሮ ቆይቷል፡፡ በዚህም ምክንያት በክልሉ ስርጭቱ እየጨመረ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡
በተለይም ደግሞ በከተሞች ስርጭቱ ከፍተኛ መሆኑን አቶ መልካም ገልጸዋል፡፡ በዚህም በአማራ ክልል ከሚገኙ ከተሞች ውስጥ 95 በመቶ በሚሆኑት የኤች. አይ.ቪ/ኤድስ ስርጭት አማካይ 4 ነጥብ 1 በመቶ መሆኑን ነግረውናል፡፡ ሴተኛ አዳሪዎች፣ ረጅም ርቀት አሽከርካሪዎች እና የቀን ሰራተኞች ደግሞ ለዚህ የበለጠ ተጠቂዎች ናቸው፡፡
ባለሙያው እንደገለጹት ወጣቶች ለኤች. አይ.ቪ/ኤድስ ያላቸው ግንዛቤ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ በዚህም ወጣት ሴቶች ስለቫይረሱ ያላቸው ግንዛቤ 24 በመቶ ሲሆን የወጣት ወንዶች ግንዛቤ ደግሞ 36 በመቶ መሆኑን ነው የገለፁት፡፡
ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን ለመከላከል መንግስት ከሚያከናውነው ተግባር ባሻገር ቫይረሱ በደማቸው ያለባቸው ሰዎች ማሕበራት ከፍተኛ ስራ ሲሰሩ መቆየታቸውን ባለሙያው ነግረውናል፡፡ ይሁን እንጅ የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩ ድርጅቶች ድጋፋቸውን ማቋረጣቸውን ተከትሎ ማኅበራቱ በመፍረሳቸው ለመከላከል ስራው መዳከም በምክንያትነት አንስተዋል፡፡
ጤና ጥበቃ ቢሮ በተቋማት እና በአደረጃጀቶች በኩል የግንዛቤ ፈጠራ ስራ እያከናወነ ቢሆንም በቂ አለመሆኑን እና በሀገሪቱ በተፈጠረው ችግር ምክንያት በታሰበው ልክ አለመሰራቱን ባለሙያው ገልጸዋል፡፡
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም መንግስት ከማሕበረሰቡ ጋር ተቀናጅቶ በትኩረት መስራት ካልቻለ ስርጭቱ እንደሚጨምር ነው ባለሙያው ያስገነዘቡት፡፡
የአለም የፀረ-ኤድስ ቀን በዓለም ለ33ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ32ኛ ጊዜ ‹‹ኤች.አይ.ቪ/ ኤድስን ለመግታት ዓለም አቀፋዊ ትብብር የጋራ ኃላፊነት›› በሚል መልዕክት ዛሬ እየታሰበ ነው፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሰራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ