
በማይካድራ ህይወታቸው ያለፉ ዜጎች ቁጥር ብዛት ሊጨምር እንደሚችል ተገለጸ፡፡
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 22/2013 ዓ.ም (አብመድ) በማይካድራ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ሊያሻቅብ እንደሚችል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈፃፀም እየመረመረ ያለው ቦርድ ያገኛቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
መርማሪ ቦርዱ ሰሞኑን በማይካድራ ከተማ ባደረገው የመስክ ምልከታ በከተማዋ ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ስለተፈጸመው አሰቃቂ የግድያ ወንጀል በቦታው ተገኝቶ መረጃ ሰብስቧል፡፡
ወንጀሉ እጅግ ዘግናኝና ዘርን መሰረት ያደረገ ስለመሆኑ የመርማሪ ቦርዱ አባላት ያነጋገሯቸው የአይን እማኞችና ከግድያ ሙከራው የተረፉ ወገኖች እንዲሁም የሟች ቤተሰቦች አስረድተዋል፡፡
የመርማሪ ቦርዱ አባላት ከ50 እስከ 60 አስከሬኖች በአንድ ላይ የተቀበሩባቸውን ቦታዎች ተዘዋውረው ተመልክተዋል፤ በማይካድራ አቡነ አረጋዊ ቤተ ክርስቲያን ያሉት መቃብሮችም ቢሆኑ ከ6 እስከ 12 አስከሬኖች በአንድ ላይ የተቀበሩባቸው ናቸው፡፡
የሟቾችን ቁጥር በተመለከተ ቀደም ሲል የተለያዩ ሚዲያዎችና የሰብዓዊ መብት ተቋማት 600 መሆኑን ባወጡት ሪፖርት የጠቀሱ ቢሆንም፤ መርማሪ ቦርዱ ባገኘው መረጃ ግን የሟቾቹ ቁጥር ሊያሻቅብ እንደሚችል ነው፡፡
ቦርዱ የምርመራ ስራውን እያከናወነ ባለበት ወቅት በአካባቢው የሚገኘው ጊዜያዊ አስተዳደር ገና ያልደረሰባቸው አስከሬኖች በአካባቢው ከሚኖሩ ሰዎች እየተጠቆመ የምርመራ ቡድኑ አባላት እንዲያዩት ተደርጓል፤ በተለይ “ሸለላ መውጫ” በተባለው አካባቢ በአንድ ገደል ውስጥ የተገኙት አስከሬኖች የተደራረቡ በመሆናቸው ብዛታቸውን ለማወቅ እንኳን አልተቻለም ነበር፡፡
በወቅቱ በአካባቢው የነበረው የሚሊሻና የፖሊስ ጸጥታ መዋቅር የፌዴራሉን የሀገር መከላከያ ሰራዊት እርምጃ ሸሽቶ አካባቢውን ለቆ ከመውጣቱ በፊት “ሳምሪ” ከተባለ መደበኛ ያልሆነ የትግራይ ወጣቶች ቡድን ጋር በማበር የፈጸሙት ወንጀል ስለመሆኑ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡
“ሳምሪ” የተባለው የወጣቶች ቡድን አሰቃቂ ወንጀሉን ቢፈጽምም፤ በአንጻሩ የትግራይ ተወላጅ ከሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አጥቂው ቡድን ሲያሳድዳቸው የነበሩ ሰዎችን በቤታቸው፣ በቤተክርስቲያንና በእርሻ ቦታዎች በመደበቅ የብዙ ሰዎች ህይወት እንዲተርፍ ማድረጋቸውን መርማሪ ቦርዱ ያገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡
የመርማሪ ቦርዱ አባላት ተጎጂዎቹ በብዛት በሚኖሩበትና በተለምዶ “ግንብ ሰፈር” በተባለው አካባቢ ተገኝተው ከሟች ቤተሰቦችና ከግድያ ሙከራው ከተረፉ ሰዎች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ለማ ተሰማ ከጉዳቱ ሰለባዎች ጋር በተወያዩበት ወቅት የጉዳቱን ኢ-ሰብዓዊነት ገልጸዋል፤ መንግስት ወንጀለኞቹን አድኖ ለፍርድ እንዲያበቃ ለማገዝ እንደሚሰሩ በመግለጽ የተጎጂ ቤተሰቦችን አጽናንተዋል፡፡
መረጃው ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይፋዊ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘ ነው፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m